1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የያዙት ሻምበል ትራኦሬ

ቅዳሜ፣ መስከረም 28 2015

ረቡዕ በይፋ ሥልጣኑን የነጠቁት የ34 ዓመቱ ትራኦሬ ካዛሬ ሳምንት አርብ በፊት በሀገራቸውም ይሁን ከሀገራቸው ውጭ የሚያውቃቸው አልነበረም። ያለፈው ሳምንቱ መፈንቅለ መንግሥት ፣ ከሻምበልነት በአንዴ የዓለም ወጣቱ መሪ ካደረጋቸው በኋላ ታዋቂነታቸው በሀገራቸው ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ተዳርሷል።

Lage in Burkina Faso I 2. Oktober 2022
ምስል Vincent Bado/REUTERS

በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የያዙት ሻምበል ተራኦሬ

This browser does not support the audio element.

ያለፈው ሳምንቱ  የቡርኪናፋሶ መፈንቅለ መንግሥት የመሩት ፣ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ በዚህ ሳምንት ረቡዕ  የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት መሆናቸው በይፋ ታውጇል። ቃል አቀባያቸው ሻምበል ኪስዌንድሲዳ ፋሩክ አዛሪያ ሶርጎ በብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ፣ ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ ርዕሰ ብሔር፣እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሆነው መሰየማቸውን ተናግረዋል። ቃል አቀባዩ እንዳሉት ትራኦሬ« የአርበኞች ንቅናቁ ለደኅንነትና መልሶ ማቋቋም» የተባለው ሀገሪቱን ከጎሮጎሳዊው 2022 መጀመሪያ አንስቶ  ሲመራ የቆየው ወታደራዊው ኹንታ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሹመዋል። ወታደራዊው ኹንታ ከጎርጎሮሳዊው ጥር 2022 ዓ.ም. አንስቶ በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን በያዙት በሌተና ኮሎኔል ፓውል ሄነሪ ሳንዳኦ ዳሚባ ሲመራ ነበር። ሆኖም በዳሚባ አስተዳደር ቅር የተሰኙ የኹንታው አባላት፣ ባለፈው ሳምንቱ መፈንቅለ መንግስት እርሳቸውን ከስልጣን አውርደው ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬን በቦታቸው ተክተዋል። ቃል አቀባዩ የዳሚባ መንግሥት ተበትኖ ሕገ መንግሥቱም ለጊዜው ታግዷል፤ ድንበሩም ተዘግቷል ብለዋል። የፕሬዝዳንቱን ሃላፊነቶችም ዘርዝረዋል። 
«የአርበኞች ንቅናቄ ለደኅንነትና መልሶ ማቋቋም(ኤም ፔ ኤስ አር)ፕሬዝዳንት የብሔራዊ ነጻነት፣ የግዛት ሉዓላዊነት  ፣የሀገሪቱ መረጋጋትና ቀጣይነት ዋስትና ሰጭ እንዲሁም ቡርኪናፋሶ አባል የሆነችባቸውን ዓለም አቀፍ ውሎችና ስምምነቶች አክባሪ ይሆናል። » 
ረቡዕ በይፋ ሥልጣኑን የነጠቁት የ34 ዓመቱ ትራኦሬ ካዛሬ ሳምንት አርብ በፊት በሀገራቸውም ይሁን ከሀገራቸው ውጭ የሚያውቃቸው አልነበረም። ያለፈው ሳምንቱ  መፈንቅለ መንግሥት ፣ ከሻምበልነት በአንዴ የዓለም ወጣቱ መሪ ካደረጋቸው በኋላ ታዋቂነታቸው በሀገራቸው ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ተዳርሷል።በሀገራቸው በተለይም በዋና ከተማዋ ኡጋዱጉ እዚህም እዚያም ፎቶአቸው ተሰቅሏል።  የሻምበሉ ፎቶ፣በሰው እጅ ሕይወታቸው እንደጠፋው እንደ ቶማስ ሳንካራ ፎቶ በኦጋዱጉ ዋና የገበያ ስፍራ እየተቸበቸበ ነው። እስካሁን የዓለም ወጣት መሪን ክብረወሰን የያዙት በሁለት ዓመት የሚበልጧቸው የቺሊው ፕሬዝዳንት ጋብርየል ቦሪክ ነበሩ። የመፈንቅለ መንግሥት መነሻ ፣ከጥሩ መፈንቅለ መንግሥት ምክንያት ጋር ተመሳሳይ ነው ተብሏል። ያኔም ሆነ አሁንም ለመፈንቅለ መንግሥቱ ምክንያት የተባለው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ያጠፋውና ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን  ከቀያቸው ያሰደደው፣ የአክራሪ ጽንፈኞች ሰርጎ ገብ ጥቃት አለመቆም ነው ። ጥቃቱ ሰባት ዓመታት አስቆጥሯል።
ምዕራብ ቡርኪናፋሶ ውስጥ በምትገኘው ቦንዶኩቭ የተወለዱት ትራኦሬ የውትድርናውን ዓለም ከመቀላቀላቸው በፊት ጂኦሎጂ ተምረዋል።በጦር ሠራዊትነት ማግልገል የጀመሩትም የዛሬ 12 ዓመት ነው።ከዚያም  ጆርጅ ናሞናኦ ከተባለው ወታደራዊ ትምሕርት ቤት በመኮንንነት ተመረቁ ።ወታደራዊ ትምሕርቱን በሁለተኛነት ጨርሰው  በውትድርናው
ከጽንፈኛ ሰርጎ ገቦች ጋር ለዓመታት ይካሄድ በነበረው ውጊያም ብዙ ልምድ አካብተዋል።በውትድርና ከተሰለፉባቸው ግንባሮች መካከል ጽንፈኞች ክፉኛ ያጠቋቸው የነበሩት የሀገሪቱ ሰሜናዊ እና ማዕከላዊ ስፍራዎች ይገኙበታል። በጎርጎሮሳዊው 2018 በጎረቤት ማሊ በተሰማራው የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይል በምህጻሩ ሚኑስማ ስር ዘመቱ። በ2020 የሻምበልነት ማዕረግ ተሰጣቸው።ባለፈው ጥር የቀድሞው ወታደራዊ ኹንታ መሪ ዳሚባ በምርጫ ሥልጣን የያዙትን ፕሬዝዳንት ሮህ ማርክ ክርስቲያን ካቦሬን ከስልጣን ሲያወርዱ ትራኦሬ የአርበኞች ንቅናቄ አባል ሆኑ። በመጋቢት ወር ማዕከላዊ ቡርኪናፋሶ የሚገኝ መድፈኛ ጦር የመምራት ሃላፊነት ተሰጣቸው።  ዳሚባ ለትራኦሬ ይህን ሃላፊነት ሲሰጡ ውድቀታቸው አፋጠኑ። በትራኦሬ የሚመራው ጦር ቅሬታ ወደ ኡጋዱጉ ቢዝጎደጎድም ምላሹ ቁጣውን አባብሶ መፈንቅለ መንግሥቱን አስከትሏል።
በዚህ ሳምንት ረቡዕ ራሳቸውን የሽግግር ርዕሰ ብሔር አድርገው የሰየሙት ሻምበል ትራኦሬ  በርካታ ፈተናዎች ይጠብቋቸዋል።ከመካከላቸው ዋነኛው በአልቃይዳ እና እስላማዊ መንግሥት በሚባሉት ጽንፈኛ ቡድኖች ላይ የበላይነትን መያዝ ነው ።እነዚህ ቡድኖች በሀገሪቱ ጥቃት ከጀመሩበት ከዛሬ 7 ዓመት አንስቶ በቡርኪናፋሶ የተጠናከረ ጥቃት መሰንዘራቸው ቀጥሏል።ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም ዩናይትድ ስቴትስ አዲሱ የሽግግር መንግሥት ትራኦሬ የገለበጡዋቸው ዳሚባ የዛሬ ሁለት ዓመት በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሲቪል አስተዳደር  እንዲተካ የገቡትን ቃል እንዲያከብር አሳስባለች። ትራኦሬም ፣ቡርኪናፋሶ አባል ለሆነችበት የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ በምህጻሩ ኤኮዋስ ፣ በጎርጎሮሳዊው 2024 በሀገሪቱ የሲቪል አስተዳደር ለመተካት ዳሚባ የገቡትን ቃል እንደሚያከብሩ አስታውቀዋል። የኤኮዋስ ልዑካን በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ቡርኪናፋሶ ተገኝተው የሃይማኖትና የአካባቢ መሪዎችን እንዲሁም ትራኦሬን አነጋግረው መርካታቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።  ልዑካኑን የመሩት ሸምጋይ የቀድሞ የኒዠር ፕሬዝዳንት ማሃማዱ ኢሱፉ በተካሄደው ንግግር መርካታቸውን አስታውቀዋል። ከህዝቡ ጎን እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል። 
«ከሻምበሉ ጋር ባካሄድነው ንግግር ሙሉ በሙሉ ረክቻለሁ። የተለያየነውም በመተማመን ነው። ለኤኮዋስን ፕሬዝዳንትና ተልዕኮአችን ለሚመለከታቸውን ሌሎች ርዕሳነ ብሔራት ገለጻ እናደርጋለን። ኤኮዋስ ከህዝቡ ጋር እንደሚቆም እና  በተጋረጠበት በዚህ አስቸጋሪ ፈተና ወቅትም ህዝቡን ማገዛችንን እንደምንቀጥል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።»
ጽንፈኝነት የሚታገለው ገለልተኛው የምዕራብ  አፍሪቃ ማዕከል ሃላፊ ሙታሩ ሙሙኒ ሙክታር ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ግን የቡርኪናፋሶ ሁኔታ አሳሳቢ ነው።  ችግሩ በቡርኪናፋሶ ብቻ ሳይወሰን ወደ ጎረቤት ሀገራትና ከዚያም ባሻገር  እየተዛመተ መሆኑ ፈተናውን አክብዶታል።
«ባለፉት 6 ዓመታት በአካባቢው የሚሆነውን የሚከታተል ማንኛውም ሰው በጣም በጣም ይጨነቃል። በአሁኑ ጊዜ ሽብርተኝነትና የጽንፈኞች ጥቃት በሳህል ሀገራት ብቻ ሳይሆን ከነርሱ በታች ወደሚገኙ ሀገራትም እየተዛመተ ነው። የተቀላቀሉት የደኅንነት ስጋቶች ሁላችንንምሊያሳስቡ ይገባል። ጋናን የመሳሰሉትን ሀገራት ጭምር ያሰጋሉ። » 
ስጋቱ ቢያይልም፣ቡርኪናፋሶ ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ እየተረጋጋች መሆኑ ነው የሚነገረው። አዲሱን ፕሬዝዳንት የወደዱም በአደባባይ ሰልፍ ድጋፋቸውን መግለጻቸውን ቀጥለዋል።
 
ጉቦ ያሽመደመደው የአፍሪቃ ወደቦች ንግድ

ምስል Olympia de Maismont/AFP
ምስል RADIO TELEVISION BURKINA FASO/REUTERS
ምስል Vincent Bado/REUTERS

 

ከአፍሪቃ ወደቦች ባለሥልጣናት አብዛኛዎቹ ፣ምርመራን ለመሸሽ ኪሳራቸውን ሸሽገው ትርፋቸውን ብቻ ማሳወቅን ይመርጣሉ ይላል የዶቼቬለው የአይሳክ ሙጋቤ ዘገባ። እንደዘገባው የወደቦች ባለሥልጣናት በድረ ገጾቻቸው ላይ ኪሳራን የሚመለከቱ መረጃዎችን በየጌዜው ማደስ ሲገባቸው ይህን አያደርጉም።ለምሳሌ ከአፍሪቃ ወደቦች ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት ትልቁ የሌጎስ ወደብ  በጎርጎሮሳዊው 2022 የመጀመሪያው አራት ወራት አንድ ነጥብ 23 ቢሊዮን ዩሮ ገቢ አድርጓል። ሲሉ አስታውቀው ነበር።ማሪታይም ፀረ-ሙስና መረብ  የተባለውዓለም አቀፉ የባህር ንግድና የመርከበኞች ቡድን  እንዲሁም የሌጎስ ንግድ ምክር ቤትና ኢንዱስትሪ ናይጀሪያ በወደቦቿ በተንሰራፋ ሙስናና በስራ ብቃት ጉድለት ሰበብ በየዓመቱ የ7 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደሚደርስባት የናይጀሪያው ዘ ቫንጋርድ ኤንድ ቢዝነስዊክ ይፋ አድርጓል።  በናይጀሪያ ኩባንያዎች ገንዘብ እንዲሰጡ ይጠየቃሉ፤ ዛቻም ይሰነዘርባቸዋል።ሳሙኤል አዴቢሲ በሌጎስ ወደብ እቃዎችን ከወደቦች የሚቀበል  ወኪል ነው። እርሱ እንደሚለው ለጉምሩክ ባለሥልጣናት ጉቦ ሳይሰጥ እቃ ከወደቡ ማውጣት አይታሰብም። እንደ አዴቢሲ ባለሥልጣናት የተለያዩ ሕገ ወጥ የመቆጣጠሪያ ኬላዎችን በመትከል እቃ ጭነው ከሚወጡ መኪናዎች ገንዘብ ይቀበላሉ።ከዚህ ሌላ ወደ ወደቦች የሚወስዱ መንገዶች ተጨማሪ ፈተናዎች ሆነውባቸዋል። 
«የጉምሩክ ባለሥልጣናት ወደ ወደብ የሚወስደውን መንገድ ሳይጠግኑ ገንዘብ ይወስዳሉ።በመንገዶቹ መበላሸት የተነሳ አንዳንዴ ኮንቴይነሮች ከከባድ መኪናዎች ላይ ይወድቃሉ።በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ በመርከብ የወጡ እቃዎች የመኪና መለዋወጫዎችን ጨምሮ ይጠፋሉ።
የሌጎስ ነዋሪው ማዮዋ አድሎ ደግሞ ማናቸውም እቃዎች በመርከብ  ወደ ናይጀሪያ ሲላኩ ከመካከላቸው የተወሰኑት መሰረቃቸው የተለመደ ጉዳይ ነው ይላል።
«አውዲ Q7 የ2010 ሞዴል መኪናዬ ወደብ ላይ ይገኛል።መኪናዎችን ሲጋቹ የሚደርስባቸውn ጉዳት ሊቀንስ የሚችለው አካል እና ሌላም ተሰርቆብናል። እንዲህ ዓይነቱ ነገር ሁልጊዜ ይደርሳል። እንደሚመስለኝ ምክንያቱ ማንም የጉምሩክ ባለሥልጣናትን አይጫንም።»  
በናይጀሪያ ቁጥጥር የማይካሄድበት ሙስና ከወደቦች እቃ የሚጭኑ ሾፌሮችንም አማሯል። ብዙውን ጊዜ አሽከርካሪዎቹ በወደቦቹ አካባቢ ተቃውሞአቸውን ያሰማሉ።የወደቦች የስራ እንቅስቃሴ እንዲሻሻልም ጥሪ ያቀርባሉ።ከዚህ ቀደም የናይጀሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት የሚ ኦሲንባጆ በተለይ የሌጎስን ወደብ ከጎበኙ በኋላ በሰጡት መግለጫ ሁኔታዎች ይሻሻሉ ሲሉ ቃል ገብተው ነበር። 
«ይህ ለናይጀሪያ ወሳኝ የኤኮኖሚ ዋልታ ነው ምክንያቱም የገቢና የወጪ ምርቶቻችን በዚህ ነው የሚያልፉት።ስለዚህ አሁን በሚሰራበት ሁኔታ ልንቀጥል አንችልም።»
ኦሲንባጆ ችግሩን ለመፍታት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀታቸውንና በሁለት ስምንታት ውስጥ ሊሰሩ የሚገባቸውን ጉዳዮች ዝርዝር ማውጣታቸውን እነዚህንም ለማስፈጸም ቆርጠው መነሳታቸውን  በወቅቱ ተናግረው ነበር።ይሁንና  ፖለቲከኞች ቃል ቢገቡም ቃልን በተግባር መተርጎሙ ግን እንደማይሳካላቸው ነው በሌጎስ ወደብ አሁን የሚታየውየሚያስገነዝበው። በላይቤሪያው የሞኖሮቭያ ነጻ ወደብም  ተመሳሳይ ፈተናዎች አሉ።እቃ ለማስገባት የተዘረጋው ቢሮክራሲ፣በመኪናዎች ላይ የሚጣለው  ቀረጥ  ከፍተኛ መሆን እና ሙስና ሀገሬውን ከስራው እያስወጣ ንግዱ በውጭ ዜጎች እጅ እንዲገባ አድርጓል ሲሉ አቤቱታቸውን ለዶቼቬለ የተናገሩ አሉ።በጋናም እቃዎችን ከወደቦች ለመውሰድ የሚያስፈልገው የወረቀት ስራ ቢሮክራሲ ይበዛበታል።ከ70 በመቶ በላይ የሀገሪቱ ንግድ በወደቦች በሚካሄድባት በጋና ከፍተና ቀረጥ በንግዱ ሂደት ላይ ጫና ፈጥሯል። በደቡብ አፍሪቃም በተለይ በኬፕታውን ወደብ  እቃ ጭነው የሚመጡ መርከቦች ጭነታቸውን ሳያራግፉ ለሁለት ሳምንታት እንዲጠብቁ መደረጉ ትልቅ ችግር ነው ተብሏል።በሞዛምቢክ ሙስና የወደብ ተጠቃሚ ነጋዴዎች አስመርሯል። በዚያ ተራ ላለመጠበቅ ጉቦ መስጠት ግድ ሆኗል።ለነዚህ ችግሮች እንደ አንድ መፍትሄ የተቀመጠው  አብዛኛዎቹ የአፍሪቃ ወደቦች ስራቸውን በዲጂታል ስርዓት እንዲያካሂዱ ነው።የወደብ ባለሥልጣናትም ሙስናን መወጋት የሚችሉበትን መንገድ እንዲፈልጉ ይመከራሉ።

ምስል Leon Lestrade/African News Agency/RealTime images/ABACA/picture alliance
ምስል Benson Ibeabuchi/AFP/Getty Images

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW