ራማፎዛ የ ANC ፓርቲ መሪ ሆነዉ በድጋሚ ተመረጡ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 10 2015
የደቡብ አፍሪቃ ገዥ ፓርቲ የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ «ኤኤንሲ» በሙስና ተዘፍቀዋል የተባሉትን መሪዉን ሲሪል ራማፎዛን በፓርቲ መሪነት ዳግም መረጠ። ይህ የፓርቲዉ እርምጃ ሃገሪቱን እያስተዳደሩ ያሉትን ሲሬል ራማፎዛን ለሁለተኛ ፕሬዚዳንታዊ ስልጣን ዘመን የሚያበቃ ነዉ።
የ70 ዓመቱ አዛውንት ፕሬዚዳንት ሲሬል ራማፎዛ ፓርቲያቸዉ «ኤ ኤን ሲ» ለቀናቶች ባካሄደዉ ጉባዔ መጠናቀቅያ ላይ ባካሄደዉ ምርጫ ከ 4384 ድምፅ መካከል የ2476 ድምጽ ይሁንታን አግኝተዉ ነዉ ለዳግም የፓርቲዉ መሪነት ስልጣን የበቁት። ፕሬዚዳንቱ ከምርጫዉ በኋላ ባሰሙት ንግግር ብዙ ፈተና ቢገጥመንን ብዙ ሰርተናል ብለዋል።
«እንደ አውዳሚው የኮሮና ወረርሽኝ፣ ሃገሪቱ ዉስጥ ያጋጠምን የሕዝብ አለመረጋጋት፣ እንዲሁም በሃገራችን የተከሰተዉ የጎርፍ ማጥለቅለቅ ብሎም በመንግሥታችን ውስጥ ያሉት ሌሎች ፈታኝ ሁኔታዎች አቅማችን የፈቀደውን ያህል ሕዝባችንን ከማገልገል ወደኋላ እንድንል አድርገዋል። ይሁንና እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት ብዙ ማድረግ ችለናል ።»
የደቡብ አፍሪቃ ገዥ ፓርቲ የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ «ኤኤንሲ» ዉሳኔ ዛሬ የተሰማዉ ከጎርጎረሳዉያኑ 2018 ዓ.ም ጀምሮ በስልጣን ላይ የሚገኙት ሲሬል ራማፎዛ የሃገሪቱን የፀረ ሙስና ህግንም ሆነ ህገ መንግስቱን ጥሰዋል ተብሎ በሙስና መዘፈቃቸዉ እየተነገረና ከፍተኛ ትችትና ወቀሳ እየደረሰባቸዉ ባለበት በአሁኑ ጊዜ መሆኑ ነዉ።
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ