ሱዳን „የተጻራሪ መንግሥት“ ምስረታን ተቃወመች
ቅዳሜ፣ የካቲት 15 2017
ሱዳን „የተጻራሪ መንግሥት“ ምስረታን ተቃወመች
የናይሮቢዉ መንግሥት በሱዳን ተነጻጻሪ መንግሥት ለመመስረት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይላትን እና አጋሮቻቸዉን ያሳተፈ ስብሰባ ናይሮቢ ላይ ማዘጋጀቱን በመቃወም በያዝነዉ ሳምንት ሃሙስ ሱዳን፤ ኬንያ የሚገኘዉን አምባሳደሯን ጠርታለች። የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ካማል ጃባራ በሰጡት መግለጫ፤ ናይሮቢ የሚገኘዉን አምባሳደር የጠራነዉ፤ የፈጥኖ ደራሽ ሚሊሻያዎች እና አጋሮቻቸዉ በኬንያ አስተናጋጅነት ሱዳን ላይ የጥላቻ እርምጃ የሚወስዱ ስብሰባዎች ላይ ምላሽ ለመስጠት ነው ብለዋል። ሚኒስቴሩ የአካባቢውን ሰላም እና ደህንነት የሚያደፈርስ እና ሽብርተኝነትን እና የዘር ማጥፋትን የሚያበረታታ የናይሮቢዉ መንግስት "አደገኛ አካሄድን" ያሉትን እንዲተዉ አሳስበዋል። ሱዳን ቀደም ሲል የኬንያ ፕሬዝደንት፤ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የሚመራ መንግስትን ለመመስረት የሚደረግ ሴራን በመደገፍ እና በማበረታታት ስትል መክሰስዋ ይታወሳል። ኻርቱም ውስጥ በጦርነት መኻል የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈዉ ጦርነት
ሚያዝያ 2015 ዓም የተቀሰቀሰዉ እና ሁለት አመት ሊሞላዉ በጣም ጥቂት ጊዜ የቀረዉ የሱዳኑ የእርስ በእርስ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወትን ቀጥፏል፤ ከ 12 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ከቤት ንብረታቸዉ አፈናቅሏል። የቀድሞ የሱዳን ፕሬዚዳንት ዑመር አልበሽርን ከስልጣን ያስወገዱት የሱዳን ጦር ሰራዊት እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይላቱ ናቸዉ ያሉት በለንደን የሚገኙት የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ አብዱራህማን ሰይድ ፤ የህዝቡን ትግል ሰርቀዉ የፈፀሙት ጋብቻ ቀድሞዉንም ያላቻ ስለነበር ወደ ጦርነት አምርተዋል ብለዋል። የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ለሱዳን
አረብ ኢምሬት እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍ
የሱዳኑ የእርስ በእርስ ጦርነት የዉጭ ኃይላትን በማሰለፉ ነገሩን ከባድ እና አስጊ እያደረገዉ ነዉ ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ፤ ጦርነቱ በቀላሉ መፍትሄ የሚያገኝ እንዳልሆነም ጥርጣሬያቸዉን ገልፀዋል። ባለፈዉ ሰሞን አዲስ አበባ ላይ 38ኛዉ የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ተካሂዷል። እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሱዳናዊያን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማሰባሰብ አዲስ አበባ ላይ የተቀመጠ ጉባኤም ነበር። በዚህ ጉባኤ ላይ አረብ ኢምሬት ለሱዳን 200 ሚሊዮን ዶላር ሰብዓዊ እርዳታ ሰጥታለች። ኢትዮጵያ በበኩልዋ ለሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ የ 15 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንደምትሰጥ መግለጽዋ ተዘግቧል። በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት 30 ሚሊዮን ሱዳናዊያን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸዉ ተገልጿል። በመድረኩ ላይ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ፣ የቀድሞዉ የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀማት፣ የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ፣ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ሚንስትር ዴኤታ ሼክ ሻክቡት ቢን ናህያን አል ናህያን እና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዉ ነበር።የሱዳን ሰብአዊ ቀውስ መባባስ፤ ከጋና ምስጫ ምን እንማር?
የካርቱም እና የናይሮቢ ዉዝግብ
የአፍሪቃ ህብረት ለሱዳን ቀዉስ እስካሁን ለምን መፍትሄ አላገኘም ? የናይሮቢዉ መንግሥት በሱዳን ተነጻጻሪ መንግሥት ምስረታን በተመለከተ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይላትን የሚያሳትፍ ስብሰባ ናይሮቢ ላይ ይዘጋጃል መባሉን በመቃወም በያዝነዉ ሳምንት ሃሙስ ሱዳን ኬንያ የሚገኘዉን አምባሳደሯን አስጠርታለች። የሱዳን እና የኬንያ ቁርቁስ ዋናዉ ምክንያት ምንድን ነዉ? ሱዳን ሉዓላዊነቴን ተዳፍራለች፤ ጣልቃ ገብታኛለች ስትል ኬንያን ትከሳለች። ግን እንደዉ ኬንያ ከሱዳን ሚሊሻያ መሪ ከሃምዳን ዳጋሎ ሃሚቲ ወይም፤ ከፈጥኖ ደራሹ ኃይል የምታገኘዉ ልዩ ጥቅም አለ? ለምን ይህን እርምጃ ፈለገችዉ? ኬንያ አሁን የሱዳኑን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ማስተባበርዋን ትቀጥል ይሆን? ምን ይገምታሉ። ወይስ በግፊት ታቆመዉ ወይም ትገታዉ ይሆን?
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ