1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ኪነ ጥበብኢትዮጵያ

"በመጨረሻም ያለን ትውስታችን ብቻ ነው፤ እሱን ካልያዝን ማንን? “ሰዓሊ ብርሃኑ

አዲያም ታደለ አባዲ/ Adiam Tadele Abadi
ማክሰኞ፣ የካቲት 18 2017

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የኪነጥበብ መድረክ ላይ ብቅ ያለው ወጣት ኢትዮጵያዊው ብርሃኑ ማናዬ በአስተሳሰብ ቀስቃሽ እና ረቂቅ ስራዎቹ ዓለምአቀፍ ትኩረትን እያገኘ ነው። በቅርቡ በጀርመን ሀገር ኮለኝ ከተማ ዓውደ-ርዕዩን ያቀርባል።

Äthiopien 2025 | Künstler Birhanu Manaje
ምስል፦ Privat

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የኪነጥበብ መድረክ ላይ ብቅ ያለው ወጣት ኢትዮጵያዊው ብርሃኑ ማናዬ በአስተሳሰብ ቀስቃሽ እና ረቂቅ ስራዎቹ ዓለምአቀፍ ትኩረትን እያገኘ ነው።

 ከኢትዮጵያ ባሻገር፣ ሮማኒያ፣ ቱርክ እና አሜሪካ በሚገኙ ኤግዚቢሽኖች (ዓውደ- ርዕዮች) ላይ በመሳተፍ በዓለምአቀፍ ደረጃ ስራዎቹን አሳይቷል።ለአርቲስት ብርሃኑ እያንዳንዱ የብሩሽ ምት ስለ ባህል፣ ጽናትና ታሪክ ይናገራል።

ለብርሃኑ ጥበብ ከአገላለጽ በላይ ነው።  በዙሪያው ያለውን ዓለም መመርመርያ እና ጥያቄ መጠየቅያ ዘዴ ነው ።በኢትዮጵያ በፈጣን ሁኔታ የከተሞች መስፋፋት፣ የባህል ቅርሶች መደምሰስ ስጋት ባለበት ሁኔታ ይህ ኢትዮጵያዊ አርቲስት በእደ ጥበቡ ትውስታን እና ማንነትን ለመጠበቅ እየተጠቀመበት ይገኛል።

ሰዓሊ ብርሃኑ ማናዬ ምስል፦ Privat

ትዝታን ለጥበብ

"የእኔን ፈጠራ የሚያነሳሳው በዕለት ተዕለት ሕይወቴ ውስጥ በማያቸው እና የማዘወትራቸዉ ነገሮች ላይ በማሰላሰል ነው" ይሏል ብርሃኑ። “ዓይናችንን በቀላሉ በዙሪያችን ላለው ኣካባቢ ከከፈትን ኢትዮጵያ ማለቂያ የሌለው መነሳሻ ትሰጣለች" ሲልም ይናገራል። ለብርሃኑ ትዝታ ቋሚ አካል አይደለም። ይልቁንስ ቀጣይነት ያለዉ እና ሁልጊዜ የሚደጋገም ነው። የእሱ ጥበባዊ ሂደት፣ የግል ትውስታዎች ከጋራ ታሪክ ጋር እንዴት እንደሚጣመሩ በመመርመር ላይ የተመሠረተ ነው። "ትውስታ ሁላችንም በውስጣችን የምንይዘው ነገር ነው፣ነገር ግን ከግላዊ ስሜት በላይ ትልቅ ነው"ሲል ያስረዳል። "በጊዜ ሂደት ከባህላችን እና ከታሪካችን ጋር ያገናኘናል"። ሲልም ያክላል።

ሃገራዊነት በኪነጥበብ መነፅር

ብርሃኑ በትዝታ እና ሃገራዊ ማንነት መካከል ያለውን ግንኙነትም ይመለከታል። ጥበቡን የኢትዮጵያን ባህላዊ ቅርሶችን መጠበቅያ ዘዴ አድርጎም ያምናል። "የአንድን ሀገር ማንነት በብዙ መንገዶች መግለፅ ቢቻልም በጋራ እና የግል ልምዶቻችን ላይ የተመሠረተ ነው" ይላል። የታወቁ የኢትዮጵያን ባህል የሚገልፁ፣ ቁሳቁሶችን እና ምስሎችን በመጠቀም የኢትዮጵያን ባህል መዝግቦ መጠበቅ ይፈልጋል።

ያለፈውን ሁኔታ በማስታወስ እና ዘመናዊነትን በመቀበል መካከል ያለው ትግል በአዲስ አበባ በብዛት ይታያል። ከተማዋ በፍጥነት እየተቀየረች ነው፣ የጥንት ሰፈሮች በአዲስ ህንፃዎች እየተተኩ ይገኛሉ። ታድያ ለብርሃኑ ይህ ለውጥ ደስታንም ሀዘንንም ይፈጥራል። "የቀድሞዋ አዲስ አበባ ለአርቲስቶች ፈጠራ ልዩ መነሳሻ ቦታ ነበረች" የሚለው ብርሃኑ  ምንም እንኳን እነዚህ ታሪካዊ ቦታዎች አሁን ቢለወጡም «ሥነ ጥበብ ትውስታን የማቆየት ኃይል አለው"  ሲልም ገልጿል።

ሰዓሊ ብርሃኑ ማናዬ የጥበብ ስራዎቹን በጎይተ ኢኒስቲቲውት አዲስ አበባ አሳይቷልምስል፦ Privat

ብርሃኑ በጀርመን ሀገር ኮለኝ ከተማ በቅርብ ጊዜ ዓውደ-ርዕዩን ያቀርባል።  ለመጀመሪያ ጊዜ ጨርቃ ጨርቅን በሥነ ጥበብ ስራው ተጠቅሞ ባህላዊ ታሪክን መግለፅ ይፈልጋል። "እያንዳንዱ ጨርቅ የራሱ የሆነ ትረካ አለው እና አንድ ላይ በመስፋት አዲስ ነገር በጥበብ እገልጻለሁ" ሲል ያብራራል።

 " በቅርብ ጊዜ ስራዎቼ ያተኮሩት ትዝታ እና  መፈናቀል ላይ ነው " የሚለው ብርሃኑ። የኢትዮጵያን የበለጸጉ ቅርሶች ለማስታወስ እንደ ጀበና እና መሶብ ያሉ ባህላዊ ቁሶችን በስነ ጥበቡ አካቷል።

ብርሃኑ ጨርቃ ጨርቅን ተጠቅሞ የሰራው የሥነ ጥበብ ስራምስል፦ Privat

ለኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ተግዳሮቶች እና እድሎች

«የዘመኑ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ዓለምአቀፍ እውቅና በማግኘት ረገድ ትልቅ እንቅፋት እየገጠማቸው ይገኛል ። » የሚለው ብርሃኑ ዘመናዊ የኢትዮጵያ ጥበብ የሚታዩባቸው ጋለሪዎች  ጥቂት ናቸው የሚል እምነት አለው። እሱ እንደሚለው ይህም ባለሙያዎቹ ተገናኝተው በስራቸው ላይ ሀሳብ የመለዋወጥ እድላቸውን ይገድባል። "ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች አስደናቂ ጥበብን መፍጠር ይችላሉ። ነገር ግን ትክክለኛ ድጋፍ ካልተደረገላቸው አቅማቸው ታይነትን ያጣል" ይላል።

ብርሃኑ የኢትዮጵያን የበለጸጉ ቅርሶች ለማስታወስ እንደ ጀበና፣ መሶብ እና የመሳሰሉ ባህላዊ ቁሶችን በስነ ጥበቡ ይጠቀማልምስል፦ Privat

መፍትሔው ምንድን ነው?

 ይህንን ክፍተት ለመቅረፍ በኢትዮጵያ ውስጥ ተጨማሪ የጥበብ ተቋማት እንዲኖሩ እና ከዓለምአቀፍ የጥበብ አውታሮች ጋር ጠንካራ ትብብር እንዲኖር ብርሃኑ የመፍትሔ ሀሳብ ይሰነዝራል።  የበለፀገ የኪነጥበብ ማህበረሰብን ለማፍራት የመንግሥት ድጋፍ፣ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት እና ዓለምአቀፍ አጋርነት ወሳኝ ናቸው ብሎም ያምናል።

የሰዓሊ ብርሃኑ ማናዬ የጥበብ ስራዎች በጎይተ ኢኒስቲቲውት አዲስ አበባምስል፦ Privat

ብርሃኑ ማናዬ  ሰዎች አዳዲስ ለውጦችን እየተቀበሉ ታሪክን ስለመጠበቅ እንዲያስቡ በጥበብ ስራው ይጋብዛል። ስራው የኢትዮጵያን ያለፈ ታሪክ ያከብራል እናም መጪው ትውልድ ታሪኩን እንዲያስታውስ እና እንዲቀጥል ያበረታታል።  ጥበብ ታሪክ እና ትዝታዎችን ከአንድ ትውልድ ወደ  ሌላኛው ትውልድ ማስተላለፊያ እንዲሁም ባህልን እና ማንነትን የማቆያ መንገድ እንደሆነ ግልፅ ነው።

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW