1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን «ጥቃትና ግፍ እየደረሰባቸዉ ነዉ» ድርጅቶች

ኢሳያስ ገላው
ዓርብ፣ ሚያዝያ 24 2017

ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽና ድምፃቸው እንዲቀየር የጠየቁት እነዚህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፣ በቅርቡ አንደኛው ልጃቸው ትከሻውን በጥይት ተመትቶ እስካሁን ተገቢውን ህክምናም ሆነ ማስታገሻ መድኃኒት ባለማግኘቱ ምክንያት በከፍተኛ ስቃይ ላይ እንደሚገኝ ይናገራሉ።

ራቁባ በተባለዉ የሱዳን አካባቢ ከሰፈሩ የኢትዮጵያ ስደተኞች መካከል በከፊል።በአብዛኛዉ ከትግራይ ክልል የተሰደዱት ሰዎች እስካሁን ወደ ሐገራቸዉ አልተመለሱም
የትግራይ ወይም የሰሜን ኢትዮጵያ የሚባለዉ ጦርነት በተደረገበት ወቅት በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ጦርነቱን ሸሽተዉ ወደ ሱዳን ተሰድደዋል።ምስል፦ Hussein Ery/AFP

ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን «ጥቃትና ግፍ እየደረሰባቸዉ ነዉ» ድርጅቶች

This browser does not support the audio element.

 

የሱዳን መከላከያ ጦር ባልደረቦች በሐገሪቱ ርዕሠ ከተማ ኻርቱም ዉስጥ የሚኖሩ ኢትዮጳዉያን ሥደተኞችን እየደበቡ፣ እያገቱና እያንገላቱ መሆናቸዉን ሥደተኞቹ አስታወቁ።ሥደተኞቹ እንደሚሉት በቅርቡ ርዕሠ-ከተማ ካርቱምን ከጠላቱ ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር የተቆጣጠረዉ የሱዳን መከለከያ ኃይል ባልደረቦች በኢትዮጵያዉኑ  ላይ «የበቀል» የሚመስል በደል እያደረሱ ነዉ።የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር UNHCR ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን ከጥቃት እንዲከላከል ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የኢትዮጵያዉያን-አሜሪካዉያን የመብት ተሟጋች ተቋማት ጠይቀዋል።

ከሁለት ዓመት በላይ በተካሄደው የሱዳን ጦርነት፣ ክፉኛ በወደመችው መዲናዋ ኻርቱም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኛ ቤተሰቦች ናቸው።

በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የተፈጸመው አፈና

ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽና ድምፃቸው እንዲቀየር የጠየቁት እነዚህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፣ በቅርቡ አንደኛው ልጃቸው ትከሻውን በጥይት ተመትቶ እስካሁን ተገቢውን ህክምናም ሆነ ማስታገሻ መድኃኒት ባለማግኘቱ ምክንያት በከፍተኛ ስቃይ ላይ እንደሚገኝ ይናገራሉ።

ይህ ያነሰ ይመስል፣ሰሞኑን ደግሞ የሱዳን ጦር ታጣቂዎች የተጠለሉበት ቤት ውስጥ ዘለቀው ገብተው ሌላኛዋ ሴት ልጃቸዉን ከሌሎች ኢትዮጵያውን ጋር አፍነው ወስደዋቸዋል ሲሉ ገልፀዋል።

"ከዚህ ካለንበት፣ከተጠጋንበት ብቻ ወደ 10 ሰዎች ነው የወሰዷቸው፤ ገብተው ክፍል ፈትሸው ነው የወሰዷቸው ሌሎች ብዙ ሀበሾች በመንገድ ላይ የተገኙትን ወስደዋል እና ስቃይ ላይ ነው ያለነው።"

እነዚህን ኡትዮጵያውያን ስደተኞችን፣የአሜሪካ ኢትዮጵያውያን የህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ አባላት ከወራት በፊት ባደረጉት ጥረት፣ ወደ ደቡብ ሱዳን ለማሻገር የተደረገው ጥረት፣የሱዳን ጦር መዲናዋን ከተቀናቃኙ የፈጥኖ ደራሽ ኅይል ለመንጠቅ በከፈተው ማጥቃት ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱ ተመልክቷል።

«የበቀል ዕርምጃ ይመስላል»

መዲናዋ ኻርቱምን፣በእጃቸው ያስገቡት የሱዳን ጦር ኀይል ታጣቂዎች፣አሁን ኢትዮጵያውያኑ ላይ የበቀል የሚመስል እርምጃ እየወሰዱ እንደሆነም  ስደተኞቹ ይናገራሉ።

"ሁሉ ፉከራቸው ወደ እኛ ላይ ነው፤ የተዋጋናቸው ነው የሚመስላቸው፤በውነት በጣም ነው የተሰቃየነው ሁለት ዓመት ጦርነቱ አልበቃ ብሎ ደግሞ እነሱ መጥተው መከራ ሆነ።"
ሌላ በኻርቱም ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በበኩላቸው፣እየተፈጸመ ያለውን በደል አስመልክተው የሚከተለውን ተናግረዋል።

"ብዙ  ችግር እንደደረሰብን፣እንደተደበደብን በዙ ነገር ደርሶብናል ከአሁን በፊት። አሁን ያለንበትን አካባቢ መንግስት ተቆጣጥሮት ነው ያለው፤ በእዛ ላይ አንዳንድ ህገ ወጥ የሆኑ ወታደሮች እኛ ላይ ይህን ሃገር ለቀን እንድንሄድ፣ ከዚህ በኋላ ሱዳን ውስጥ ቦታ እንደሌለን እያስፈራሩን እየተናገሩ ነው።"

በድርጅቶቹ የቀረበው ጥያቄ

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የሲቪል እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እነዚህን በደቡባዊ ኻርቱም  ለስቃይ የተዳረጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ህይወት ከአደጋ እንዲታደግ፣ለመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጥያቄ አቅርበዋል።

የትግራይ ወይም የሰሜን ኢትዮጵያ በሚባለዉ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ ሸሽተዉ ራቁባ በተባለዉ የሱዳን አካባቢ ከተጠለሉ ስደተኞች መካከል ጥቂቱምስል፦ Ebrahim Hamid/AFP

እነዚሁ ስምንት ድርጅቶች፣ለኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዴ፣ባቀረቡት አቤቱታ፣ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ ከተለያዩ ታጣቂ ኀይሎች በሚሰነዘርባቸው ጥቃት ምክንያት ህይወታቸው ለአደጋ ተጋልጦ ይገኛል ብለዋል።

ጥያቄውን ካቀረቡት እነዚህ ድርጅቶች መኻከል፣ የአሜሪካ ኢትዮጵያ የህዝብ ጉዳዮች ከሜቴ/ኤፓክ/ የቦርድ አባልና ዋና ጸሐፊ አቶ ዮም ፍሰሐ ጉዳዮን በተመለከተ  ተከታዮን አስተያየት ለዶቼ ቬለ ሰጥተዋል።

"እነዚህ ሰዎች ያሉበት ሁኔታ በጣም አደገኛ እየሆነ ሰዎቹ  እየተገደሉ ከቤታቸው መውጣት አይችሉም ብለን ለነሱ ጽፈናል።ይህን በሚመለከት፣ለሱዳን ኤምባሲ እንደዚሁም ደግሞ ኮሚሽኑ ዋና መስሪያ ቤት አለ ለእነሱም ልከናል።"

 ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ ከከተማዋ ኻርቱም ወጥተው፣ የደኅነት ጥበቃና ሰብዓዊ ዕርዳታ ወደሚያገኙበት አካባቢ የሚሄዱበት ሁኔታ ሊመቻችላቸው እንደሚገባ፣ ሁኔታውን  በቅርበት የሚከታተሉት ሌላኛው  የኤፖክ አባል አቶ ደሴ  አዬበል አሳስበዋል።

" የተባበሩት መንግስታትም ይሁን ከተቻለ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትም ቢሆን የሱዳን ኤምባሲም ይህን አውቆ ዜጎች እንደ ስደተኛ መብታቸው ተጠብቆ ወደ አንድ ቦታ እንዲወጡ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ።"

ለጥቃት ከተገለጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኛ ቤተሰቦች  መኻከል ወደ 1000 የሚጠጉት ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውና የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን የመታወቂያ ካርድ የያዙ መሆናቸው ተመልክቷል። ስደተኞቹ በምግብ፣ መድኃኒትና መጠለያ እጦትም እየተሰቃዩ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

ታሪኩ ኃይሉ

ነጋሽ መሐመድ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW