ኢትዮጵያ ዉስጥ ሰብአዊ መብት የሚጥሱ ዓለም አቀፍ ክስ እንዲቀርብባቸው ተጠየቀ
ረቡዕ፣ ጥቅምት 28 2016በኢትዮጵያ የሰብእዊ መብት ጥሰት ይፈጽማሉ ባሏቸው ባለሥልጣናትና ግለሰቦች ላይ ዓለም አቀፍ ክስ እንዲቀርብባቸው በአሜሪካ የሚገኙ ሲቪክ ድርጅቶች ጠየቁ። የአሜሪካ ሲቪል ካውንስልና ሌሎች አስር ድርጅቶች፣ በጋራ በመሆን በጉዳዩ ላይ ከአሜሪካ ምክር ቤትና ሴኔት ተወካዮች ጋር በመምከር፣ ባለሥልጣናትና ግለሰቦች ተጠያቂ የሚያደርገው «ማግኔቲስኪ» የተባለው ሕግ ተግባራዊ እንዲሆን መጠየቃቸውን የካውንስሉ ሊቀመንበር ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ ለዶይቸ ቨለ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያን አሜሪካን ሲቪክ ካውንስልና ሌሎች አስር ድርጅቶች ሰሞኑን ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በጠሩት ስብሰባ፣ ጥሪ ለተደረገላቸው ዓለም አቀፍ አካላትና ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ገለጻ አድርገዋል። በዚህ ውይይት ላይ የአሜሪካ ሕግ አውጪ ምክር ቤትና የሴኔት ወኪሎች እንደተሳተፉበት ዲያቆን ዮሴፍ ተናግረዋል። ድርጅቶቹ በጋራ ባሰሙት ድምፅ፣ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይፈጽማሉ ያሏቸው ባለሥልጣናትና ግለሰቦች በዓለም መድረክ ይጠየቁ ዘንድ «ማግኔቴስኪ» የተባለው ሕግ ተግባራዊ እንዲሆን መጠየቃቸውን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
ይህን ጥሪ ተከትሎም፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የዘር ጭፍጨፋና የሰብዓዊ መብት የዘር ጭፍጨፋና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙ ባለሥልጣናትና ግለሰቦችን ለመክሰስ፣ ጥሪ ከተደረገላቸው የሕግ ባለሙያ ማኀበራት አንዱ የዓለም አቀፍ ጠበቃ በፈቃደኝነት ከካውንስሉ ጋር እንደሚሠራ መግለጹን ዲያቆን ዮሴፍ አመልክተዋል። የአሜሪካ ሲቪክ ካውንስልና ሌሎች አስር ድርጅቶች፣ በጋራ በመሆን እነማን መከሰስ እንዳለባቸው ጥናት አድርገው በቅርቡ ያቀርባሉም ተብሏል። ዲያቆን ዮሴፍ እንዳሉት፣የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወደ የት እያመራ እንደሆነ ከዓለም ዓቀፍ ተወካዮቹ ጋር በተካሄደው ውይይት ላይ፣ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት አሁን ላሉት ችግሮች እንደ ዋነኛ መንስኤነት ተነስቶ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።
«ከመሠረቱ የተበላሸ፣ ከሕገ መንግሥቱ የተበላሸ ነው። አወቃቀሩ የተበላሸ ነው። የዘር ፌዴሬሽን የሚባል በዓለም ውስጥ የሌለ ሙከራ ነው። ከእዛ ውስጥ የሚወጡ መሪዎች ሁሉ ከጥፋት፣ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ከጦርነት ከግድያ፣ ማናቸውም አይድኑም፣ እኛም አንድንምና ከመሠረቱ የሚቀየርበትን ይህንን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አጋር ሆናችሁ የሚወገድበትን ነገር እንድትረዱን እንጠይቃለን የሚል ነው።» ነው ያሉት።
«ግሎባል አሊያንስ ፎር ዘ ራይት ኦፍ ኢትዮጵያንስ» የተባለውን የሲቪክ ድርጅት በመወከል በውይይቱ ላይ ንግግር ካደረጉት መኻከል ዶክተር አክሎግ ቢራራ በበኩላቸው በሰጡን አስተያየት፣ ምክክሩ ከፍተኛ የሆነ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
አክለውም ሲቪክ ድርጅቶቹ በቀጣይም የኢትዮጵያን አንገብጋቢ አጀንዳዎች በማንሳት፣ ውይይቶችን የማካሄድ ውጥን እንዳላቸው፣ ዶክተር አክሎግ ጠቁመዋል። «ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የልማት መንገድ ምንድን ነው? ምን ዓይነት ስትራቴጂ ያስፈልጋታል? ፍኖተ ካርታው ምን ይሆናል የሚለው ላይ ሌላ ሰፊ ውይይት ማድረግ እንፈልጋለን።» ነው ያሉት። በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ሲቪክ ድርጅቶቹ ባደረጉት ውይይት ዙሪያ፣ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
ታሪኩ ኃይሉ
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ