1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሰሞኑን ጥምረት የመሠረቱ ክልላዊ ፓርቲዎች ግንባር እስከመመሥረት እንደሚጓዙ ገለፁ

ሰለሞን ሙጬ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 20 2017

ጥምረቱ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በክልላዊ ፓርቲዎች ላይ ተከትሏል ያለው "አግላይ አካሄድ" ለመመስረቱ መነሻ እንደሆነው ከዚህ በፊት አስታውቋል።ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ግን ይህን አቋም "ተገቢነት የሌለው" በማለት---- ወቀሳዉን ውድቅ አድርጓል።

የጋራ ጥምረት የመሠረቱት የ11 ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች።ጥምረቱ በአንድ የምርጫ ምልክት እንደሚወዳደርና ወደፊት ወደ ግንባርነት ለማደግ ዕቅድ እንዳለዉ መሪዎቹ አስታዉቀዋል።
የጋራ ጥምረት የመሠረቱት የ11 ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች።ጥምረቱ በአንድ የምርጫ ምልክት እንደሚወዳደርና ወደፊት ወደ ግንባርነት ለማደግ ዕቅድ እንዳለዉ መሪዎቹ አስታዉቀዋል።ምስል፦ Solomon Muchie/DW

ሰሞኑን ጥምረት የመሠረቱ ክልላዊ ፓርቲዎች ግንባር እስከመመሥረት እንደሚጓዙ ገለፁ

This browser does not support the audio element.

በቅርቡ "ሰላም ጥምረት" በሚል ስያሜ የተሰባሰቡ 11 ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሂደት ግንባር ለመፍጠር ውጥን መያዛቸውን አስታወቁ።

በአንድ የምርጫ ምልክት መወዳደር ከጥምረቱ ዓላማዎች አንዱ መሆኑን ያስታወቀው ጥምረቱ "ትልቁ ነጥብ" የሀገሪቱን የፖለቲካ ባህል ማዘመን ነው ብሏል። ይህም "የሀሳብ ፖለቲካ" ማራመድ መሆኑን ገልጿል።

ጥምረቱ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በክልላዊ ፓርቲዎች ላይ ተከትሏል ያለው "አግላይ አካሄድ" ለመመስረቱ መነሻ እንደሆነው ከዚህ በፊት አስታውቋል።በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጠው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይህን አቋም "ተገቢነት የሌለው" በማለት ፓርቲዎቹ ማህበራዊ መሠረታችን ነው ከሚሏቸው ክልሎች አልፈው በፌዴራል ደረጃ በነበረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይም ተሳትፈዋል ሲል የቀረበበትን ወቀሳ ውድቅ አድርጓል።

ባለፈው ረቡዕ እና ሀሙስ የመስራች ጉባኤውን ያደረገው ይህ የ11 ፓርቲዎች ጥምረት የስብሰባውን ቃለ-ጉባኤ እና ሌሎች አስፈላጊ ያላቸውን ሰነዶች ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቅርቦ ስያሜውን ለማስፀደቅ በሂደት ላይ መሆኑን አስታውቋል።

ቦርዱ የምስክር ወረቀት ከሰጣቸው የጥምረቱን አላማዎች ወደ መፈፀም እንደሚገቡ የጥምረቱ አስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ዳሮት ጉምአ ዛሬ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

"ጥምረቱ የምርጫ ዓላማ ከሚለው የበለጠ ሰፋ እና ጠለቅ ያሉ ዓላማዎች አሉት። እነዚህን ዓላማዎች ማሳካት የምንችልበትን ስልታዊ ዕቅድ ነው የምናወጣው መጀመርያ።" 

ፓርቲዎቹ ይህንን ጥምረት ለመመስረትሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለፈው ዓመት ከፓርቲዎች ጋር ባደረጋቸው ውይይቶች በክልላዊ ፓርቲዎች ላይ "አግላይ አካሄድ" ተከትሏል የሚለው መሆኑን ጠቅሶ ነበር። በዚህ ላይ ምላሽ የሰጡት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥበቡ ታደሰ ይህ ተገቢ ያልሆነ ምልከታ ነው ብለዋል።

"ለመሰባሰባቸው በምክክር ሂደቱ ላይ ቀደም ሲል የነበራቸው ተሳትፎ ላይ ክፍተቶች ስለነበሩ ነው የሚለው ሀሳብ ተገቢ ነው የሚል እምነት የለንም።"

አቶ ዳሮት ጉምአ እንደሚሉት ግን ፓርቲዎቹ በወቅቱ መገለል ደርሶባቸው ነበር።

አቶ ዳሮት ጉምአ።የጋራ ጥምረት የመሠረቱት የ11ዱ ክልላዊ ፓርቲዎች ጥምረት ጊዚያዊ አስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ የነበሩ። ምስል፦ Solomon Muchie/DW

"በወቅቱ አግልላችሁናል፣ እያገለላችሁን ነው፣ በዚህ አይነት ሊኬድ አይገባም በምክክር ሂደቱ ሙሉ ተሳትፎ ሊኖረን ይገባል የሚል ጥያቄ አቅርበን በዚያ ሁኔታ መድረኮች እንደተፈጠሩ እነሱም እኛም የምናውቃቸው ናቸው።"

የፓርቲዎች መሰባሰብ በበጎ የሚታይና የሚበረታታ ነው ያሉት አቶ ጥበቡ በበኩላቸው የዚህ ፍላጎት መነሻው  ፓርታዎቹ ክልላዊ እና በቦታ የተወሰነ እንቅስቃሴ ይዘው ሳለ እንደ ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች መታየት መፈለጋቸው ነው።

ጥምረቱ በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ በአንድ ምልክት እና ኀልዮት ለመወዳደር፣ "ሥልጣንንም ለመጋራት የሚችል ኃይል የመሆን" ውጥን መያዙንም ገልጿል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ


 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW