1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡግና ወረዳ ከ79 ሺህ በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ይሻሉ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 14 2017

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በተከሰተዉ ድርቅና የምግብ እጥረት ምክንያት 79 ,418 ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተባለ። በወረዳው ከ 10 ሺህ በላይ እናቶችና ሕፃናት በከፋተኛ የምግብ እጥረት ምክንያት ጉዳት እንደደረሰባቸዉ የወረዳዉ ጤና ጽሕፈት ቤት ከዚህ ቀደም አሳውቋል።

ሰሜን ወሎ መልክአ ምድር
የሰሜን ወሎ አካባቢ መልክአ ምድር በከፊል ፎቶ ከማኅደርምስል S.Getu/DW

በሰሜን ወሎ ዞን አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የሚሹ ወገኖች

This browser does not support the audio element.

በአሁኑ ጊዜ በወረዳዉ በሚገኙ 16 ቀበሌዎች ከችግሩ ጋር በተያያዘ የሞቱ ሕጻናት ቁጥር አምስት መድረሱን በአካባቢው ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች በሚመራው አስተባባሪ ኮሚቴ ዉስጥ አባል የሆኑት አቶ ፀጋው ታደሰ ይናገራሉ።

የቡግና ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ዓለሙ በበኩላቸዉ በዓለም የምግብ መርሃግብር WFP እና በዩኒሴፍ በኩል የመድኃኒት እና አልሚ ምግብ ለእናቶችና ሕጻናት እየደረሰ ነዉ ብለዋል። በተለይም አካባቢው በተደጋጋሚ በድርቅ የተጎዳ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እየተደረገ ያለዉ ድጋፍ በቂ አይደለም የሚሉት አንድ የአካባቢው ኗሪ በመንግሥት በኩል የሚደረገው ድጋፍ የዘገየ ነው ይላሉ።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽንዲያቆን ተስፋው ባንታብል ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ የኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ለ110 ሽህ ተጠቃሚዎች የምግብ እህል ማጓጓዝ ተጀምሯል ብለው ነበር። ይሁን እንጁ የቡግና ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢምረዉ ሙሌ በመንግሥት በኩል ይደርሳችኋል ከተባለው የምግብ ድጋፍ ውስጥ እስካሁን የደረሰ የለም ነው ያሉት።

አሁን በወረዳው ከተፈጠረው ድርቅና የምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ 79,418 ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸዉ ቢሆንም በመንግሥት በኩል እየመጣ ነው የተባለው 4000 ኩንታል እህል ግን በቂ አይደለም ሲሉ ነው የቡግና ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢምረዉ ሙሌ የሚናገሩት።

ኢሳያስ ገላው

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW