1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስኢትዮጵያ

ራስ፤በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ሰው ሰራሽ አስተውሎትን መጠቀም የሚያስችለው መተግበሪያ

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 14 2017

እንደ ቻት ጂፒቲ ( ChatGPT)ያሉ በሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረቱ ዲጅታል መድረኮች በአብዛኛው በእንግሊዝኛ የሚሰሩ በመሆናቸው ለኢትዮጵያውያን ተጠቃሚዎች ምቹ አይደሉም። በሶስት ወጣቶች በቅርቡ ይፋ የሆነው ራስ መተግበሪያ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን (AI ) በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ለመጠቀም ዕድል የሚሰጥ ነው።

Symbolfoto ChatGBT kuenstliche Intelligenz
ምስል፦ Andreas Franke/picture alliance

ራስ፤በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ሰው ሰራሽ አስተውሎትን መጠቀም የሚያስችለው መተግበሪያ

This browser does not support the audio element.

የሰው ሰራሽ አስተውሎት በአሁኑ ወቅት በፍጥነት በማደግ ላይ ያለ ቴክኖሎጂ ነው። ይህ ቴክኖሎጂ ማሽኖች ከመረጃ እና ከድግግሞሽ እንዲማሩ በማድረግ እና ባገኙት መረጃ ላይ በመመስረት ሰዎችን ተክተው  በመስራት የተለያዩ ጠቀሜታዎችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

በተለይ እንደ ቻት ጂፒቲ ያሉ ( ChatGPT) በሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረቱ ዲጅታል መድረኮች  በዓለም ዙሪያ  የሚሊዮኖችን የዕለት ተዕለት ህይወት በማቃለል  ላይ ይገኛሉ።
ፕራይስ ዋተርሃውስ ኩፐርስ  የተባለው ዓለም አቀፍ የሙያ አገልግሎት ትስስር  (PwC ) በጎርጎሪያኑ 2017  ዓ/ም ባወጣው ጥናት መሠረት ሰው ሰራሽ አስተውሎት  በጎርጎሪያኑ 2030 ዓ/ም እስከ 14 በመቶ የሚሆነውን አጠቃላይ ምርት ሊያሳድግ ይችላል። ይህም በግምት 15.7 ትሪሊዮን ዶላር ለዓለም ኢኮኖሚ ይጨምራል ። ለአፍሪካም  የዚህ መርሃግብር ትርፍ 5.6% ማለትም ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP)  1.2 ትሪሊየን ዶላር ይሆናል። ይህም በአሁኑ ወቅት  በአህጉሪቱ ከሚገኝ ከየትናውም ሀገር፤ የሀገር ውስጥ ምርት ይበልጣል። 
ነገር ግን እነዚህ ዲጅታል መድረኮች  በአብዛኛው በእንግሊዝኛ የሚሰሩ በመሆናቸው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በራሳቸው ቋንቋ ለሚጠቀሙ የአፍሪቃ ሀገራት  ተጠቃሚዎች ምቹ አይደሉም።
ይህንን  ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያውያን የፈጠራ ባለሙያዎች የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል በሶስት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የተሰራው ራስ መተግበሪያ አንዱ ነው።
በቃሉ ተመስገን፣ባስላኤል ሰላሙ እና እዮብ ደስታ  በተባሉ ወጣቶች የተሰራው ይህ መተግበሪያም መነሻው ይህ መሰሉ ችግር መሆኑን ከመስራቾቹ አንዱ የሆነው በቃሉ ተመስገን ገልጿል።

የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተፅዕኖ በዲጅታል መድረኮች

በጎርጎሪያኑ 2023 ዓ/ም የቀረበ መረጃ እንደሚያሳየው 18% የሚሆነው የዓለም ህዝብ እንግሊዘኛ ይናገራል። ነገር ግን እንግሊዘኛ ከ 49% በላይ በሁሉም ድረ-ገጾች ላይ ጥቅም ላይ ይውላል።የእንግሊዘኛ ተፅዕኖ  እስከ መረጃ ቋት እና ስልጠና ድረስ የሚዘልቅ ሲሆን 90% የሚሆነው መረጃ የሚገኘው በእንግሊዝኛ ቋንቋ  ነው።ነገር ግን አፍሪቃ  ከ2,000 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባት አህጉር ሆና ሳለ፤ አብዛኛዎቹ ቋንቋዎች በዲጂታል መድረኮች ላይ እምብዛም አይገኙም።
ኔቸር መፅሄት ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ በሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ  (AI) ዘመን በአፍሪካ የሚነገሩ ቋንቋዎች ችላ እየተባሉ ነው። ለምሳሌ፣ ቻት ጂፒቲ ChatGPT በናይጄሪያ 94 ሚሊዮን ሰዎች በሚናገሩት በሃውሳ ቋንቋ  የተፃፉ አረፍተ ነገሮችን ከ10-20% ብቻ ነው የሚያውቀው። ምክንያቱም በስልጠና እና በመረጃ እጥረት እነዚህ ቋንቋዎች በትልልቅ የቋንቋ ሞዴሎች (LLMs) ዝቅተኛ ውክልና ነው ያላቸው። ይህም በሀገር በቀል ቋንቋዎች  ዲጅታል መድረኮችን መጠቀም  አስቸጋሪ ያደርጋል።ይህንን ለመቀየር ሀላፊነቱ በአፍሪካውያን ተመራማሪዎች ትከሻ ላይ መውደቁን ዘገባው አመልክቷል።

በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ የተመሰረተው የጉግል ዲጅታል የትርጉም አገልግሎት ቅልጥፍናን በመጨመር ዘርፈ ብዙ ጥቅም እየሰጠ ይገኛሉ።ነገር ግን ዲጅታል መድረኩ ውጤታማ የሚሆነው የተጠቃሚው ቋንቋ በዚህ ዲጅታል መድረክ የሚደገፍ ከሆነ ነው።ከዚህ አንፃር የማሽን ትርጉም ለአንዳንድ የአፍሪቃ ቋንቋዎች አስቸጋሪ ነው።ምስል፦ Valentin Wolf/imageBROKER/picture alliance

መተግበሪያው ለአንድሮይድ ተጠቃሚዎች ቀርቧል

ከአራት ወር በፊት የተሰራው እና ከሁለት ሳምንታት በፊት ለአንድሮይድ ተጠቃሚዎች በሙከራ መልክ የቀረበው ራስ መተግበሪያ፤ የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በሀገር በቀል ቋንቋዎችተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ በሶስት የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አገልግሎት ይሰጣል።እንደ በቃሉ ገለፃ መተግበሪያው ልክ እንደ ቻት ጂፒቲአይነት አገልግሎት የሚሰጥ  እና ለሚጠየቀው ጥያቄ መልስ ለመስጠት መረጃዎችን ማስታወስ የሚችል ነው። ከዚህ በተጨማሪ በመተግበሪያው «ሚኒ አፕ» የሚባል  ታሪኮችን ለመናገር የሚያስችል ተጨማሪ ዲጅታል መድረክም አለው።
ይህ መተግበሪያ በፅሁፍ እና በድምፅ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፤ከአንድሮይድ በተጨማሪ በአይኦኤስ ለማካተት እየሰሩ መሆኑን ገልጿል።ጎግል ላይ የማይገኙ እንደ ንግድ መረጃ ያሉ ሀገር በቀል መረጃዎችን ለማካተት አስበዋል።

በሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረቱ ዲጅታል መድረኮችን በሀገር በቀል ቋንቋዎች መጠቀም ኣ,ስቸጋሪ ነው።ምስል፦ DW

መተግበሪያው ለአጠቃቀም ቀላል ነው

በኢትዮጵያ የአንድሮይድ ተጠቃሚዎች በርካታ በመሆናቸው በአንድሮይድ መጀመሩ አገልግሎቱ ለበርካቶች እንዲደርስ ያግዛል የሚለው በቃሉ፤አጠቃቀሙም ቀላል ሆኖ መሰራቱን ያስረዳል።
ወጣቶቹ  ከአራት ዓመት በፊት «ናይል ስትሪም» የሚባል በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ የሚሰራ ዲጅታል መድረክ  ሰርተው የነበረ ሲሆን፤ በቃሉ እንደሚለው ብዙም ስኬታማ አልነበረም።ነገር ግን  የአሁኑን መተግበሪያ ለመስራት ትልቅ ግብዓት እንደሆናቸው ተናግሯል።እንደ በቃሉ ገለፃ ራስ መተግበሪያን ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አውርደው ተጠቅመውበታል። በዚህም ከተጠቃሚዎች ጥሩ ግብረመልስ መገኘቱን ገልጿል።

ለወደፊቱም አገልግሎቱን የተሻለ ለማድረግ ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን የማካተት  እቅድ እንዳላቸው አመልክቷል።ከአፍሪቃ ቋንቋዎችም ኪሲዋሂሊን በአገልግሎቱ ለማካተት አቅድ ይዘዋል።ሞዴሎችን ለማሰልጠን ቲክቶክን ከመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  መረጃ እንደሚሰበስቡ የገለፀው በቃሉ፤ በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች በቂ እና የተደራጀ እና ትክክለኛ  መረጃ  አለመኖር ግን ተግዳሮት መሆኑን ገልጿል.

የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች በዲጅታል መድረኮች

በሀገር ውስጥ  ቋንቋዎች  ትልልቅ የኤአይ ሞዴሎችን ( LLMs) ማሰልጠን እና የመረጃ ቋቶችን መፍጠር በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መረጃ እንዲያገኙ ያስችላል። እነዚህ ሞዴሎች ተማሪዎች ውስብስብ ትምህርቶችን በሚረዱት ቋንቋ  በተሻለ እንዲማሩ በማድረግ ትምህርትን ለማሻሻል ይችላሉ። በታካሚዎችና በህክምና ባለሙያዎች መካከል የተሻለ ግንኙነትን በማመቻቸትም የጤና አጠባበቅን ማሻሻል ይችላሉ።በመንግስት አስተዳደርም አገልግሎቶችን ለተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ተደራሽ በማድረግ ግልጽነትን እና የዜጎችን ተሳትፎ  ለማጎልበት ያግዛሉ።ስለሆነም እንደ ራስ  ያሉ በሀገር በቀል ቋንቋዎች የተዘጋጁ መተግበሪያዎችም የበኩላቸውን ሊያበረክቱ ይችላሉ።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ፀሐይ ጫኔ
ልደት አበበ 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW