ሪዮ ዲ ጄኒሮ፤ የብሪክስ አባል ሃገራት የመሪዎች ጉባኤ ብራዚል ውስጥ ዛሬ ተጀመረ
እሑድ፣ ሰኔ 29 2017
ሁለቱን የምስራቁ ዓለም ኃያላን የሩስያ እና ቻይና መሪዎች ያልተገኙበት የብሪክስ አባል ሃገራት የመሪዎች ጉባኤ ሪዮ ዲ ጄኒሮ ብራዚል ውስጥ ዛሬ ተጀመረ። ለሁለት ቀናት ይቆያል በተባለው ጉባኤው ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጠንካራ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ምላሽ መስጠትን ጨምሮ በዋና ዋና የጥምረቱ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሏል። ብራዚል የወቅቱ ፕሬዚዳንት በሆነችበት የጥምረቱ ጉባኤ የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ቺንፒንግ አለመገኘታቸው ተዘግቧል። ይህም የፕሬዚዳንቱ በጉባኤው አለመገኘት ብሪክስ ከተመሰረተ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም እንዲሁ በጉባኤው ያልተገኙ ሲሆን ምክንያታቸው ደግሞ በዩክሬን ላይ ወረራ ፈጽመዋል በሚል በዓለማቀፉ የወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት የክስ ማዘዣ ዋራንት ወጥቶባቸው ስለነበር ነው ተብሏል። ጉባኤተኛው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለተከተሉት ጠንካራ የቀረጥ ፖሊሲ አቋማቸውን በአንድነት ለመግለጽ መዘጋጀታቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዲ ፒ ኤ ዘግቧል።
ጉባኤው በተጨማሪ የጤና ፖሊሲ ፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ዓለማቀፍ የአየር ንብረት ጥበቃ በዋነናነት ትኩረት እንደሚሰጡበት ነው የሚጠበቀው።
ብራዚል ፣ ሩስያ ፣ ህንድ ፣ ቻይና ፣ እና ደቡብ አፍሪቃ በጥምረት የመሰረቱት እና በኋላም ኢትዮጵያ ፣ ግብጽ ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ፣ የተቀላቀሉበት ጥምረቱ 48 በመቶ የዓለማችን የህዝብ ቁጥር እና 24 ከመቶ የኢኮኖሚ ድርሻ እንደሚይዙ ዘገባው አመልክቷል።
የብሪክስ አባል ሃገራት ጥምረት በኤኬኖሚ የበለጸጉ የቡድን ሰባት አባል ሃገራትን ለመገዳደር የተመሰረተ ጥምረት ነው። በጉባኤው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የተቀሩ የጥምረቱ ሃገራት መሪዎች እና ተወካዮች ታድመዋል።