1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

ሰው ሰራሽ አስተውሎት የመጭው ዘመን ፈተና

ረቡዕ፣ ጥር 8 2016

የሰው ሰራሽ አስተውሎት በተለያዩ ዘርፎች ምርታማነትን ማሳደግ፣ጊዜን እና ወጭን መቆጠብ፣አስቸጋሪ እና ውስብስብ የሆኑ ስራዎችን መከወን እንዲሁም የስራ ጫናን መቀነስ ከሚጫወታቸው አወንታዊ ሚናዎች ጥቂቶቹ ናቸው።ይሁን እንጅ ከጠቀሜታው ጎን ለጎን የዚህ ቴክኖሎጅ አብዮት በርካታ ተግዳሮቶችንም ደቅኗል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር ተግዳሮቶችም አሉት።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር ተግዳሮቶችም አሉት።ምስል Knut Niehus/picture alliance

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ተግዳሮቶች

This browser does not support the audio element.



ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በአሁኑ ወቅት የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት ህይወት በአወንታዊም ይሁን በአሉታዊ  መልኩ እየለወጠ ነው።
በተለይ የሰዎችን ጥያቄ በሰከንዶች የሚመልሱ እንደ ቻትጂፒቲ ያሉ የዚህ ቴክኖሎጅ ውጤቶች ከመጡ ወዲህ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሰው ልጆች የወደፊት ህይወት ያለው ተፅዕኖ አነጋጋሪ  እየሆነ መጥቷል።
 ይህ ቴክኖሎጂ የህብረተሰብን ገጽታ ፣የግል ሕይወትን ፣ የንግድ እንቅስቃሴን፣ የፀጥታ ሁኔታን ፣ የትምህርት፣የህክምና እና  የመረጃ  ስርጭት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው።  
የአዲስ ወይ/AddiS Way/ የቴክኖሎጅ ሶሉሽን  መስራች እና የሰውሰራሽ አስተውሎት ባለሙያ የሆኑት አቶ መሀመድኑር ኢብራሂም እንደሚሉት ቴክኖሎጅው የማይዳስሰው ዘርፍ የለም። 

የሰው ሰራሽ አስተውሎት በተለያዩ ዘርፎች ምርታማነትን ማሳደግ፣ጊዜን እና ወጭን  መቆጠብ፣አስቸጋሪ እና ውስብስብ የሆኑ ስራዎችን መከወን እንዲሁም የስራ ጫናን መቀነስ ከሚጫወታቸው አወንታዊ ሚናዎች ጥቂቶቹ ናቸው።
እንደ ባለሙያው  ብዙ መሰረተ ልማት ባልተሟላባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ ሀገራት ደግሞ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የተለያዩ ዘርፎችን በመደገፍ ለማህበረሰቡ በርካታ ጠቀሜታዎችን ይሰጣል። 

ይሁን እንጅ ከጠቀሜታው ጎን ለጎን የዚህ ቴክኖሎጅ አብዮት  በርካታ ተግዳሮቶችንም ደቅኗል።
በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ የተመሰረቱ ቴክኖሎጂዎች ምንም እንኳ ምክንያታዊ፣ ሚዛናዊ እና ስሜትን የመረዳት አቅማቸው ከሰው ልጆች ጋር ባይስተካከልም የሚይዙትን መረጃ ግን ከሰው ልጆች በተሻለ መንገድ ይሰንዳሉ።ለዚህም እንደ ቻትቦት እና ቻትጂፒቲ ያሉትን መጥቀስ ይቻላል።በተለይ ቻትጂፒቲ የተባለው ቴክኖሎጂ ከጠቅላላ ዕውቀት አኳያ ሲታይ ከሰው ልጆች የበለጠ ነው። የመረጃ ፍለጋን ያቀለለው ቻትጂፒቲ

እንደ ቻትጂፒቲ ያሉ የዚህ ቴክኖሎጅ ውጤቶች ከመጡ ወዲህ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሰው ልጆች የወደፊት ህይወት ያለው ተፅዕኖ አነጋጋሪ እየሆነ መጥቷልምስል Andreas Franke/picture alliance

ማሽንን የማስተማር እና የማሰልጠኑ ሂደት /ማሽን ለርኒንግ/ አመክንዮን እና ምክንያትን አካቶ በተሻለ እና በረቀቀ መንገድ ከተሰጠ ደግሞ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጅ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የሰው ልጅን  በልጦ መገኘቱ አይቀሬ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ያም ሆኖ እነዚህ ቴክኖሎጅዎች  በውስብስብነታቸው እና በሰዎች ቁጥጥር እጦት ምክንያት ያልተጠበቁ ባህሪያትን ሊያሳዩ ወይም ያልተጠበቁ ውጤቶችን ሊወስኑ ይችላሉ። ይህ ያልተጠበቀ ሁኔታ በግለሰቦች፣በንግድ ተቋማት ወይም በአጠቃላይ  በማህበረሰብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ውጤቶችን ሊያስከትል ይችላል።
የሰው ሰራሽ ቴክኖሎጅ ውጤቶች ሰዎችን ተክተው በመስራትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰሰዎችን  ከስራ ገበታ እንዲፈናቀሉ፣ሊያደርጉ ይችላሉ  የሚል ስጋትም አሳድሯል። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት/IMF/ በቅርቡ ባወጣው መረጃም 40% የሚሆነው የዓለም ህዝብ ለወደፊቱ በዚህ ቴክኖሎጂ ስራውን ሊያጣ ይችላል ሲል ይህንኑ ስጋት  የሚያጠናክር ትንበያ አስቀምጧል።አቶ መሀመድኑር ስጋቱ ትክክለኛ ስጋት ነው ይላሉ።

በሌላ በኩል በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚፈጠሩ ይዘቶች በተለይ እንደ /Deep Fake/ ጥልቅ ሀሰተኛ  ያሉ  ድምጽ በማስመሰል፣ የቪዲዮ ምስሎችን በመፍጠር  እውነት ያልሆነ  መረጃ እንዲስፋፋ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።በዚህም በእውነት እና በሀሰት መካከል ያለው ልዩነት እንዲደበዝዝ  ያደርጋሉ።ጉዳዩን ከኢትዮጵያ አንፃር የተመለከቱት አቶ መሀመድኑር በማህበረሰቡ ዘንድ ብዙ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ያስረዳሉ። .

ይህ ቴክኖሎጅ በዓለማችን የሚታዩ የኢፍትሃዊነት እና የአድሏዊነት ችግሮችንም የበለጠ እንዲጨምሩ ሊያደርግ ይችላል። .
የኢፍትሃዊነት እና አድሎአዊነት የሚከሰተው በተዛባ የስልጠና መረጃ ወይም በስለተቀመር ንድፍ ምክንያት በመሆኑ፤አድልዎ ለመቀነስ እና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ ከአድልዎ የራቁ ስልተ ቀመሮችን እና የተለያዩ የሥልጠና መረጃዎችን ማዘጋጀት ወሳኝ መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል።

እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ብዙ ጊዜ የግል መረጃዎችን በመሰብሰብ እና በመመርመር ስራቸውን የሚያከናውኑ በመሆናቸው፤ከዚህ አንፃር ከውሂብ ግላዊነት እና ደህንነት ጋር የተያያዙ ችግሮችም ይነሳሉምስል Klaus Ohlenschläger/picture alliance

መረጃዎች እንደሚያሳዩት እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ብዙ ጊዜ የግል መረጃዎችን በመሰብሰብ እና በመመርመር ስራቸውን የሚያከናውኑ በመሆናቸው፤ከዚህ አንፃር ከውሂብ ግላዊነት እና ደህንነት ጋር የተያያዙ ችግሮችም ይነሳሉ።ይህንን ስጋት ለማቃለል ባለሙያዎቹ የሚመክሩት ጥብቅ የውሂብ ጥበቃ ደንቦችን እና ደህንነቱ የተጠበቀ የውሂብ አያያዝ ልምዶችን ማዳበርን ነው። የማሽን ትርጉም በአማርኛ ቋንቋ ለምን አስቸጋሪ ሆነ ?

በሌላ በኩል እንደ ሰው አልቫ አውሮፕላን/ድሮን/ ያሉ የጦር መሳሪያዎችም ይህንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም መንግስታት እና ሌሎች ተዋናዮች  የጭካኔ ተግባራትን   እንዲፈጽሙ በማድረግ አደጋን ያባብሳሉ።ምክንያቱም ሰዎችን ተክተው የሚሰሩት እነዚህ ማሽኖች ከተሰጣቸው መረጃ ውጭ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የሰዎች ቁጥጥር፣ ማገናዘብ እና ርህራሄ ይጎድላቸዋልና። 
ከዚህ በተጨማሪ የመረጃ አጠቃቀም የግልፅነት ችግር፣ የሰው ልጆችን የፈጠራ ስራ ማቀጨጭ፣ የተጠያቂነት እና የአእምሮአዊ ንብረት መብቶችን መጣስ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የሚነሱ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ባለሙያው ይገልፃሉ። 
በአጠቃላይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እድገት  ከሚሰጠው በርካታ ጥቅሞች ባሻገር ለሰው ልጆች የረጅም ጊዜ ስጋትን ደቅኗል። ይህም ከሰው ልጆች እሴት ወይም ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ነገሮች ጋር  ባለመጣጣም ያልተፈለገ እና አስከፊ ውጤት ሊያስከትል ይችላል።
በዚህ የተነሳ ፖለቲከኞች እና አንዳንድ የቴክኖሎጂ ተቋማት መሪዎች የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የሕግ ማዕቀፍ ሊኖረው ይገባል በሚል ግፊት እያደረጉ ነው።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በአሁኑ ወቅት የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት ህይወት በአወንታዊም ይሁን በአሉታዊ መልኩ እየለወጠ ነው።ምስል DW

ቴክኖሎጂው ያሳሰባቸው እንደ ፣አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ቻይና ያሉ ሀገራት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍን የሚቆጣጠር ሕግ ለማውጣት እየተዘጋጁ ነው።የአውሮፓ ህብረት በጎርጎሪያኑ ሰኔ 2023 ዓ/ም ሕግ ለማውጣት የሚያስችል ሰነድ አጽድቋል።
አቶ መሀመድ ኑር ኢትዮጵያ በቴክኖሎጅው መጠቀሟ ብዙ ችግሮችን እንደሚፈታላት ገልፀው፤ ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ለማስቀረት ግን ከወዲሁ ፖሊስ መንደፍ ጠቃሚ መሆኑን ያስረዳሉ።የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ ዕድል እና ፈተና
በሰው ሠራሽ አስተውሎት ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ የዘርፉ ተመራማሪዎችም በደህንት ጥበቃ ምርምር ላይ በንቃት መሳተፍ፣ በስነምግባር መመሪያዎች ላይ መተባበር እና በቴክኖሎጂው እድገት ውስጥ ግልፅነትን ማበረታት አለባቸው። ለማሽን ስልጠና በሚሰጡ መረጃዎች ላይ ጠንካራ ፍተሻ፣ ግምገማ እና የክትትል ሂደቶችን በማድረግ  ለሰው ልጆች ጥቅም መቆማቸውን እና በህልውና ላይ ስጋት እንደማይፈጥሩ ማረጋገጥ ደግሞ ከሁሉም በላይ አስፈላጊ ነው።
በመንግስታት እና በተቋማት በኩል በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ አዳዲስ የህግ ማዕቀፎችን ፣ ደንቦችን  እና ፖሊሲዎችን ማዘጋጀት ወሳኝ ነው። ያካልሆነ ግን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር ያልተፈለገ እና አስከፊ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያውች እያስጠነቀቁ ነው።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW