1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ዜጎች ለቀው ሄደው እኛ የሰው ሀገር ተረክበናል፤ መሄጃ የለንም።»

ዓርብ፣ ሐምሌ 12 2016

በሱዳኑ ከባድ ውጊያ፣ በጦር ቀጣና ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውን ስደተኞች ከሀገሪቱ በአስቸኳይ የሚወጡበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ጥሪ አቀረቡ። የስደተኞቹ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ለዶይቸ ቨለ እንደገለጹት፣በሱዳን በሚካሄደው ጦርነት ምክንያት፣ ብዙ ኢትዮጵያውያን የተገደሉ ሲሆን የተቀሩት በረሃብ፣በመድኃኒት እጦትና በጭንቀት ከፍተኛ ስቃይ ላይ ይገኛሉ።

የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት
የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ምስል AFP

«ዜጎች ለቀው ሄደው እኛ የሰው ሀገር ተረክበናል፤ እኛ መሄጃ የለንም።» ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች

This browser does not support the audio element.

በጦርነቱ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን

በስልክ ቃለ ምልልስ ያደረግንላቸው ሱዳን ኻርቱም የሚገኙት የስደተኞቹ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት፣ የሚደርስባቸውን የአጸፌታ ጥቃት በመስጋትና ለደህንነታቸው ሲባል ስምና ድምጻቸው እንዲቀየርላቸው ጠይቀውናል። አቶ አስራት በኩራት፣ በሚል ስም  አስተያየት የሰጡን ስደተኛ እንደሚሉት፣ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች፣ ማለትም የሱዳን ጦርና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በኻርቱምና አካባቢው የሚተኩሷቸው ከባድ መሳሪያዎች በየሰፈሩ እየወደቁ ብዙ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል።
"በጸጥታው ችግር በክርስቲያን መቃብር ወስደን አንቀበራቸውምና፣ የሚሞቱ ሰዎች በተባራሪ ጥይት፣ በአካባቢው በሚገኝ ክፍት ቦታ ነው የምንቀብራቸው፤አሁን እዛ ላይ ባየኸው ቪዲዮ፣ 95  በመቶ ኢትዮጵያውያኖች ናቸው።"የሱዳን ጦርነት መዘዝ ለኢትዮጵያዉያን ስደተኞች

ከዚህ ሃገር የሚያወጣን እንፈልጋለን

አቶ ታዬ መንግሥቱ በበኩላቸው፣እየተባባሰ በመጣው ጦርነት መኻል፣የስደተኞቹ ሕይወት ከባድ አደጋ ላይ መውደቁን ገልጸው፣የሚመለከተው አካል በአስቸኳይ እንዲደርስላቸው ተማጽነዋል።


"በጦርነት መኻል ነው ያለነው፤ከባድ መሳሪያ እየመጣ በአካባቢያችን ይወድቃል።ስንት ወንድሞቻችን በከባድ መሳሪያ አረር ተፈናጥሮ የሚሄደው አረር ነው የገደለን።አሁን ሰሞኑን እንኳን አንድ ወንድማችን ሞቶ በሌሎች ሕብረተሰብ፣ ከማናውቃቸው ሕብረተሰብ ጋር ወስደው ሆስፒታል ቀበሩት።በየቦታው ነው የምንቀብረው እና ብዙ ነገር አለብን።እኛ ከዚህ ሃገር የሚያወጣን እንፈልጋለን።"ከ1300 በላይ የሱዳን ስደተኞች ከመጠለያ ጣቢያ ወጡ
ጦርነቱ ሲጀመር ፣ወጊያው ከበረታባት የሱዳን መዲና ኻርቱም፣ወደሌላ የአገሪቱ ግዛት ለመሄድ የገንዘብ ችግር ስለነበር መሄድ  አልቻልንም ያሉት የስደተኞቹ ተወካዮች፣ገንዘብ ኑሯቸው ከከተማዋ የወጡትም ያሰቡትን ያለማግኘታቸውን አመልክተዋል።
"ከአሁን በፊት፣ ካምፕ ውስጥ ያሉት፣ከኻርቱም የወጡት ሰዎች ከገዳሪፍ ደውለው፣የሰጡን መልስ ምን መሰለህ? እንጉርጉሮ የሚባል የስደተኞች ካምፕ ላይ፣ አማራ እና ኤርትራውያን እንዲሁም ትግሬዎች ለይተው ያስቀምጣሉ። ስለዚህ እንዳትወጡ ነው ያሉን። እኛ ወደ እዛ ተርበንም እንድረስ ብለን ነበር፣ ይህን ስንሰማ አደጋ ስለሆነ ምናልባት ችግር ይደርስብናል ከማለት አንጻር አልቻልንም።" አሁን፣ጦርነቱ ከአንድ ዓመት ከአራት ወር በላይ ባስቆጠረበት ሁኔታ በኻርቱምና አከባቢው የቀሩት ስደተኞች፣ በርሃብ፣ በመድኃኒት እጦትና  በጭንቀት እየተቸገሩ መሆኑን የገለፁት ስደተኞቹ፣ ከችግራቸውም በላይ በታጣቂዎች እየተደበደቡና ንብረታቸው እየተወረስ መሄጃ በማጣት መቀመጣቸውን አስረድተዋል።

ደቡብ ኮርዶፋን የሚገኙ ስደተኞች ምግብ ለመቀበል ተሰልፈውምስል Guy Peterson/AFP

የተባባሰው የከባድ መሣሪያ ድብደባ

"አሁን ስማ አውሮፕላን መጣ ልትደበደብ፣ ከባድ መሳሪያ እየተ ተኮሰ ነው ሰምተህ ከሆነ አሁን? ሁልጊዜ ጦርነት ነው።ሁልጊዜ ይተኮሳል በአካባቢው ፎቆች ሁሉ ፈራርሰዋል ቤት የሚባል፣ ህብረተሰቡ ሁሉም ለቅቆ ወጥቷል።እኛ መኼጃ ስሌለን ነው የተቀመጥነው።ዜጎች ለቀው ኼደው እኛ የሰው ሃገር ተረክበን ተቀምጠናል።

ተፈናቃዮች በሱዳን ዳርፉር ዋና ከተማ ኤል ፋሸር ምግብ ለመቀበል ተሰልፈው ምስል AFP

"በደቡባዊ ኻርቱም፣ከ700 እስከ 800 የሚደርሱ ስደተኞች እንደሚገኙና የሚረዳቸው አካል እንደሚፈልጉ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት በላኩት የአቤቱታ ደብዳቤ አመልክተዋል።የአሜሪካ ኢትዮጵያውያን የህዝብ ጉዳይ ኮሚቴ(ኤፓክም) ስደተኞቹ እርዳታ እንዲያገኙ ለማገዝ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ዮም ፍሰሐ ለዶይቸ ቨለ አስታውቀዋል።የሱዳን ስደተኞች ወደ 3ኛ አገር መሄድ እንደሚፈልጉ ገለፁ
"ለኢትዮጵያ እስከቆምን ድረስ፣ እነዚህ ሰዎች መርዳት አለብን። በተለይም ደግሞ ችግራቸው ታውቆ የሚመለከታቸው ድርጅቶች ዕርዳታ እንዲያደርጉላቸው፣ እንደ ቀይ መስቀል፣ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ እነዚህን የመሳሰሉ ድርጅቶች እነዚህን ሰዎች ባሉበት ሁኔታ፣ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በጦርነት መኻል ነው ያሉት፤ የሚገደለው ህዝብ ግማሹ በተባራሪ ጥይት በድሮን ነው የሚገደለው።"ብለዋል።

ታሪኩ ኃይሉ 
ኂሩትመለሰ 
ታምራት ዲንሳ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW