1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሪህ ምንድነው? መንስኤና ምልክቶቹስ

ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 5 2016

የመገጣጠሚያ ላይ እብጠትና ብግነት ወይም ከባድ ህመም የሪህ ህመም እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። በእርግጥ ሪህ ህመም ምንድነው? መንስኤው ይታወቃል? ሪህ በሽታ በዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች እንዴት ይገለጻል?

የሪህ ህመም እብጠት
መገጣጠሚያ ላይ እብጠት የሚያስከትለው የሪህ ህመም እብጠት ፎቶ ከማኅደርምስል picture-alliance/Okapia

ሪህ ምንድነው? መንስኤና ምልክቶቹስ

This browser does not support the audio element.

የሪህ በሽታ ምንነት

ስለሪህ ህመም በብዙዎች ዘንድ ያለው ግንዛቤ በጥቁር አንበሳ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል፤ የውስጥ ደዌ ከፍተኛ ሀኪም እና የሮማቶሎጂ ንዑስ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ዶክተር ብርሃኑ ደምመላሽ ከገለጹት ይለያል። ብዙዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እግሬን ቆረጠመኝ፤ እግሬ ተሳሰረ፤ አለያም እግሬን በጣም ያመኛል ሪህ ነው ሲሉ ይደመጣል። ለሪህ ህመም እንደዋነኛ መንስኤነት የሚጠቀሱ ምግቦችም አሉ፤ አዘውትሮ የበሬ ሥጋ መመገብ፤ ጮማና ቅባት አብዝቶ መብላት ለዚህ በምክንያትነት በግንባር ቀደምትነት ይነሳሉ።

የውስጥ ደዌ ከፍተኛ ሀኪም እና የሮማቶሎጂ ንዑስ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ብርሃኑ ደምመላሽ ዶክተር ብርሃኑ ደመላሽ ሪህ በሽታ በጣም የተለመደው በህክምናው አርትራይተስ ተብሎ የሚጠራው መገጣጠሚያ ላይ ከሚከሰቱ የቁርጥማት ዓይነቶች አንዱ ህመም ነው ይሉታል። እንደ የህክምና ባለሙያው አንድ ሰው ሪህ ታሟል ለማለት የግድ በመገጣጠሚያው ላይ እብጠት መኖር አለበት። እብጠቱም ከባድ ህመምና ስቃይ አለው ነው የሚሉት።

የሪህ ህመም ምልክቶችና ዩሪክ አሲድ

ዶክተር ብርሃኑ ስለ ሪህ ህመም ምልክቶች ሲናገሩ «የመገጣጠሚያ ላይ እብጠት፣ አካባቢው መቅላት፤ ኃይለኛ የሚያሰቃይ ሕመም» ዋና መገለጫዎቹ ናቸው ይላሉ።  

የሪህ ህመም በሰውነት ውስጥ ዩሪክ አሲድ የሚባለው ንጥረ ነገር ከመጠን በላይ የመከማቸቱ ውጤት እንደሆነ ነው የሚገለጸው። በሰውነት ውስጥ የዩሪክ አሲድ ክምችት መጠኑ መብዛት ብቻውን ግን አንድ ሰው በሽታ አለበት  ለማለት እንደማይቻል ነው ባለሙያው የተናገሩት። በምሳሌ ሊያስረዱም አንድ መቶ የሆኑ ዕድሜያቸው በአርባዎቹ እና ከዚያም በላይ የሆነ ጎልማሶችን የዩሪክ አሲድ መጠን ቢመረመር፤ ከመካከላቸው 20ዎቹ ላይ መጠኑ ሰባትም፤ ስምንትም፤ ዘጠኝና ከዚያ በላይ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች በሪህ ህመም ተይዘዋል ማለት አይደለም። ማሳሰቢያ እንደመሆኑ አመጋገባቸውን በመቆጣጠር፤ በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ እያደረጉ ይበልጥ የዩሪክ አሲዱ መጠን እንዳይጨምር ማድረግ ይኖርባቸዋል።

የሪህ ህመም በጉልበት መገጣጠሚያ ላይም የሚከሰትበት ጊዜ አለፎቶ ከማኅደርምስል Colourbox

ዶክተር ብርሃኑ እንደሚሉት የዩሪክ አሲዳቸው መጠን ከፍተኛ የሆነ ሰዎች የመገጣጠሚያ ላይ እብጠትና ህመም ሳይኖረው የአሲዱን መጠን ለመቀነስ በሚል ህክምና ማድረግ አይመከርም። ቢሞከር እንኳን እስከ አምስት ዓመት ድረስ ሊወስድ ይችላል፤ ይህ ደግሞ ከወጪም አኳያ አዋጣም ባይ ናቸው።

ዩሪክ አሲድን የመቀነስ ሙከራ

ዩሪክ አሲድ በሰውነት ውስጥ ከፍ ለማለቱ አመጋገብ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ይነገራል። ስጋና ስብ ብቻ ሳይሆን ጣፋጭ ምግቦችም ለዩሪክ አሲድ መፈጠር ብሎም ለሰውነት ክብደት መጨመር ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ በማመልከት ያለውን ትስስር ዶክተር ብርሃኑ ይገልጹታል።

የውስጥ ደዌ ከፍተኛ ሀኪም እና የሮማቶሎጂ ንዑስ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ እንደሚሉት አንድ ሰው በሰውነቱ ውስጥ ያለው የዩሪክ አሲድ ክምችት ከፍ ያለ መሆኑ ለሪህ ህመም ተጋላጭነቱን ይጨምረዋል እንጂ የግድ ግለሰቡ የሪህ ታማሚ ነው ለማለት አይቻልም። ይህ ሁኔታ ወደ ሪህ ህመምነት የሚሸጋገረው በመገጣጠሚያ ላይ እብጠት ሲኖር እብጠቱም የሚያሰቃይ የህመም ስሜት ሲያስከትል ነው። በነገራችን አድማጮች መገጣጠሚያ አካል ላይ ስቃይ የሚያስከትለው ይህ ህመም ሪህ ተብሎ በጥቅል ይገለጽ እንጂ ዓይነቱ ወደ አንድ መቶ እንደሚደርስ ነው ባለሙያው ያብራሩት።

ለሪህ የሚደረግ ምርመራ

ከእብጠት ጋር የሚገናኘውን የሪህ ህመም በምርመራ እንዴት ማወቅ እብጠት ካለበት የመገጣጠሚያ አካል ላይ ናሙና ወስዶ መመርመር እንደሚያስፈልግ ነው ባለሙያው የገለጹት። እብጠቱ አውራ ጣትም ላይ ይሁን ጉልበት ላይ ወይም ሌላ አካል ናሙናው የሚወሰደው ከዚያ አካባቢ መሆን አለበት። እብጠቱ የተከሰተው በርከት ባሉ የተለያዩ የመገጣጠሚያ የሰውነት ክፍሎች ላይ ከሆነ ግን በደም እና በአልታሳውንድ እንዲሁም ኤም አር አይ ላይ ምርመራው መደረግ ይኖርበታል።

በሰውነት ውስጥ ያለውን የፕሮቲን ክምችት ለመርመር የተወሰደ የደም ናሙናፎቶ ከማኅደር ምስል Pond5 Images/IMAGO

የሪህ ህመምን ለመከላከያ

ለመሆኑ ሪህ ህመም እንዳይከሰት አስቀድሞ መከላከል ይቻል ይሆን? ከተከሰተ በኋላስ በግሉ ታማሚው ሊያደርገው የሚችለው ጥንቃቄ አለ?

የዘርፉ የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ብርሃኑ ደምመላሽ እንደሚሉት የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል ቀዳሚው እርምጃ ነው። አመጋገብን በጥንቃቄ መከታተል፤ የሰውነት እንቅስቃሴ ማዘውተር፤ አልክሆል መጠጥን አለመጠጣት ቀዳሚዎቹ እርምጃዎች ይሆናሉ። እንደ ኩላሊት ህመምና ካንሰር ያሉ ተጓዳኝ ህመሞች ካሉ በቂ ህክምና እና ክትትል ማድረግ የዩሪክ አሲድን ክምችት በሰውነት ከፍ በማድረግ ለሪህ የመጋለጥ አጋጣሚን ለመቀነስ እንደሚረዳም መክረዋል። በተለይ በከተሞች የሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል በቂ እንቅስቃሴ ማድረግን እንዲያዘወትር፤ አመጋገቡ ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ፤ እንዲሁም አልክሆል መጠጣትን እንዲተውም አሳስበዋል። ለሪህ ተብለው የሚወሰዱ አደገኛ መድኃኒቶች መኖራቸውን ያመለከቱት ባለሙያው፣ ኅብረተሰቡ እንዲህ ያሉ ልምምዶችን እንዲተው አሳስበዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ የህክምና መረጃዎች የሚያመለክቱት የአኗኗር ዘይቤ መለወጥ የሰዎችን ጤና ለከባድ የህመም ዓይነቶች እያጋለጠ መምጣቱን ነው። በተለይ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ ዋናው የጤና ጠንቅ እንደሆነ እየተነገረ ነው። አመጋገብ ላይ ጥንቃቄ እያደረጉ እንቅስቃሴን ማዘውረት ጤናን ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ነው  የውስጥ ደዌ ከፍተኛ ሀኪም እና የሮማቶሎጂ ንዑስ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ብርሃኑ ደምመላሽ ያሳሰቡት። አድማጮች  በአዲሱ ዓመት በ2017 ዓ ዋዜማ ለጤናችን ትኩረት እንድንሰጥ ያሳሰቡንን ዶክተር ብርሃኑን ከልብ በማመስገን አዲሱ ዓመት በጎ ነገር የምንሰማበት፤ በጤና የምንኖርበት እንዲሆን በመመኘት እንሰናበታለን።

 ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW