«ሰሚ አጣን» የሚሉት በሃድያ ዞን የሌሞ ወረዳ ነዋሪዎች
ረቡዕ፣ ግንቦት 20 2017
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፤ ሃድያ ዞን፤ ሌሞ ወረዳ በመልካም አስተዳደር እጦት የተነሳ የማኅበራዊ አገልግሎቶች መስጫ ተቋማት መዘጋታቸውን የወረዳው ነዋሪዎች ገለጹ ። ነዋሪዎቹ እንዳሉት፦ የአስተዳደራዊ የመብት ጥያቄ ያነሱ ሰዎችም በዘፈቀደ እየታሠሩ እንደሚገኙ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ። ጉዳዩ አሳስቦናል ያሉ የወረዳው የአገር ሽማግሌዎች እና የኅብረተሰብ ተወካዮች ከዞን እና ከክልሉ መስተዳድር ለጥያቄያቸው ምላሽ ባለመገኘቱ አቤቱታቸውን ለፌዴራል ተቋማት ማስገባታቸውን ጠቅሰዋል ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፤ ሃድያ ዞን፤ የሌሞ ወረዳ ነዋሪዎች በወረዳው ሰፍኗል ባሉት የመልካም አስተዳደር እጦት የተነሳ የዕለት ተዕለት ኑሯቸው አስቸጋሪ እንደሆነባቸው እየተናገሩ ነው ። በወረዳው ከደሞዝ በወቅቱ አለመከፈል ጋር ተያይዞ የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በየጊዜው እንደሚዘጉም ነዋሪዎቹ ጠቅሰዋል ። «በወረዳው ጎሰኝነትና የመሬት ወረራ የተለመዱ ሆነዋል» ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ «በዚህ ሰዓት በርካታ ትምህርት ቤቶች እና ጤና ጣቢያዎች ተዘግተው ነው ያሉት ። ይህ የሆነው ሠራተኛው ደሞዝ አልተከፈለኝም በሚል ወደ ሥራ መግባት ባለመቻሉ ነው ። ችግሩ የመልካም አስተዳደር አለመኖር ነው ። ለምሳሌ አመራሮቹ ለከተማ መስፋፋት በሚል አርሶአደሩን ሳያወያዩና መተማመን ሳይፈጥሩ መሬት አጥረው ይይዛሉ ። እንግዲህ ሕዝቡ ምን አርሶ ይብላ?» በማለት ጠይቀዋል ።
የጠያቂዎቹ እሥር
በወረዳው የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር የሚነቅፉና ለምን ብለው የጠየቁ ነዋሪዎች የተለያዩ ጥቃቶች እንደሚደርስባቸው የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ « ይህ ልክ አይደለም ብሎ የጠየቀ ማሰር፣ ማሳደድ እና ማሸማቀቅ ይደርስበታል ፡፡ አሁን ላይ ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ ከ40 በላይ ሰዎች ታስረው ይገኛሉ ፡፡ ታሳሪዎቹ ለምን እንደታሰሩ ቢጠየቀም አሳሪው አካል በዚህ ምክንያት ነው ብሎ የሚሰጠው መረጃ የለም» ብለዋል ፡፡
የነዋሪዎቹ አቤቱታ እና ምላሹ
ዶቼ ቬለ የነዋሪዎችን ቅሬታ አስመልክቶ የሃድያ ዞን እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተዳደር ኃላፊዎችን ለማነጋገር ጥረት ቢያደርግም ምላሽ የሚሰጠው አካል ግን ሊያገኝ አልቻለም ፡፡ ለቅሬታችን ከዞን እና ከክልሉ አስተዳደር መፍትሄ አላገኘንም የሚሉት የወረዳው ነዋሪዎች በበኩላቸው ከትናንት በስቲያ ሰኞ የአገር ሽማግሌዎችን እና የማህበረሰብ ተወካዮችን ያካተተ ቡድን አዲስ አበባ በመላክ አቤቱታቸውን ለተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ማሰማታቸውን ከቡድኑ አባላት ሁለቱ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡
የነዋሪውን አቤቱታ ለጠቅላይ ሚንስቴር ጽሕፈት ቤት ፣ ለብልፅግና ፓርቲ ፣ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን /ኢሰመኮ/ እና የሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋምን ጨምሮ ለተለያዩ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ማስገባታቸውን የጠቀሱት አባላቱ " በተለይ ከብልፅግና ፓርቲ ወደ ወረዳው ገምጋሚ ቡድን በመላክ አቤቱታቸንን እንደሚያጣራ ተገልጾልናል ፡፡ የተሰጠን ተስፋ ሰጪ ምላሽ መሬት ላይ ሥለመውረድ አለመውረዱ ግን በቀጣይ የምናየው ይሆናል " ብለዋል ፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኘው የሃድያ ዞን የሰራተኞች ደሞዝ ክፍያና የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭትን ጨምሮ የተለያዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንደሚስተዋሉበት በተደጋጋሚ ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ