1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሱዳን፣ የሩሲያ ጥልፍልፍ ስልት ማሳያ፣ የኒዤር ዉዝግብ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 8 2016

ሩሲያ ዩክሬንን በመዉረሯ ምዕራባዉያን መንግስታት በጣሉባት ማዕቀብ ለደከመዉ ኤኮኖሚዋ ወርቁ ጥሩ መደጎሚያ ነዉ።አሁን ግን ሞስኮዎች ከጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ቡድን ጋር ያላቸዉን ግንኙነት ላላ አድርገዉ የመንግሥትነትን ሥልጣን ከተቆጣጠረዉ ከጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን ኃይል ጋር «ፍቅር እንደገና»ን እያንጎራጎሩ ይመስላል።

ወደ አንድ ሺሕ የሚጠጉት የአሜሪካ ወታደሮችና የጦር መሳሪያዎች ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ ከኒዤር እየወጡ ነዉ
ኒዤር የሠፈረዉ የአሜሪካ ጦር ኃይል ባልደረቦች በበረሐማይቱ ሐገር አሰሳ በሚያደርጉበት ወቅትምስል picture-alliance/J. Delay

ሱዳን፣ የሩሲያ ጥልፍልፍ ስልት ማሳያ፣ የኒዤር ዉዝግብ

This browser does not support the audio element.

 

የሱዳን ጦር ኃይል የሚመራዉ የሐገሪቱ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ማሊክ አጋር መንግሥታቸዉ ሥለሚከተለዉ መርሕ እንዴትነት አይጠራጠሩም።አጋር፣ ባለፈዉ ግንቦት ማብቂያ ሳይንት ፒተርስበርግ-ሩሲያ በተደረገዉ የዓለም የምጣኔ ሐብት ጉባኤ ላይ በሚሳተፉበት ወቅት ሱዳን ትሪቡን ለተባለዉ የሐገራቸዉ ጋዜጣ እንደነገሩት ሩሲያ ቀይ ባሕር ጥግ የባሕር ኃይል ሠፈር  እንድትገነባ መንግስታቸዉ ይፈልጋል።

ሩሲያ ፖርት ሱዳን ዉስጥ የባሕር ጦር ሠፈር መመስረት የሚያስችላትን ስምምነት ለመዋዋል  ሁለቱ ሐገራት መደራደር ከጀመሩ ቆይተዋል።የቀድሞዉ የሱዳን ፕሬዝደንት ዑመር ሐሰን አልበሽርና የሩሲያዉ አቻቸዉ ቭላድሚር ፑቲን በ2017 (እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ተስማምተዉ ነበርም።
«አንደርስታንዲግ ዎር» የተሰኘዉ አምደ መረብ እንደዘገበዉ ያኔ በተደረገዉ ስምምነት መሠረት ጦር ሠፈሩ በመቶ የሚቆጠሩ የሩሲያ ወታደሮችና ቢያንስ አራት መርከቦች የሚሠፍሩበት ነዉ።ዉሉን የሱዳን ምክር ቤት ሳያፀድቀዉ ምሥራቅ አፍሪቃዊቱ ሐገር በምጣኔ-ሐብት፣ ፖለቲካና ጦርነት ትመሰቃቀል ገባች።
ሩሲያ ዩክሬን ዉስጥ የሱዳን ጄኔራሎች እርስበርስ ከጦርነት ሲመሰጉ የካርቱምና የሞስኮ ባለሥልጣናት ለ7 ዓመት ያክል የተዘነጋ መዝገባቸዉን አዋራ እያረገፉ ያገላብጡ ያዙ።የሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌትናንት ጄኔራል ያሲር አል አታር ባለፈዉ ግንቦት እንዳሉት ድርድሩ ዳግም ተጀምሯል።«ዉጤታማ» ብለዉታልም ጄኔራሉ-ድርድሩን።
በሱዳኑ ጦርነት የሩሲያ የሥልት ለዉጥ

ሩሲያ ከካርቱም መሪዎች ጋር መደራደር መጀመሯ በሱዳኑ የርስ በርስ ጦርነት ለአንድ ዓመት ያክል ስትከተለዉ የነበረዉን ሥልት ለመቀየሯ ማረጋገጪያ ነዉ።በሱዳን መከላከያ ሠራዊትና በሐገሪቱ ፈጥኖ ደራሽ ጦር መካከል በሚደረገዉ ጦርነት ሩሲያ ቫግነር በተባለዉ የቅጥረኛ ወታደሮች ኩባንያ በኩል የፈጥኖ ደራሹን ጦር ሥታግዝ ነበር።በሩሲያ መንግስት የሚደገፈዉ ቫግነር ለፈጥኖ ደራሹ ጦር ለሚያደርገዉ ርዳታ የሱዳንን ወርቅ ይወስድ ነበር ይባላል።ምዕራባዉያን እንደሚሉት ሩሲያ ዩክሬንን በመዉረሯ ምዕራባዉያን መንግስታት በጣሉባት ማዕቀብ ለደከመዉ ኤኮኖሚዋ ወርቁ ጥሩ መደጎሚያ ነዉ።አሁን ግን ሞስኮዎች ከጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ቡድን ጋር ያላቸዉን ግንኙነት ላላ አድርገዉ የመንግሥትነትን ሥልጣን ከተቆጣጠረዉ ከጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን ኃይል ጋር «ፍቅር እንደገና»ን እያንጎራጎሩ ይመስላል።
ጊጋ በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የጀርመን ዓለም አቀፍ የጥናት ተቋም ባልደረባ ሐገር ዓሊ እንደሚሉት ግን ሞስኮዎች ለጊዜዉም ቢሆን «አንዱን ጥሎ ሌላዉን አንጠልጥሎ» ከሚል  ይልቅ ሁለቱንም የማንጠልጠሉ ሥልት ሳይከተሉ አይቀርም።

«በሱዳኑ ጦርነት አሸናፊና ተሸናፊዉ ከማይለይበት ደረጃ ላይ ደርሷል።አንድ ዓመት በሞላዉ ጦርነት ግልፅ የሆነ ነገር ቢኖር ከተቻለ ከሁለቱም ኃይላት ጋር የሚያስተባብር ሥልት መከተል ጥሩ አማራጭ ነዉ።ይሕ ሥልት ኋላ ወዳንዱ ለማዘንበል ጠቃሚ ነዉ።ሩሲያ አሁንም ማዕቀብ እንደተጣለባት ነዉ።የዩክሬኑ ጦርነትም ተጨማሪ ወጪ ይጠይቃታል።ሥለዚሕ ሁኔታዉ እስኪለይለት ከፈጥኖ ደራሹ ጦር ጋር ያላትን ትብብር ሳትቋርጥ ከመከላከያዉ ሠራዊት ጋር ግንኙነታን የሚያጠናክር መንታ ሥልት መከተል ትመርጣለች።»
የሩሲያ ወታደራዊ ድጋፍ ለሱዳን

የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ከሱዳኑ የጦር ኃይሎች አዛዥና የሐገሪቱ መሪ ከጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን ጋር-ካርቱምምስል Palace Media Office/REUTERS

ሱዳን ለሩሲያ የባሕር ኃይል ሠፈርስትፈቅድ፣ ሩሲያ በምትኩ ለሱዳን ጦር ኃይል የጦር መሳሪያ ድጋፍ ታደርጋለች።«አንደርስታንዲግ ዎር» የተሰኘዉ አምደ መረብ እንደዘገበዉ በአፍሪቃና በመካከለኛዉ ምሥራቅ የሩሲያ ልዩ መልዕክተኛ ሚኻኤል ቦግዳኖቭ መንግስታቸዉ ለሱዳን መከላከያ ኃይል «ዘመናይ ጦር መሳሪያ እንደሚያስታጥቅ» ቃል ገብተዋል።እዚሕ ቦን የሚገኘዉ የፀጥታና የሥልት የቅንጅት ጥናት ተቋም (CASSSIS) መሥራች አንድሬስ ሐይነማን እንደሚሉት የሱዳን መከላከያ ሠራዊት ከዚሕ ቀደም ሩሲያ SU-30ና SU-35 የሚባሉት የጦር ጄቶች እንዲሁም S-400 የተባሉት ሚሳዬሎች እንዲሰጠዉ ጠይቆ ነበር።የፖለቲካ ተንታኝ ሐገር ዓሊም የሱዳኑ ጦርነት በተራዘመ ቁጥር የሐገሪቱ መከላከያ ሠራዊት በተለይም አየር ኃይሉ ከሩሲያ የሚፈልገዉ የጦር መሳሪያ ዓይነትና ብዛት እየጨመረ መምጣቱ አይቀርም ባይ ናቸዉ። 

«የሱዳን ጦር ኃይል የታጠቃቸዉ አብዛኞቹ መሳሪያዎች ሩሲያ ሠራሽ ናቸዉ።መጀመሪያ ከሶቭየት ሕብረት ቀጥሎ ቤሎሩስ፣ዩክሬንን ከመሳሰሉ የቀድሞ የሶቭየት ሕብረት ሪፐብሊኮች የተሸመቱ መሳሪያዎች ናቸዉ።እነዚሕን መሳሪያዎች በቅጡ የሚያዉቀዉ የሱዳን ጦር አሁንም ጦርነቱ እየተራዘመ ሲሔድ የሩሲያ ጦር መሳሪያዎች ለረጅም ጊዜ ያስፈልጉታል።»
ሩሲያ ግን ለሱዳን ጦር ኃይል ጦር መሳሪያ ማስታጠቋ ባይቀርም እስካሁን የጦር ኃይሉን ጥያቄ መቀበል አለመቀበሏም ሆነ የምታስታጥቀዉን መሳሪያ ዓይነት በግልፅ አላሳወቀችም።ሁለቱ ወገኖች ረጅም ጊዜ የተደራደሩ፣ ብዙ የተወራ ምዕራቦችን ያሰጋዉ የጦር ሠፈር ስምምነት ገቢር ከሆነ ግን የአካባቢዉን የኃይል አሰላለፍ ሚዛን መቀየሩ አይቀርም።

የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር አዛዥ ከጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ጋር-ካርቱምምስል Sudan's Presidential Palace/Handout/AA/picture alliance

ሩሲያ ለሶሪያዉ ፕሬዝደንት ለበሽር አል አሰድ መንግሥት ድጋፍ በመስጠትዋ ታርቱስ የሚገኘዉን የቀድሞ የሶቭየት ሕብረት ጦር ሠፈርን መልሳ ተቆጣጥራለች።ከዚያ ጦር ሠፈር ተፅዕኖዋን እስከ ሊቢያ ድረስ ማስፋፋት ችላለች።የሱዳኑን የቀይ ባሕር በር ከተቆጣጠረች ደግሞ የፖለቲካ ተንታኝ አንድሬስ ሐይነማን እንደሚሉት ከሰሐራ በስተደቡብ ለሚገኙ የአፍሪቃ ሐገራት በቀላሉ ጦር መሳሪያ ማቅረብ፣ ከሲዊስ ቦይ እስከ ሕንድ ዉቅያኖስ ባለዉ የዉኃ መስመር ላይ ተፅዕኖ ማሳደርም ትችላለች።

«ሩሲያዎች ቀይ ባሕርን መቆጣጠር፣ ወደ ሕንድ ዉቅያኖስ በቀላሉ መሸጋገር የሚችሉበትን ጦር ሠፈር መመሥረት ይሻሉ።ከና ወደ ስዊስ ቦይ የሚታለፈዉም በፖርት ሱዳን በኩል ነዉ።ይሕ ማለት የሆነ ተፅዕኖ ማሳረፊያ መሣሪያ ነዉ።ሩሲያዎች በይፋ የሚሉት ጦር ሠፈሩ ያስፈለጋቸዉ የባሕር ላይ ወንበዴዎችን ለመዋጋት ነዉ።ሶቭየት ሕብረት ዘመንም ባካባቢዉ ሥለነበሩ የቀድሞዉን ሠፈራችን መልሰን ያዝን ማለታቸዉ አይቀርም።ይሁንና ጁቡቲ ዉስጥ ጦር ካሰፈረችዉ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በገጠሙት ሽሚያ ሱዳንን በመቆጣጠር ባካባቢዉ መኖራቸዉን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ።»
በአዉሮጳ ጥቅም ላይ የሚኖረዉ ጫና
ሩሲያ ከዚሕ ቀደም ከማሊ እስከ ኒዠር ከሚገኙ መፈንቅለ መንግስት ከተደረገባቸዉ የአፍሪቃ ሐገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት መሥርታለች።የማሊ፣ የኒዠርና የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ ሁንታዎች  የፈረንሳይ፣ የዩናይትድ ስቴትስንና የተካታዮቻቸዉን ሐገር ጦር ሠፈሮች እየዘጉ ከሩሲያ ጋር እየተወዳጁ ነዉ።
የኃይል አሰላለፉ ለዉጥ ከጂኦ ፖለቲካ፣ ከጦር መሳሪያዉ ሽያጭ  በተጨማሪ ሞስኮዎች የኒዠርን ዩራኒየም፣ የማሊን አልማዝ፣ የሱዳንን ወርቅ በቀላሉ ከጠንካራ እጃቸዉ አስገቡ ማለት ነዉ።ጀርመናዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ አንድሬስ ሐይነማን እንደሚሉት የአፍሪቃ መንግስታት ከሩሲያ ጋር ከተባበሩ አዉሮጶች ለአፍሪቃ የሚሰጡት የልማት ምናልባትም የሰብአዊ ርዳትን አሰጣጥ መርሐቸዉን ማጤን አለባቸዉ።

«እንዲሕ አይነት መፈንቅለ መንግስት ሲደረግና መፈንቅለ መንግስት አድራጊዎቹ ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ ትብብር ሲመሠርቱ አዉሮጶች የሚሰጡት የልማት ርዳታ ቅድመ ግዴታ ሊኖር አይገባም ወይ የሚል ጥያቄ ማንሳት አለባቸዉ።በመፈንቅለ መንግስት ሥልጣን የያዙት ኃይላት ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ ትብብር ከመሰረቱ (አዉሮጶች የሚሰጡት) የልማት ተራዳኦ ምናልባትም የሰብአዊ ርዳታ  ገደብ ሊደረግበት ይገባል።በዚሕ ረገድ ፈረንሳይ ከጀርመን የተሻለ ጠንካራ አቋም ይዛለች።ይሁን እስካሁን ምዕራባዉያን መንግስታት ከሩሲያ ወታደራዊ ድጋፍ በሚያገኙት መፈንቅለ መንግስት አድራጊዎች አንፃር ወጥ አቋም የላቸዉም።»

ሩሲያ ከማሊ ጀምራ ኒዠርና ቡርኪና ፋሶን ተቆጣጥራ ሱዳን ለመግባት በምታደባበት ባሁኑ ወቅት የአዉሮጳ ፖለቲከኞች የአፍሪቃ ስደተኛ እንዳይገባባቸዉ በራቸዉን ለመዝጋት እየተጣጣሩ ነዉ።
ቱኒዚያ፣ ግብፅ፣ ሞሮኮና ሊቢያን የመሳሰሉ ሐገራት  የስደተኞን መተላለፊያ እንዲዘጉ አዉሮጶች በብዙ ቢሊዮን ዩሮ የሚቆጠር ገንዘብ ለሰሜን አፍሪቃዎቹ መንግስታት ሰጥተዋልም።ይሁንና ሩሲያ የስደተኞች መሸጋጋሪዎቹን መስመሮች ቀስበቀስ ከተቆጣጠረች ስደተኛዉ ከአፍሪቃ መዉጣት አለመዉጣቱ የሚወሰነዉ በሞስኮዎች ፈቃድ እንጂ በለንደን-ብራስልስ፣ በቱኒስ-ካይሮ ይሁንታ ሊሆን አይችልም።

የኒዤር ዉዝግብና አሜሪካ

እንደ ሱዳን ሁሉ ሁሉ ኒዤርም የአፍሪቃና የአፍሪቃን ጉዳይ የሚዘግቡ መገናኛ ዘዴዎችን ትኩረት ስባ ነዉ የሰነበተችዉ።የኒዤር ወታደራዊ ገዢዎች ባለፈዉ ሳምንት ባንድ በኩል የዩናይትድ ስቴትስ ጦርን ካገራቸዉ ሲሸኙ፣ በሌላ በኩል ከትንሽ ጎረቤታቸዉ ቤኒን ጋር ሲወዛገቡ ሳምንቱ በሳምንት ተተካ።

ትናንት ደግሞ የኒዤር ከፍተኛ ፍርድ ቤት አምና ሐምሌ በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን የተወገዱት የፕሬዝደንት የመሐመድ ባዝሙን ያለመከሠስ መብት ገፍፏል።ትናንትናዉኑ ኮቶኑ-ቢኒን ያስቻለዉ የቤኒን ፍርድ ቤት ባለፈዉ ሳምንት የቤኒን ፀጥታ አስከባሪዎች የያዟቸዉ የኒዤር የነዳጅ ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅና ሁለት ረዳቶቻቸዉ እንደታሰሩ እንዲቆዩ በይኗል።ከመጀመሪያዉ ጀምረን ባጫጭሩ እንቃኛቸዉ።

ኒዤር የሠፈረዉ የዩናይትድ ስቴትስ ከሐገሩ እንዲወጣ የኒዤር ሕዝብ ባደባባይ ሠልፍ ሲጠይቅምስል Mahamadou Hamidou/REUTERS

ጄኔራል አብዱረሕማኔ ሳኒ የመሩት ወታደራዊ ሁንታ የሐገሪቱን የሲቢል ፕሬዝደንት መሐመድ ባዝሙን ከሥልጣን ካስወገዱ ከአምና ሐምሌ ወዲሕ የሰሐራ በራይቱን ሐገር ፖለቲካ ከምራብ ወደ ምሥራቅ እየገፉት ነዉ።ከኒዤር በፊት መፈንቅለ መንግስት የተደረገባቸዉ የማሊና የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ ሁንታዎች እንዳደረጉት ሁሉ የኒዤር አዳዲስ ገዢዎችም ሐገሪቱ ከሩሲያና ከቻይና  ጋር የነበራትን ቀዝቃዛ ግንኙነት እያሟሟቁ ከምዕራባዉያን ጋር የነበራትን ጠንካራ ወዳጅነት እያላሉት ነዉ።

የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ከኒዤር መዉጣት ጀመረ

የኒያሚ ወታደራዊ ገዢዎች የኒዤር ከቀድሞ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጨርሶ በጥሰዉ፣አብዛኞቹን የፈረንሳይ ኩባንዮች አባርረዋል።ከሁሉም በላይ ለበርካታ አመታት ኒዤር የሠፈረዉን የፈረንሳይ ጦርም ከሐገራቸዉ አስወጥተዋል።

ባለፈዉ ግንቦት ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ከኒዤር እንዲወጣ ወስነዋል።ዩናይትድ ስቴትስ «አሸባሪዎችን የሚወጋ» ያለችዉን ወደ አንድ ሺሕ የሚጠጋ ወታደሮች ያሉት ጦር ኃይል ኒዤር ዉስጥ አስፍራ ነበር።የኒዤርና የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ባለፈዉ ግንቦት አጋማሽ ባደረጉት ስምምነት መሠረት የአሜሪካ ወታደሮች ካለፈዉ ሳምንት አርብ ጀምሮ ኒያሚ የሚገኘዉን ጦር ሠፈራቸዉን እየለቀቁ ነዉ።
የኒዤር የዞር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ኮሎኔል ማማኒ ሳኒ ኪያኦ ባለፈዉ ቅዳሜ በይፋ በተደረገዉ የሽኝት ሥርዓት ላይ እንዳሉት አርብና ቅዳሜ 270 የአሜሪካ ወታደሮች ከኒዤር ወጥተዋል።
«የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች ከኒዤር እንዲወጡ ሁለቱ ሐገራት ባለፈዉ ግንቦት 19፣2024 ከተስማሙ ወዲሕ ኒዠር ከሠፈሩት 946 የአሜሪካ ወታደሮች 269ኙ ከኒዠር ወጥተዋል።በርካታ ቶን መሳሪያም ከኒዤር ወጥቷል።ነሐሴ 7 ከኒያሚ ወታደራዊ አዉሮፕላን ማረፊያ የተነሳዉ የአሜሪካ C-130 ግሎባል ማስተር 3 ወታደራዊ አዉሮፕላን የመጀመሪያዎቹን ወታደሮችና የጦር መሳሪያ አሳፍሮ በርሯል።»

የኒዤርና የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ባደረጉት ሥምምነት መሠረት የአሜሪካ ጦር እስከሚቀጥለዉ መስከረም ድረስ የሠሐራ በረሐማይቱን ሐገር ሙሉ በሙሉ ለቅቆ ይወጣል።የኒዠር ዞር ኃይል በሕዝብ የተመረጡትን የሐገሪቱን ፕሬዝደንት በኃይል ከሥልጣን ማስወገዳቸዉን የፕሬዝደንት ጆ ባይደን መስተዳድር በተደጋጋሚ አዉግዟል።
የኒዤር ወታደራዊ ሁንታ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ከሐገሩ እንዲወጡ ከወሰነበትን ምክንያቶች አንዱም አሜሪካኖች በቀጥታም፣ በፈረንሳዮችም በምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ (ECOWAS) በኩሉም በወታደራዊ ሁንታዉ ላይ የሚያደርጉትን ግፊት ለመቃወም ነዉ። 

የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮችን ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ ከኒዤር የሚያጉዘዉ የአሜሪካ አይር ኃይል አዉሮፕላን ምስል Getty Images/AFP/L. Gelfand

ይሁንና የኒዤር ወታደራዊ ሁንታ ከሐገሪቱ የቀድሞ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ጋር የገዘጠመዉን ዓይነት አተካራ ከዩናትድ ስቴትስ ጋር አልገጠመም።ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ኮሎኔል ማማኒ ሳኒ ኪያኦም  የአሜሪካ ወታደሮች ከኒዤር መዉጣታቸዉ በሁለቱ ሐገራት ግንኙነት ላይ የሚያደርሰዉ ተፅዕኖ የለም ባይ ናቸዉ።
«በመጨረሻም ይሕ የአሜሪካ ኃይል ከኒዠር መዉጣት በኒዠር ሪፐብሊክና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል አሁን ባለዉ ግንኙነት ላይ ተፅዕኖ እንደማያሳድር ሁለቱ ሐገራት በድጋሚ ተስማምተዋል።»

የኒዤርና የቤኒን ዉዝግብ
ኮሎኔል ኮሎኔል ማማኒ ሳኒ ኪያኦ ርዕሠ ከተማ ኒያሚ ዉስጥ የአሜሪካን ጦር ሲሸኙ ወደ ትንሺቱ የኒዠር አጎራባች ቤኒን የተጓዙ የኒዠር የነዳጅ ዘይት ኩባንያ ባለሥልጣናትና ሠራተኞ እዚያዉ ቤኒን ዉስጥ ታስረዋል።ወደብ አልባዋ ኒዤር ነዳጅ ዘይት ወደ ዉጪ የምትልከዉ ሴሜ-ክፖጂ በተባለዉ የቤኒን ወደብ በኩል ነዉ።

ኒዤር ከረጅረም ዘመን ፍለጋ በኋላ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2011 አጋዴም በተባለዉ ግዛትዋ ያገኘችዉን ነዳጅ ዘይት ወደ ቤኒን ወደብ የሚያወርደዉን ቧንቧ የገነባዉ ዋብኮ-ኒዤር የተሰኘዉ የቻይናና የኒዤር ኩባንያ ነዉ።የቤኒን ፖሊስ ባለፈዉ ሳምንት የኒዤር ዜጎችን ያሰረዉም ሰዎቹ ሴሜ-ክፖ ወደብ የሚገኘዉን የነዳጅ ማጠራቀሚያ ሲጎበኙ ነዉ።ከታሠሩት አምስት ሰዎች አንዱ የኩባንያዉ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ናቸዉ።

የቤኒን ባለሥልጣናት እንደሚሉት ሰዎቹ የታሠሩት በሕገወጥ መንገድ ቤኒን በመግባታቸዉ ነዉ።ኒዤር ግን ቤኒን ዜጎቼን አግታለች በማለት ትወቅሳለች።የኒዤርና የቤኒን ዉዝግብ በራበት ትናንት ኒያሚ-ኒዤር ያስቻለዉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞዉ የሐገሪቱ ፕሬዝደንት የመሐመድ ባዝሙን ያለመከሰስ መብት ገፍፏል።የሱዳን ጦርነት የኒዤር ዉዝግብም ቀጥሏል።እኛ ለዛሬዉ በቃን።
ነጋሽ መሐመድ 
ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW