1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሱሉልታ፦ በኦነግ-ኦነሰ አዲስ ጥቃት ያጠላው ስጋት

ሥዩም ጌቱ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 2 2017

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሱሉልታ ወረዳ ከጫንጮ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቅርብ ርቀት ላይ የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ለገሰ ሥዩምን ጨምሮ ሶሦት የፀጥታ አባላት በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አማጺያን ተገድለዋል።

 Äthiopien Addis Ababa | Landschaft Oromia Region
ምስል Seyoum Getu/DW

የሱሉልታ ወረዳ ፖሊስ አዛዥን ጨምሮ ሶሦት የፀጥታ አባላት በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መገደል

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሱሉልታ ወረዳ ከጫንጮ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቅርብ ርቀት ላይ የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ለገሰ ሥዩምን ጨምሮ ሶሦት የፀጥታ አባላት በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አማጺያን ተገድለዋል። ከፖሊስ አዛዡ በተጨማሪ የወረዳው የብልፅግና ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ሲሳይ በሻዳ በጥቃቱ ቢቆስሉም ሕይወታቸው ተርፎ ጫንጮ ሆስፒታል በህክምና ላይ መሆናቸውን ዶቼ ቬለ ከምንጮች አረጋግጧል፡፡ ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የፈጸሙት ወደ ሰላም ለመመለስ በሚል  ለባለሥልጣናቱ አቀባበል አድርጉልን ብለው ከተቀጣጠሩ በኋላ ነው ተብሏል፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በፊናው የጥቃቱን መፈጸም አምኖ ርምጃው የተወሰደው ግን ባለሥልጣናቱ ታጣቂዎቹን ለማስፈታት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ነው ብሏል። 

የአደጋው አፈጻጸም

ጥቃቱ ከተፈጸመበት ረቡዕ ገበያ ከተባለ ስፍራ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአከባቢው የዐይን እማኞች መንግስት ሸነ ሲል የሚጠራውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) ያለው አማጺ ቡድን ጥቃቱን የፈጸመው ትናንት ታኅሣሥ 1 ቀን፣ 2017 ዓ.ም. እኩለ ቀን 5 ሰዓት ግድም ነው ብለዋል። በሰሜን ሸዋ ዞን ስር በምትተዳደረው ሱሉልታ ወረዳ ጫንጮ ከተማ ወደ ደርባ ሲሚንቶ እና ሙሎ ወረዳ በሚወስድ አቅጣጫ “በሰላም ልንገባ ነው” ያሉትን ታጣቂዎች ለመቀበል በጸጥታ አካላት ታጅበው ስጓዙ የነበሩት የአከባቢው የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ ታጣቂዎቹን ለመቀበል ስጓዙ ነበር የተባሉት ላይ ጥቃቱ የተፈጸመውም ከከተማዋ ብዙም ሳይርቁ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡ 

ደንገተኛው የተኩስ እሩምታ

“ያው በትናንትናው እለት የመንግስት አካላት እና በጫካ ያሉ ታጣቂዎች በስልክ ተደዋውለው አቀባበል አድርጉልን ካሉ በኋላ ድንገት የተኩስ እሩምታ እንደከፈቱባቸው ነው እኛ የሰማነው” ያሉት ጥቃቱ ከተፈጸመበት ስፍራ ቅርብ ርቀት ላይ ከምትገኘው ሮብ ገቢያ ከተባለ ስፍራ አስተያየታቸውን ሰጡን የአከባቢው ነዋሪ፤ “የመንግስት አካላት ከፓርቲ ጽህፈት ቤት፣ ከጸጥታ ጽ/ቤት እና ከነዋሪዎች ጋር ሆነው አቀባበል ለማድረግ ስጓዙም ነበር” ብለዋል፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው በግምት ቀን አምስት ሰዓት አከባቢ ይሆናል ያሉት አስተያየት ሰጪው ታጣቂዎቹ የመንግስት አካላቱ ላይ ድንገት ነው ተኩስ ከፈቱት ብለዋል፡፡ “እኛ አጠገቡ ደርሰን ባንቆጥርም ሶስት አራት ሰው ህይወቱ አልፏል ነው የተባለው፡፡ የአከባቢው የፓርቲ ኃላፊው እስካሁን ሆስፒታል በመልካም ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ሰምተናል” ነው ያሉት፡፡

አስተያየት ሰጪው ቀጥለው እንዳብራሩትም፤ “ያው ታጣቂዎቹ የመንግስት አካላትን የጠሩዋቸው አቀባበል አድርጉልን ወደ ሰላም ልንመለስ ነው በማለት እንደጠሯቸው ከጥቃቱ በኋላ እናም ሰምተናል፡፡ ድንገት ነው በሙሎና ደርባ መገንጠያ አስፓልት ላይ ተኩስ ከፈቱባቸው፡፡ በእርግጥ የመንግስት አካላቱ እንዲህ ይደርስብናል ብለው ስላልጠበቁት እንጂ በጸጥታ አካላት ታጅበው ነበር፡፡ ግን ያልጠበቁት ነው የገጠማቸው” ብለዋል፡፡

ኦሮሚያ ክልል፤ መልክዓ-ምድር በከፊል። ፎቶ ከምስል ማኅደርምስል Seyoum Getu/DW

ዶቼ ቬለ ስለጉዳዩ ተጨማሪ መረጃዎችን ለመጠየቅ ለአከባቢው ባለስልጣናት በተለይም ለወረዳው አስተዳዳሪ አቶ አበበ ወርቁ፣ ለወረዳው ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አሸናፊ እና ለዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ከፍያለው አደሬ ደጋግመው ብደውልም ባለስልጣናቱ አስቸኳይ ያሉት ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ገለጸው አስተያየታቸውን አላጋሩንም፡፡

የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት  ድርጊቱን መፈጸማቸውን አረጋግጠው አስተያየታቸው ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የኦነግ-ኦነሰ አዛዥ አማካሪ ጅሬኛ ጉደታ፤ “ስለጉዳዩ ሪፖርቶች ደርሰውናል እውነት ነው” ያሉት አቶ ጅሬኛ “ታጣቂዎቻቸው ኑና ውሰዱን ማለታቸውን አላረጋገጥንም” ብሉም ታጣቂዎቻቸው ወታደራዊ ጥቃቱን ወሰዱት ለማስፈታት በተንቀሳቀሱ የጸጥታ ኃይሎች ላይ ነው ብለዋል፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመው “በተነሳው ፍልሚያ ነው” ያሉት የኦነግ-ኦነሰ ባለስልጣኑ፤ በሰራዊታቸው ላይ የደረሰ ጉዳት መኖሩን አልገለጹም፡፡ “በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በኩል የተዘገበ ጉዳት የለም፡፡ ግን በነሱ በኩል የአከባቢው ፖሊስ አዛዥን ጨምሮ የጸጥታ አካላት ስገደሉ የብልጽግና ፓርቲ አመራር ላይ ጉዳት መድረሱን አረጋግጠናል” ነው ያሉት፡፡

የትናንቱ የአማጺያን ጥቃት የተሰማው መንግስት ከሰሞኑ ከታጣቂዎች ጋር ተደርሷ ባለው የሰላም ስምምነት መሰረት በርካታ ታጣቂዎች እስከነሙሉ ትጥቃቸው እየተመለሱ ነው ባለበት ወቅት ነው፡፡ አስተያየት ሰጪው የአከባቢው ነዋሪ እንዳሉት ግን በዚህ በሰሜን ሸዋ በኩል ታጣቂዎቹ ስገቡ ግን እምብዛም አልታየም፡፡ “ያው ባለፈው ሳምንት በሰማነው መረጃ የተወሰኑ የታጠቁ አካላት ከኩዩና ኤጄሬ መጡ የተባሉ እየተኮሱ በዚህ በጫንጮ ማለፋቸውን ሰምተናል፡፡ ግን ሌሎች አከባቢዎች እንደተመለከትነው በገፍ የገባ ኃይል በዚህ የለም” ብለዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW