ሰላም እንዴት ይምጣ?
እሑድ፣ ታኅሣሥ 6 2017
በኦሮሚያ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሃይሎችና በአካባቢው ነፍጥ አንግበው በሚንቀሳቀሱ መንግስት ኦነግ ሸኔ ብሎ ከሚጠራቸውና እራሳቸውን ኦነግ ኦነሰ ማለትም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፤ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ ከሚጠሩት ሃይሎች መካከል በሚካሄዱና እየተካሄዱ ባሉ ጦረነቶች የተፋላሚ ሃይላትን ጨምሮ በርካታ ዜጎች ህይወት ጠፍቷል፤ ቆስለዋል በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደግሞ ተፈናቅሏል። ጦርነቱ እስከአሁን እየቀጠለ ሲሆን በጃል ሰኚ የሚመራ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላት በሰላም ለመታገል ወስነው ከነትጥቃቸው ወደ መንግስት እየገቡ እንደሆነ ዘገባዎች ያመለክታሉ።
በኦሮሚያ ክልል በመንግስት በኩል የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ንጹሃን ዜጎችን ይገድላሉ፣ ያግታሉ፣ ባንክ ይዘርፋሉ የሚሉና ሌሎች ክሶች ይሰነዝራል። በኦነግ ኦነሰ በኩልም ይህን ተግባር በሰራዊቱ እንደማይፈጽም ይልቁንም በራሱ በመንግስት የመከላከያ ሰራዊት የሚፈጸሙ ናቸው በማለት ያስተባብላል።
በቅርቡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጃል ሰኚ ከሚመራው የኦነግ ኦነሰ አመራሮች አደረኩት ባለው ስምምነት መሰረት የታጠቁ የሰራዊቱ አባላት የተሃድሶ ስልጠና ወደሚካሄድባቸው ማዕከላት እየገቡ እንደሆነ እየተገለጸ ይገኛል። በኦሮሚያ ያለውን የሰላም እጦት ለመፍታት በክልሉና በፌደራል መንግስት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎች መተላለፋቸው ይታወቃል። ከኦነግ ኦነሰ ጋርም በታንዛኒያና ዛንዚባር የሰላም ድርድሮች እንደተደረጉ ይታወቃል። ይሁንና በክልሉ አሁንም ጦርነቶችና ግጭቶች እየቀጠሉ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። በኦሮሚያ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዴት ይምጣ? የዛሬ ውይይታችን ርዕስ ነው።
በዛሬው ውይይታችን ከኦነግ ኦነሰ ጋር ከተካሄዱ ድርድሮች የተሳተፉ፣ ከዚህ ቀደም መንግስት ባደረገው ጥሪ መሰረት ወደሰላማዊ ትግል ተመልሰው ድጋሚ በመታሰራቸው ምክንያት አሁን በስደት ላይ የሚገኙና የኦነግ ኦነሰ ወታደራዊ ዕዝ አማካሪ በውይይታችን ተሳታፊዎች ሆነዋል።
በዚህ ውይይት የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን፣ የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ቢሮ 2 የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የክልሉ ፕረዚደንት የጸጥታ አማካሪ እንዲሳተፉ ከአለፈው ሰኞ ጀምሮ ይህ ውይይት ቀረጻ እስከተቀረጸበት ሐሙስ ዕለት ድረስ በተደጋጋሚ ደውለን ስልክ ማንሳት ስላልቻሉ በውይይታችን ማካተት አልቻልንም።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ያዳምጡ፤ ለባለንጀራዎም ያጋሩ።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር