የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በኢትዮጵያ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 1 2016የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄዱ የሚገኙ የትጥቅ ግጭቶች ዘላቂ እና ሰላማዊ መፍትሔ እንዲበጅላቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በድጋሚ ጠየቀ።
ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶች መፍትሔ እንዲያገኙ ድጋሚ ጥሪ ያቀረበው 75ኛው ዓመት የአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ቀንን ተንተርሶ ባወጣው መግለጫ ነው።
ኢትዮጵያ የዚህ ድንጋጌ አንጋፋ ፈራሚ ብትሆንም ዛሬ ድረስ ከባድ የሚባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚፈፀሙባት ፣ የአጥፊዎች ተጠያቂነት የማይታይባት ሀገር መሆኗን በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ላይ የሚሰሩ ሀገር በቀል እና አለም አቀፍ ድርጅቶች በሚያወጧቸው የምርመራ ዘገባዎች ተደጋግሞ ተጠቅሷል።
በሀገሪቱ ጦርነትን እና የትጥቅ ግጭትን መነሻ ያደረጉ ፣ የሲቪክ እና የፖለቲካ እንዲሁም ሀሳብን በነፃነት መግለጽን የተመለከቱ ምህዳሮች እየጠበቡ መምጣታቸው ለአስከፊ የመብት ጥሰቶች መበራከት እና ያንን ለሚታገሉት የዘፈቀደ እሥር ተጋላጭነት ምክንያት ስለመሆናቸው ያነጋገርናቸው ዘርፉ ላይ የሚሰሩ ሰዎች ገልፀዋል።
ለመሆኑ ኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ የት ምን ላይ ነች ?
ኢትዮጵያ በግጭት ማቆም ስምምነት ከተገታ አውዳሚ ጦርነት ማግስት የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ያስደነገገ ፣ ለሌላ እየተካሄደ ለሚገኝ የትጥቅ ግጭቶች ተዳርጋለች።
እነዚህ ችግሮች ዘላቂ እና ሰላማዊ መፍትሔ እንዲበጅላቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጠይቋል። ለመሆኑ ኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ አሁን የት ላይ ነች ? የሚለው አሁንም ምላሽ የሚሻ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል። የኢሰመኮ ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለን ይህንን ጥያቄ አቅርበንላቸዋል። "ቀውስ ውስጥ ይገኛል" ሲሉ መልሰዋል።
ኮሚሽኑ በግጭትና ድህረ-ግጭት ወቅት የተጎዱ ዜጎች መብዛት ፣ መፈናቀል፣ ረሃብ እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ አሳሳቢ ሆነው መቀጠላቸውንም ገልጿል።
ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች - በኢትዮጵያ የተባለ ሀገር በቀል የሲቪክ ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መብርሂ ብርሃነ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በተጨባጭ በኢትዮጵያ የሚገኝበትን እውነታ እንዲገልፁ ከጠየቅናቸው መካከል አንዱ ናቸው። "መብቶችን በማስከበር ረገድ ቸልታ" መኖሩን ተናግረዋል።
የመብትተሟጋቾች እሥር አሳሳቢነት
ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭትን መነሻ ያደረጉየመብት ጥሰቶች፣ የሲቪክ እና የፖለቲካ ምህዳር፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ ምህዳር እየጠበበ መምጣቱን ተከትሎ አስከፊ የመብት ጥሰቶች ከመከሰታቸው ባለፈ ለመብት መከበር የሚታገሉትን ሰዎች ለዘፈቀደ እሥር መዳረግ በአሳሳቢ ደረጃ መቀጠሉን
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያ ገልፀዋል። በዚህ ረገድ ሞጋች ፀሐፊያን ፣ እውነትን ተናጋሪ ሰዎች እና በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚሰሩ 50 ሰዎች በዚህ ዓመት ብቻ ስለመታሰራቸው ተናግረዋል።
በሕይወት የመኖር እና በቂ የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብቶች ላይ ያተኮረው የኢሰመኮ ሦስተኛው ዓመት የሰብዓዊ መብቶችን በኪነ ጥበብ ለማስተማር የሚያዘጋጀው የፊልም ፊስቲባል ዛሬ ለአሸናፊዎች እውቅና እና ሽልማት በመስጠት ተጠናቋል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ