የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስን ስንብት
ዓርብ፣ ሚያዝያ 17 2017
ማስታወቂያ
ላለፉት 12 ዓመታት የሮማን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት አባ ፍራንሲስ በነገው ዕለት ሥርዓተ ቀብራቸው እንደሚፈጸም ይጠበቃል። በ88 ዓመታቸው ክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሣኤ በዓል ባከበሩበት ማግስት (በዕለተ ማዕዶት) ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን የሃይማኖት አባት እስካሁን ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች አስከሬናቸው ከሚገኝበት ስፍራ ድረስ በመሄድ እንደተሰናበቷቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። ነገ ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ,ም በሚፈጸመው ሥርዓተ ቀብራቸው ላይ ለመገኘትም የበርካታ ሃገራት ፕሬዝደንቶችና የአሁን እና የቀድሞ መሪዎች፤ እንዲሁም ንጉሣውያን ቤተሰቦች፤ የሃገራት ተወካዮች፤ የሃይማኖት መሪዎችና ወኪሎች እንደሚገኙ እየተነገረ ነው። በመላው ዓለም ከአንድ ቢሊየን በላይ የሚገመቱ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች እንዳሉ ነው የሚገለጸው። ቀጣዩን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለመምረጥም ከሳምንት በኋላ ካርዲናሎች ዝግ ስብሰባ ያደርጋሉ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስን ለመሰናበት እየተደረገ ያለውን እንዲገልጽልን የረዥም ዘመን የዶቼ ቬለ የሮም ዘጋቢ የነበረውን ተኽለእግዚ ገብረ ኢየሱስን በስልክ በአጭሩ ጠይቄዋለሁ።
ተኽለእግዚ ገብረ ኢየሱስ
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ