ሱዳን ዉስጥ ጎርፍ 10 ሰዎች ገደለ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 30 2012
ማስታወቂያ
ሱዳን ዉስጥ በያዝነዉ ሳምንት በጣለዉ ከባድ ዝናብ ምክንያት በደረሰ ጎርፍ ቢያንስ 10 ሰዎች ሞቱ ከ 3, 300 በላይ መኖርያ ቤቶች ደግሞ ፈረሱ። በፈረንሳዩ የዜና ወኪል አዣንስ ፋራንስ ፕሬስ ዘገባ መሰረት ወደ 1, 800 የሚሆኑ መኖርያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ወደ 1500 የሚሆኑት መኖርያ ቤቶች ግን የወደሙት በከፊል ነዉ። በዚሁ አደገኛ ጎርፍ 21 ትምህርት ቤቶች እና ስምንት መሳጂዶች ሙሉ በሙሉ በጎርፉ ታጥበዉ ተወስደዋል። የመንግሥታቱ ድርጅት ትናንት ይፋ እንዳደረገዉ ወደ 50 ሺህ የሚሆኑ በጎርፍ የተጎዱ ነዋሪዎች የአስቸኳይ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል። በሱዳን ከሰኔ ወር እስከ ጥቅምት ወር ድረስ ከባድ ዝናብ የሚታይበት ወቅት ሲሆን በዚህ ወቅት በሱዳን ለተደጋጋሚ ጊዜያቶች የአጎርፍ አደጋ እንደሚደርስ ተዘግቦአል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ ቅጽበታዊ ጎርፍ የሚያስከትል ከፍተኛ ዝናብ ስለሚጥል አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜትርዎሎጂ ኤጄንሲ አስጠንቅቆአል። ኤጄንሲው እንዳለው በሃገሪቱ በተከታታይ የሚጥለዉ የክረምቱ ዝናብ ድንገተኛ ጎርፍ አስከትሎ ሰው ሕይወት እና ንብረት ሊያጠፋ ይችላል።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ