ሰላማዊ ዜጎችን ፍዳ ያበላው የኮንጎ ኹከት
ቅዳሜ፣ መጋቢት 23 2015
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በዚሁ ሳምንት ረቡዕ ባወጣው መግለጫው የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ውስጥ በተፋላሚ ኃይላት የሚፈጸመውን ኹከት እና በደል «በጥብቅ» አውግዟል። የምክር ቤቱ መግለጫ፦ «የዘፈቀደ ግድያ፤ መጠነ ሰፊ ወሲባዊ እና ጾታዊ ጥቃቶች፤ እንዲሁም ሕጻናትን በውጊያ በማሳተፍ በከፍተኛ ደረጃ የውትድርና ምልመላን ጨምሮ በሁሉም ታጣቂ ኃይላት አሁንም ድረስ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የፀጥታው ምክር ቤት ያወግዛል » በሚል ይነበባል ። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን የማረጋጋት ተልእኮ (MONUSCO) ኃላፊ ቢንቱ ኬይታ ታጣቂዎች በአጠቃላይ በሚያደርሷቸው ጥቃቶች ኅብረተሰቡ ላይ መከራ ማውረዳቸውን ይናገራሉ ።
«በተለይ በሰሜን ኪቩ የM23 እና ፋርዲሲ (FARDC) ግጭት 900,000 ሰዎች ቤት ንብረታቸው ጥለው እንዲሰደዱ አስገድዷል ።»
ትጥቅ የመፍታትና ሕጻናትን ከውትድርና የማሰናበት ጥሪ
በዚህ ግጭት ከምንም በላይ ተጠቂዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች ናቸው ። እናም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ታጣቂ ቡድኖች ያነገቡትን ነፍጥ አውርደው ያስታጠቋቸውን ሕጻናት ወደየቤታቸው እንዲያሰናብቱ ጥሪ አስተላልፏል ።
በተለይ ጎረቤት ርዋንዳ ድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱት የM23 ንቅናቄ አማጺያን ሰሜን ኪቩ አውራጃ ውስጥ ጥቃታቸውን ከምን ጊዜውም በላይ አጠናክረዋል ። ለንደን በሚገኘው የሶአስ ዩኒቨርሲቲ የጎንጎ እና የታላላቅ ሐይቆች ቀጣና ጉዳይ ባለሞያው ፊል ክላርክ የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ አለመቻሉ አሳሳቢ ነው ብለዋል ።
«የፀጥታው ምክር ቤት ሊቆጣጠራቸውም ሆነ ኃላፊነት እንዲወስዱ ስልታዊ በሆነ መንገድ ሊያሳስባቸው በተደጋጋሚ አልተሳካለትም ። ስለዚህ በስተመጨረሻ ፣ ምንም እንኳን ብዙ ሃገራት በምስራቅ ኮንጎ ሞኑስኮን(MONUSCO) በተመለከተ የተወሰነ ተፅእኖ ቢኖራቸውም፤ ማንኛውም ከባድ የማሻሻያ ሂደት ግን ሞኑስኮ ምሥራቃዊ ኮንጎ ውስጥ እንዲንቀሳቀስ ባዘዘው በራሱ በፀጥታው ምክር ቤት ሊመራ ይገባል ።»
የመካሰስ ጨዋታ
ለሰሜን ኪቩው ኹከትና በደል ኪንሻሳ የሚገኘው የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሞያዎች እንዲሁም በርካታ የምእራባውያን መንግሥታት M23 ታጣቂ ቡድንን ተጠያቂ ያደርጋሉ ። ታጣቂ ቡድኑ በአካባቢው የተትረፈረፈው የተፈጥሮ ሀብት ላይ ዐይኖቹን ከጣለው የጎረቤት ርዋንዳ መንግሥት ጠንካራ ድጋፍ ይደረግለታል ። ኪጋሊ የሚገኘው የርዋንዳ መንግሥት ግን ክሱን ያስተባብላል ። በዚህም አለ በዚያ ግን የኮንጎ መንግሥት ሌሎች ላይ ማሳበቡን ትቶ ኃላፊነት መውሰዱ ላይ ውድቅ ኾኗል ሲሉ የሚተቹት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የርዋንዳ ቋሚ ልዑክ ክላቬር ጋቴት ናቸው ።
«እንዳለመታደል ሆኖ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አመራር ፖለቲካዊም፤ አመራራዊም ሆነ ትግበራዊ ብቃት የላቸውም ። ምንም እንኳን ይህ ግጭት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚያደርሰው ብርቱ መከራ መቀጠሉ ግልፅ ቢሆንም፤ የኮንጎ መንግሥት ግን የሀገር ውስጥ ድጋፍን ለማግኘት እና ከቀጣዩ ምርጫ በፊትም ተቃዋሚዎችን ዝም ለማስባል እንደ ፖለቲካ መሣሪያ እየተጠቀመበት ለመሆኑ ማስረጃ አለ ።»
በሰሜን ኪቩ ቀውስ ጎረቤታሞቹ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና የርዋንዳ መንግሥታት በሚካሰሱበት በዚህ ወቅት የM23 ታጣቂዎች ከአካባቢው እንዲወጡ የሚደረገው ጫና ፍሬ አልባ መሆኑን ክላቬር ጋቴት አክለው ተናግረዋል ። በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ንግግር እና ድርድር ለማድረግ ቢሞከርም ሳይሳካ መቅረቱንም ገልጠዋል ። የሰብአዊ ሁኔታው መባባሱ ግን በከፋ ደረጃ ቀጥሏል ። የሞኑስኮ ኃላፊዋ ኃላፊ ቢንቱ ኬይታም የታጣቂዎች ያልተቋረጠ እንቅስቃሴ በማኅበረሰቡ ላይ የከፋ ቀውስ ማስከተሉን ተናግረዋል ።
«ከM23 ጋር የተጠናከረው ውጊያ እንዲሁም ጥቂቱን ለመጥቀስ እንደ ADF፤ ዛይሬ እና ኮዴኮ (CODECO) ያሉ ቡድኖች ያልተቋረጠ እንቅስቃሴ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በቃላት የማይገለጥ መከራ እንዲቀጥል አድርጓል ። የሰብአዊ ሁኔታውን በማባባስም ጥፋቱ የከፋ እንዲሆን አድርጓል ።»
በዓለማችን እጅግ ከተዘነጉ ግጭቶች ዋነኛው በሆነው የኮንጎ ግጭት ለተከሰተው የሰብአዊ ቀውስ የሚሆን 2,3 ቢሊዮን ዶላር አስፈላጊ መሆኑን ኃላፊዋ ለፀጥታው ምክር ቤት ተናግረዋል ። እየተባባሰ የመጣው የአካባቢው ቀውስ በትምሕርት ላይ ብርቱ ጫናውን አሳርፏል ። ግጭቱ በብርቱ በጎዳቸው የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሁለት አውራጃዎች ብቻ 750,000 ሕጻናት ከትምህርታቸው ተገልለዋል ። እንደ ዓለም አቀፉ ድርጅት መረጃ ከሆነ በሰሜን ኪቩ እና ኢቱሪ አውራጃዎች ብቻ እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ከ2022 እስከ 2023 ባሉት ጊዜያት 2,100 ትምህርት ቤቶች ለመዘጋት ተገደዋል ። ኮንጎን በብዙ አቅጣጫ ያመሳቀለው ግጭት እንዲያከትም ግፊቱ ተጠናክሯል ። ከግፊት የዘለለ ርምጃ ግን ብዙም አይተዋልም ። በእምቅ የተፈጥሮ ሀብቷ አፍሪቃን ለብቻዋ የመቀለብ አቅም ባላት አፍሪቃዊቷ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረው ግጭት እስከወዲያኛው እንዲያከትም በእርግጥ ከልብ ፍላጎቱ ይኖር ይሆን? እጅግ ያጠያይቃል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ/ይሳቅ ሙጋቤ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር