“ሰላምን ማስፈን ለነጻና ገለልተኛ ምርጫ መሰረት ነው” ኦፌኮ
ሰኞ፣ ሐምሌ 14 2017
በ2018 ዓ.ም. እንደሚደረግ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ “በዲሞክራሲያዊ መታደስ ወይም በሀገር መፍረስ” መካከል የሚደረግ ነው ሲል የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) አስጠነቀቀ፡፡
የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አዲስ አበባ ውስጥ ቅዳሜ እና እሁድ ለሁለት ቀናት ያካሄደውን መደበኛ ጉባኤ ትናንት ማምሻውን ሲያጠናቂቅ «መንታ መንገድ ላይ የምትገኝ» በሚል የገለጻት ኢትዮጵያ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንድታካሄድ ነው ያሳሰበው፡፡
ለምርጫው ቅድመ ሁኔታ ሲል የተለያዩ ነጥቦችንም የዘረዘረው ኦፌኮ መንግስት በአገሪቱ ውስጥ ላለው ግጭት ሰላማዊ እልባት እንዲሰጥ ሲል አበክሮ ጠይቋል።
ቅዳሜ በመጀመሪያ ቀን ስብሰባው በውስጥ አቅም ግንባታ ላይ ያተኮረ ስልጠናን ሲያከናውን እንደነበር የገለጸውየኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ በመጨረሻ ቀን ስብሰባው ትናንት “አሳሳቢ” ያለውን ሀገራዊ ሁኔታ መገምገሙን ጠቁሟል፡፡ ኦፌኮ ያለፉትን ሰባት ዓመታት “የባከነ ተስፋ” የታየባቸው እንዲሁም የፖለቲካ፣ የጸጥታና የኢኮኖሚ ቀውሶች ወደ ከፋ አቅጣጫ ያመሩበት ነው ሲል ትችቱን ሰንዝሯል። ኦፌኮ “ውድቀት” ላለው ለዚህ ሁኔታም በሕብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ላይ የተፈጸመ ስልታዊ ያለው ጥቃትና የሰላማዊ የፖለቲካ አማራጮች መዘጋት መንስኤ ተደርጎ የሚወሰድ ብሎታል። በዚሁ በፓርቲው መግለጫ ላይ ተጨማሪ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ “እኛ የጠየቅነው የፖለቲካ ምህዳሩ የመጥበቡ ሁኔታ እና ሰላማዊ ምርጫ በኢትዮጵያ መካሄድ ያለበት ሰላምና መረጋጋት ከተፈጠረ በኋላ ነው” የሚለውን ነው ብለዋል፡፡
ስለቀጣዩ ምርጫ የፓርቲው አቋም
የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ውይይት ዋና ነጥብም በመጪው የ2018 ሀገራዊ ምርጫ ቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ አቋም ለመውሰድ ነው ያለው ኦፌኮ በምርጫው ፍትሃዊነትና ተዓማኒነት የሚረጋገጠው መንግሥት “መሰረታዊ የሆነ ማስተካከያ” ካደረገ ነው ብሏልም፡፡ ፓርቲው ባቀረባቸው ቁልፍ ያሏቸው ቅድመ ሁኔታዎችም፤ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ያለው ጦርነት በአፋጣኝና በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በተረጋገጠ መልኩ እንዲቆም እናሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት እንዲጀመር፤ ሁሉም “የፖለቲካ እስረኞች” ያሏቸው ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣ የፖለቲካ ነጻነቶች በሙሉ እንዲከበር ብሎም የታሸጉ የኦፌኮ ቢሮዎች እንዲከፈቱ እንዲሁም “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሁሉም ፓርቲዎች ሙሉ ስምምነት ላይ ተመስርቶ በአዲስ መልክ እንዲዋቀር” የሚሉ ነጥቦች ይገኙበታል።
ግጭት ማቆም እንደ ፍትሃዊ ምርጫው ቅድመ ሁኔታ
በዚሁ ላይ ማብራሪያ የሰጡት ፕሮፌሰር መረራ፤ “በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ለሚስተዋለው ግጭት ሰላማዊ እልባት እንዲበጅ ጥሪ የቀረበው ለሁሉም ተፋላሚ ቡድኖች ቢሆንም በዋናነት በሃቅ የመደራደሩ ሃላፊነትና አቅሙ ያለው መንግስት በመሆኑ ጥሪው በቀዳሚነት የቀረበው ለመንግግስት ነው” ብለዋል፡፡ “ሰላምና መረጋጋት የመፍጠሩ ጉዳይ በዋናነት የመንግስት ስራ ነው” ያሉት መረራ መንግስትን በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች በተለይም በባሌ፣ አርሲ እና ምዕራብ ኦሮሚያ አከባቢዎች የሚፈጸም ባሉት እስርና እንግልቅ ከአገር የተሰደዱ ፖለቲከኞች እና የትጥቅ ትግል መቀላቀል ምርጫቸው ያደረጉ ስለመኖራቸውም በአስተያየታቸው ጠቃቅሰዋል፡፡ መንግስት ከታጠቁም ሆነ ካልታጠቁ ተፋላሚዎች ጋር ቁጭ ብሎ እንዲመክርም ጠይቀዋል፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት አስፈላጊነት
ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የገለልተኝነት አቋም አስፈላጊነት ጋር በማያያዝ ኦፌኮ ስላነሳው ነጥብም ተጠየቁት ፕሮፌሰር መረራ፤ “እኛ በተደጋጋሚ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ዳኛ መሆን አለበት፤ ከሁሉም ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነጻ ሆኖ ውሳኔ መስጠት ያለበት ገለልተኛ ተቋም መሆን አለበት” በማለት ነጻና ገለልተኛ የምርጫ ተቋም መመስረት አለበት በሚል ከዚህ በፊትም ሆነ አሁንም በፓርቲ ደረጃ እየተከራከሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ኦፌኮ ለቀጣዩ ምርጫ እንደቅድመ ሁኔታ ያስቀመጣቸው ነጥቦቹ ባይሳኩስ ስለሚቀጥለው ምርጫ ተሳትፎ ምን አቅዶ ይሆን የተባሉት ፕሮፌሰር መረራ፤ “መርጫው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት፣ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እና ብሎም ዘላቂ ልማትን ካላረጋገጠምርጫው የተሳካ ነው አይባልም” ሲሉ ይህ እስኪሆን ተመሳሳይ ትግል እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡
በዚሁ መግለጫው ከኦሮሞና የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር እንደሚተባበር የገለጸው ኦፌኮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በመንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳድርም ነው የጠየቀው። ኦፌኮ ለሰላማዊ ትግል ቁርጠኛ መሆኑንም ገልጾ፣ ለዲሞክራሲ ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ዋነኛው ኃላፊነት በገዥው ፓርቲ ላይ የሚወድቅ ነው ብሏል፡፡
መንግስት በፊናው በተለያዩ መድረኮች በአገሪቱ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ እና ፍተሃዊና ነጻ ምርጫ በማድረግ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች የህዝብ ይሁኝታ ካገኙ ስልጣኑን አሳልፎ ለመስጠት እንደማያቅማማ ደጋግሞ ስያስተጋባ ተደምጧል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
አዜብ ታደሰ