1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ርዕደ መሬት በሰሜን ኢትዮጵያ እና በማዕከላዊ ኤርትራ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 3 2015

በዓለም ላይ አብዛኛው አውዳሚ ርዕደ መሬት የሚከሰተው በፓስፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ አካባቢ ነው።ይህ የሆነበት ምክንያትም የመሬት ንጣፍ /ፕሌቶች/ በአብዛኛው የሚንቀሳቀሱት በዚሁ አካባቢ በመሆኑ ነው።ኢትዮጵያም በአፍሪካ እና በአረብ ፕሌቶች አቅጣጫ የምትገኝ ሀገር በመሆኗ፤ በተለይ በሰምጥ ሸለቆ አካባቢ ለርዕደ መሬት ተጋላጭ ነች።

3D-Illustration eines schweren Erdbebens
ምስል Cigdem Simsek/Picture alliance

ርዕደ መሬቱ ደግሞ የመከሰት ዕድል አለው

This browser does not support the audio element.


በሰሜን ኢትዮጵያ እና በማዕከላዊ ኤርትራ በሬክተር ስኬል 5.6  የተመዘገበ ርዕደ መሬት መከሰቱን የጀርመን የሥነ-ምድር ሳይንስ ምርምር ማዕከል  በቅርቡ አስታውቋል። የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት ይህንን ክስተት በተመለከተ ባለሙያ ጋብዟል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ርዕደ መሬት በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ፣በመሬት ንጣፍ ላይ  የአለቶች መውደቅ እና  ከርሰ ምድር ውስጥ በሚፈጠር ፍንዳታ በአነስተኛ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል።በዋናነት  ግን ርዕደ መሬት ከምድር  በታች በሚገኙ አለታማ  ቁሶች ግጭት  የሚፈጠር ተፈጥሯዊ ክስተት ነው። ይህ ግጭት የሚፈጠረው የምድር ንጣፎች ወይም «ቴክቶኒክ ፕሌትስ» በሚሰኙት ጠርዝ ላይ ነው። እነዚህ የምድር  ንጣፎች የተደራረቡ እና ሁልጊዜ በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ  በመሆናቸው  አንዳንዴም ዕርስ በዕርስ  የሚጋጩበት ጊዜ አለ።ይህ ድንተኛ ግጭት የሚፈጥረው ንዝረት እና ሞገድም ምድርን በመሰንጠቅ  ርዕደ መሬት እንደፈጠር ያደርጋል።
በዚህ ሁኔታ ከሰሙኑ በሰሜን ኢትዮጵያ ከተሞች እና በማዕከላዊ ኤርትራ  በሬክተር ስኬል 5.6 የተመዘገበ ርዕደ መሬት መከሰቱን በፖትስዳም ቴሌግራፈንበርግ የሚገኘው  የጀርመን ብሔራዊ የሥነ- ምድር  ሳይንስ ምርምር ማዕከል በቅርቡ አስታውቋል። ያለፈው  ሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም ምሽት ላይ የተከሰተው ይህ ርዕደ መሬት በቀጣዩ ቀን  ንጋት ላይም ከቀደመው ባነሰ መጠን ማለትም 4.8 ሬክተር ስኬል ርዕደ መሬት ተመዝግቧል።በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የርዕደ መሬት ተመራማሪ እና መምህር እንዲሁም የኢትዮጵያ የርዕደ መሬት  መመዝገቢያ መረብ ሀላፊ  ፕሮፌሰር አታላይ አየለ እንደሚገልፁት በሰምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ አንዳንድ አካባቢዎች ለርዕደ መሬት የተጋለጡ በመሆናቸው ክስተቱ የሚጠበቅ ነው።«በተከታታይ የተለያዩ መጠን ያላቸው አሁንም እየተከሰቱ ነው።የተፈጠረበት ቦታ የሚጠበቅ ነው። ምክንያቱም የቀይ ባህር ሰምጥ ሸለቆ፣ የኤደን ባህረ ሰላጤ ሰምጥ ሸለቆ እና የምስራቅ አፍሪቃ ሰምጥ ሸለቆ ሶስቱ አፋር ላይ ይገናኛሉ።እና ከላይ ከምፅዋ አካባቢ ጀምሮ ደጋማው እና ቆላማው ክፍል የሚገናኝበት  በተለያየ ጊዜ እንዲህ አይነት የመሬት መንቀጥቀጥ ይከሰታል።እና የተፈጠረበት ቦታ በእርግጥም የሚጠበቅ ቦታ ነው። ማለት ነው።»በማለት ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል።
 

ፕሮፌሰር አታላይ አየለ፤በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የርዕደ መሬት ተመራማሪ እና መምህርምስል Privat

ርዕደ መሬት አነስተኛ፣  መካከለኛ እና ከፍተኛ በመባል በሶስት ሊከፈል ይችላል።እንደ ፕሮፌሰር አታላይ ሰሞኑን የተከሰተው ርዕደ መሬት መካከለኛ የሚባል ነው።በ10 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ላይ  የተከሰተው ይህ ርዕደ መሬት በኤርትራ  አዲ ቀይህ፣ ደቀማህረ፣ ከረን እና አሥመራ ከተሞች ውስጥ ንዝረቱ መሰማቱን የጀርመኑ የሥነ-ምድር ጥናት  ተቋም አመልክቷል። 
በኢትዮጵያ  የትግራይ ክልል ደግሞ የክልሉን ዋና ከተማ  መቐለን ጨምሮ በሽረ፣ ዓዲግራት፣ አክሱም፣ ዓድዋ እና ሌሎች ከተሞች ተሰምቷል።በንዝረቱ በተለይም ዕቃዎች ሲንቀሳቀሱ እና ሲወድቁ  መመልከታቸውንም አንድ የመቐለ ነዋሪ  ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
የዚህ ርዕደ መሬት ንዝረቱ በተለያዩ አካባቢዎች ቢደርስም የአሜሪካ የሥነ ምድር ጥናት እንዳመለከተው ክስተቱ በዋናነት በኤርትራ የወደብ ከተማ በምጽዋ የተከሰተ ነው።በክስተቱ ከመሬት በታች አንዳንድ ጉዳቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ  ጠቁሟል።ለመሆኑ ክስተቱ ምን ያህል ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው?

«በቅርብ ርቀት ቢፈጠር፤ ለምሳሌ  አሁን ምጽዋ የተፈጠረው አስመራ አጠገብ ቢሆን ወይም አዲስ አበባ ከተማ አጠገብ ቢሆን በህንፃዎች ላይ በጣም ብዙ አደጋ ሊያደርስ የሚችል ነው ።»በማለት ርዕደ መሬቱ የሚያደርሰው አደጋ  ለከተሞች ባለው ርቀት እንደሚወሰን አመልክተዋል።
ርዕደ መሬት ከተፈጥሯዊ በተጨማሪ በሰው ሰራሽ መንገድ በግንባታ፣ በማዕድን ቁፋሮ እና በአቶሚክ ቦንብ ፍንዳታ ሊከሰት ይችላል። እነዚህን ሰውሰራሽ መንስኤዎች መከላከል ቢቻልም በተፈጥሮ የሚከሰትን ርዕደ መሬት ግን መተንበይም ሆነ መከላከል አይቻልም።ነገር ግን ባለሙያው እንደሚሉት የሚያደርሰውን ጉዳት ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ መቀነስ ይቻላል።

ምስል Sunil Sharma/Photoshot/picture alliance

«አሁን በደረስንበት ደረጃ ትንበያ አይቻልም።ግን ምንድነው የሚደረገው ከዚህ በፊት ከተሰበሰበ መረጃ የመሬት መንቀጥቀጥ የት የት አካባቢ እንደሚፈጠር ስለሚታወቅ።በዚያ አካባቢ የሚገነቡ ማንናውም ግንባታ የህንጻ ግንባታ ሊሆን ይችላል። ድልድይ፣ መንገድ ወይም ግድብ ሊሆን ይችላል።የመሬት ንዝረት ቢመጣ ሊቋቋም የሚችል ሆኖ እንዲሰራ ግብዓት ይሆናል መረጃው።» ካሉ በኋላ ሁለተኛው ጥንቃቄ ደግሞ የተጠናከረ የአደጋ ጊዜ  አሰራር  በመዘርጋት የሰው እና የንብረት ውድመትን ማስቀረት እንደሚቻል ጠቁመዋል። 
ባለሙያዎቹ እንደሚሉት የመሬት ውስጣዊ እንቅስቃሴን ከሰዎች ይልቅ እንስሳት ቀድመው የመረዳት ባህሪ ስላላቸው  ርዕደ መሬት ከመከሰቱ በፊት እንግዳ ባህሪ ያሳያሉ።በመሆኑም የእንስሳቱ ያልተለመደ ባህሪ በደንብ መረዳት ከተቻለ ሌላው የቅድመ ጥንቃቄ መንገድ ሊሆን ይችላል።
በዓለም ላይ 81 በመቶው የሚሆነው አብዛኛው አውዳሚ ርዕደ መሬት የሚከሰተው በፓስፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ  አካባቢ ነው።ይህ የሆነበት ምክንያትም የመሬት ንጣፍ /ፕሌቶች/ በአብዛኛው የሚንቀሳቀሱት በዚሁ አካባቢ በመሆኑ ነው።ባለፈው ጥር 29 ቀን 2015 ዓ/ም አውዳሚ  ርዕደ መሬት የተከሰተባቸው ቱርክ እና ሶርያም በዚሁ አካባቢ የሚገኙ ሀገሮች ናቸው።
ባለሙያወቹ እንደሚሉትም በእነዚህ ሀገራት የተፈጠረው ክስተት  የአረቢያን የመሬት ንጣፍ  /ፕሌት/ ወደ ሰሜን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከምስራቅ አናቶሊያ የመሬት ንጣፍ /ፕሌት/ ጋር በመጋጨቱ የተፈጠረ  ነው።

ምስል Science Photo Library/IMAGO

ኢትዮጵያም ርዕደ መሬትን ከሚያስከትሉት ዋና ዋና የመሬት ንጣፎች/ የቴክቶኒክ ፕሌትስ/ መካከል ማለትም  በአፍሪካ እና በአረብ ፕሌቶች አቅጣጫ  የምትገኝ ሀገር በመሆኗ፤ በተለይ በሰምጥ ሸለቆ አካባቢ ለርዕደ መሬት  ተጋላጭ ነች። ያ በመሆኑ  ከሰሜን ኢትዮጵያ በተጨማሪ አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ ፣ ሀዋሳ እና ሌሎች የሰምጥ ሸለቆ የሚያልፍባቸው ረባዳ ቦታዎች  ቀደም ሲል  ርዕደ መሬቶች  ተከሰቶባቸዋል። እስካሁን ከተመዘገቡት ርዕደ መሬቶችም  ከፍተኛው 6.8 ሬክተልስኬል ሲሆን፤ ይህም በምስራቅ ደጋማው ክፍል የተከሰተ እና ንዝረቱ ግን አዲስ አበባ ከተማ የደረሰ ነው። «ከፍተኛ የሚባለው 6.8 ነው።ይህ እንግዲህ በኛ አቆጣጠር በ1896 በአፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት ነው።ነሀሴ ወር ውስጥ ነው የተፈጠረው።ያን ጊዜ አዳሜቱሉ የምትባል ከተማ ናት ተብሎ  ነው በሚሽነሪዎች ሪፖርት የተደረገው። ነገር ግን  መሳሪያው የሚያሳየው ወደ ደቡብ ምስራቅ የኢትዮጵያ ደጋማው ክፍል ማለት ወደ ባሌ ተራሮች የሚያሳይ ነገር አለው።ወቅቱ ረዥም ጊዜ ከመሆኑ የተነሳ አስቸጋሪ ነገር አለው።» በማለት ከገለፁ  በኋላ በ1961 ዓ/ም ሰርዶ የምትባል አፋር ውስጥ የምትገኝ ከተማ በርዕደ መሬት ውድመት እንደደረሰባት አብራርተዋል።ፕሮፌሰሩ አያይዘውም ይህ መሰሉ ክስተት ከብዙ ዓመታት በኋላ ሊደገም እንደሚችልም ተናግረዋል። 
ተመራማሪው እንደሚሉት ከቀይ ባህር ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ኬንያ ድንበር ድረስ በዓመት ቢያንስ አንድ ጊዜ ርዕደ መሬት ይመዘገባል። 
በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል  እና  በኤርትራ የታየው የሰሞኑ ክስተትም የመጀመሪያ አይደለም።በዘንድሮው ዓመት ሐምሌ መጀመሪያ እና ግንቦት አጋማሽ 2015 ዓ.ም. ላይም በእነዚህ አካባቢዎች አነስተኛ ርዕደ መሬት  አጋጥሞ ነበር።
ስለሆነም ተጋላጭነትን አውቆ  መንግስትም ሆነ ተቋማት ትኩረት ሰጥተው መስራት  እንደሚገባ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አታላይ አየለ ያሳስባሉ።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ። 


ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW