1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዛሬ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ቀን ነው

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 1 2017

በጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በየዓመቱ ታኅሣሥ 10 ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን ይታሰባል።የተባበሩት መንግሥታት እንዲህ ያሉት ቀናት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የሚሆኑ የጋራ እሴቶችን እና መርሆዎችን በማቋቋም፣ በማወቅ እና በማክበር በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚደርሱ ጥሰቶች፣ ግጭቶች እና ጥቃቶች ከመከሰታቸው በፊት ለማስወገድ ይረዳሉ ብሏል።

ጄኔቭ የተመድ
የተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን መድረክ በጄኔቫ ፎቶ ከማኅደርምስል FABRICE COFFRINI/AFP/Getty Images

ዛሬ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ቀን ነው

This browser does not support the audio element.

ለሰብዓዊ መብቶች መከበርም እና መጣስ ግለሰቦችም ሆነ መንግሥታት የራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው የሚገልፁ አንድ በዘርፉ ላይ የሚሠሩ ባለሙያ በዚህ ላይ የበለጠው ድርሻ የመንግሥት መሆኑን አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኪሚሽን መንግሥት የሽግግር ፍትሕን ለመተግበር የያዘውን ጥረት በበጎ ገልፆ፤ ሆኖም አሁንም ለከባባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት የሆኑ ግጭቶችን በሰላማዊ ሁኔታ እና በዘላቂነት መፍታት የሚቻልበት ዕድል እንዲኖር ድርድሮች እንዲቀጥሉ ጠይቋል።

የሰብዓዊ መብቶች ቀን ጭብጥ 

ዛሬ በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር ታኅሣሥ 10 ቀን የሚታሰበው የሰብአዊ መብቶች ቀን የተሰየመው በዚሁ ዘመን በ 1948 የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ሁለንተናዊ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ ያፀደቀበትን ቀን ለማሰብ ነው። የዘንድሮው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ዘመቻ የሚያተኩረው ሰብዓዊ መብቶች ለነገ የሚተው ሳይሆኑ ዛሬውኑ እንዲጠበቁ እና ከለላ እንዲያገኙ የሚያስፈልግ መሆኑ የሚገለጽበት ነው።

ሰዎች የሰብዓዊ መብቶችን አስፈላጊነት እና አግባብነት እንዲገነዘቡ ማነሳሳት፣ አሉታዊ እና የተሳሳቱ አመለካከቶችን በመቃወም አመለካከቶችን እንዲቀይሩ እና ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት እንቅስቃሴዎችን ለማነቃቃት እርምጃዎችን ለማንቀሳቀስ ተስፋ መጣል የዓመቱ የዕለቱ ግብ ነው። ይህንን መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያን አሁናዊ የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታ የጠየቅናቸው ኢትዮጵያዊ ተነሳሽነት ለሰብዓዊ መብቶች የተባለው ሀገር በቀል የሲቪክ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ሰለሞን፤ «በአሁን ሰዓት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ሁኔታ ያስፈራል። ሌላው ቀርቶ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ የማትችልበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው»። ይላሉ።

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አርማፎቶ ከማኅደር ምስል Solomon Muchie/DW

በጉዳዩ ላይ የኢሰመኮ የሥራ ኃላፊ አስተያየት 

«ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፈው ዓመት ሁሉን አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ 75 ኛው ዓመት ሲከበር መንግሥታት ለሰብዓዊ መብት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደገና ተመልክተው ግልፀው ነበር» ያሉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ራኬብ መሰለ የኢትዮጵያ መንግሥትም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ቁርጠኝነቱን ገልጾ እንደነበር አስታውሰዋል።

መንግሥት ቃል ገብቷቸው ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ የሽግግር ፍትሕ ሰብዓዊ መብቶችን ባማከለ መልኩ እንዲተገበር ቃል መግባቱ፣ ከባባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይም ተጠያቂነትን አሰፍናለሁ ብሎ እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ ራኬብ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው መጽደቁን እና የፍትሕ ሚኒስቴር ልዩ ችሎት ለማቋቋም መግለፁን በዐወንታ ጠቅሰዋል።

ሆኖም አሉ፤ «አሁንም በግጭቶች ውስጥ ያሉ አካባቢዎች አሉ። ግጭቶች አሉ ማለት ደግሞ ከባድ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸው ይቀጥላል ማለት ነው»። 

ኢትዮጵያዊ ተነሳሽነት ለሰብዓዊ መብቶች የተባለው ሀገር በቀል የሲቪክ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ሰለሞን ወቅታዊውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ አስፈሪ ነው ሲሉ ያንን ሁኔታ ምን አመጣው ስንል ጠይቀናቸዋል።

«ምን አመጣው? ከመንግሥት ባሕሪ ነው የሚመነጨው። ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ዴሜክራሲንና ሰብዓዊ መብቶችን ያከብራል ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ መንግሥት ደግሞ ሰብዓዊ መብቶችን አያከብርም»።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ራኬብ መሰለ ብሔራዊ ምክክሮች እንደ ሀገር ሰላማዊ ሂደቶችን ለማምጣት መሠረት የሚጥሉ ማድረግ እና አካታችነትን መጠበቅም እንደሚገባ ጠቅሰዋል። የሲቪክ ድርጅቶች ተሳትፎ ወደጎን መባል እንደሌለበትም አመልክተዋል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት ከአንቀጽ 14 እስከ 44 ድረስ ዋና ዋና የሰብዓዊ እና የዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን አካትቶ ይዟል። ሆኖም ግን አተገባበራቸው ላይ ብዙ ዐሉታዊ ጥያቄዎች ይነሱበታል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW