1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና ሰሜን ሸዋ አዋሳኝ ግጭት

ሐሙስ፣ መጋቢት 19 2016

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ልዩ ዞን እና ሰሜን ሸዋ ዞን አዋሳኝ አካባቢ ለተከታታይ ሁለት ሳምንታት የቀጠለው ግጭት ባለፉት ሁለት ቀናት ጋብ ማለቱን የየዞኖቹ ነዋሪዎች አስታወቁ።

ከሚሴ ከተማ
ከሚሴ ከተማምስል Seyoum Getu/DW

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና ሰሜን ሸዋ አዋሳኝ ግጭት

This browser does not support the audio element.

ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች በኩል የሚቀርቡ ቅሬታዎች

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የጂሌ ዱሙጋ ወረዳ ወሰን ቁርቁር ቀበሌ ነዋሪ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ሲሰጡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአካባቢው በብሔረሰብ አስተዳደር ዞኑ እና ሰሜን ሸዋ ዞን አዋሳኝ አካባቢ የተከሰተው ግጭት ባለፉት ሁለት-ሦስት ቀናት መጠነኛ መረጋጋት ማሳየቱን አስረድተዋል። ለደህንነታቸው ሲባል ስሜ ይቆይ ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ በወረዳው ባልጪ፣ ጥቁሬ፣ ኮላሽ፣ መረረ፣ አላላ፣ በሪሲሳ እና ጉባ ዋጩ በተባሉ ቀበሌያት ግጭቱ ተስፋፍቶ መቆየቱንም ገልጸዋል። በዚህ ሁለት ቀናት ግን የተኩስ ድምጽ እንደማይሰማም ጠቁመው ስጋቱ ግን እንዳለ መቀጠሉንም ተናግረዋል።

«የረመዳን ጾም ከተያዘ ወዲህ ከባድ ችግር ነው ያለው። ዛሬ ግን ምንም የለም። ተኩስ የከፈተብን ከሰሜን ሸዋ ታጥቆ የሚመጣ ፋኖ የሚባል ኃይል ነው። እናፈናቅላችኋለን ነው የሚሉን። ለዚህ ነው በጦርነት ላይ ያለነው። ይህ ጦርነት እየቆመ ብቀጥልም ከጀመረን አምስት ዓመት እያስቆጠረ ነው። በዚህን ወቅት ማኅበረሰቡ ከእጁ ያለውን ተዘርፎ ባዶ እጁን ነው ያለው። በዚህ ወደ አዲስ አበባ መውጫ የለንም። ማኅበረሰባችን ሴት የለ አዛውንት መንገድ ላይ ይገደላል። ጦርነት የከፈቱብን አካላት ከዚህ ተነስታችሁ ወደ ኦሮሚያ ግቡ ነው የሚሉን» ብለዋል።

አስተያየት ሰጪው የዐይን እማኝ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በዚህ ወረዳ ብቻ ብያንስ 20 ሰው መገደሉን ያወሳሉ።

በቅርቡ ግጭት ተስፋፍቶበት ሰንብቷል የተባለበት ይህ የጂሌ ዱሙጋ ወረዳ በክልሉ ከሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ-አጣዬ ከተማ፣ ተሬ፣ ሸዋ ሮቢት እና መርዬ ከተባሉ አካባቢዎች ይዋሰናል። ሌላው የወረዳው ነዋሪም አስተያየታቸውን አከሉ። ከጂሌ ዱሙጋ በተጨማሪ በሃርጡማ ፉርሴ እና ዳዋ ጨፋ ወረዳዎችም ግጭቱ ተስፋፍቶ መሰንበቱን አስረድተዋል። በዚህ በዳዋ ጨፋ ወረዳ በኩል ደግሞ ማጀቴ እና መኮይ የሚባሉ የሰሜን ሸዋ ዞን አከባቢዎች ይዋሰናሉ፡፡

 

በሰሜን ሸዋ ነዋሪዎች በኩል የሚሰጡ አስተያየቶች

በሰሜን ሸዋ ዞን ስር ከምትገኘው ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ አጣዬ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪም እንደ ጂሌ ዱሙጋ አስተያየት ሰጪዎች ሁሉ በዚህ ሁለት ቀናት አንፃራዊ ሰላም ቢኖርም ስጋቱ ግን አላባራም ይላሉ። «ስጋቱ እዳለ ሆኖ አሁን የተኩስ ድምጽ አይሰማም። ግን ከተማዋ ስጋት ውስጥ ናት፡፡ ያም ሆነ ይህ በዚህ ሁለት ሳምንት ውስጥ የሰፋውን ስጋት በመቀልበስ መከላከያ አጣየን አድኗል» ብለዋል የአጣዬ ከተማ አስተያየት ሰጪው። እኚህ አስተያየት ሰጪ በጂሌ ዱሙጋ በኩል ከሚነሱት አስተያየቶች የሚቃረኑት አንዱ ይህን ነው። «ፋኖ በዚያ ሄዶ የሚፈጽመው ጥቃት የለም» ሲሉም አየሁ ያሉትን ሃሳባቸውን ያጋራሉ።

በሸዋ ሮቢት በኩል የቤቶች ቃጠሎን ጨምሮ የንብረት ውድመትም መከሰቱን ገልጸው፤ ያለፉትን ሁለት ሳምንታት አጣዬ ላይ ተከፍቷል ላሉት ጥቃትም የሚከሱት አካል «ወረራ ነው ሚፈጸመው። ምንም አይታወቅም ከተማ ላይ መጥተው ተኩስ ነው የሚከፍቱት። እነዚህን አካላት እነሱ ገበሬ ናቸው ይላሉ። እና ግን ሸነ የተባሉ ታጣቂዎች እንደሆኑ ነው የምናውቀው» ይላሉ። የሆነ ሆኖም በሰሞነኛው ግጭቱ ከሁለቱም ወገን ወደ 80 ሰው ሕይወት ሳይቀጠፍ እንዳልቀረ አስረድተዋል።

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ልዩ ዞን እና ሰሜን ሸዋ ዞን አዋሳኝ አካባቢ ለተከታታይ ሁለት ሳምንታት የቀጠለው ግጭት ባለፉት ሁለት ቀናት ጋብ ማለቱን የየዞኖቹ ነዋሪዎች አስታወቁ።

የጥቃት አድራሾች ማንነት

የጂሌ ዱሙጋው አስተያየት ሰጪም ሃሳባቸውን ስቀጥሉ፤ «ሌት ተቀን እንቅልፍ ሚነሳን ሰልጥኖ በባለሃብቶች የሚዘወር ሠራዊት ነው። በዚህ ዙሪያ ተከበን በፈጣሪ ሃይል ነው ያለነው። ላለመፈናቀል ለህልውናችን ስንታገል ሸነ ይሉናል። በዚህ ቋንቋ ካልሆነ ይህን ያስባለን፤ በዚህ አይደለም ሸነ ታጥቆ ጫካ እንኳ የሚያድር የታጠቀ አካል አናውቅም» ይላሉ። 

ዶቼ ቬለ ለሁለቱም ዞኖች አመራሮች በተለይም ለኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ኃላፊ አቶ አህመድ አሊ እና ለሰሜን ሸዋ ዞን ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሙሉነህ በተደጋጋሚ በስልክ እና ጽሑፍ መልእክቶች ተጨማሪ ማብራሪያ ብጠይቃቸውም ለጊዜው ምላሻቸውን ማግኘት አልተቻለም።

ግጭቱ እንዲረግብ የቀረቡ ጥሪዎች

የኦሮሞነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከሰሞኑ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ «በወሎ ኦሮሞ ላይ የጅምላ ግድያ እየተፈጸመ ነው» ብሏል። ዩናይትድ ስቴትስ ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል ባስተላለፈችው መልእክት በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ልዩ ዞን እና በሰሜን ሸዋ ዞን አዋሳኞች አከባቢ የሚሰሙ የግድያ፣ ጉዳት እና መፈናቀሎች ያሳስቡኛል ብላለች። ዜጎችን ከቄዬያቸው የሚያፈናቅል ሊኖር አይገባም ያለችው አሜሪካ፤ ውስብስብ የፖለቲካ እና ደህንነት ጉዳዮቹ በውይይት እንዲፈታና ለሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ እንዲደረግ ጠይቃለች።

አስተያየት ሰጪ የአከባቢው ማኅበረሰቦቹ በፊናቸው ለዘለቄታዊው መፍትሄ «ሁላችንም እርስ በርሳችን ተከባብረን ያለውን ጥያቄ በሕጋዊ መንገድ መፍታት ነው። በዚህ ላይ መንግሥት አበክሮ ሊሠራ ይገባል» ይላሉ።   

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW