1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሱዳን ግብፅና ኤርትራ ታጣቂዎችን ይደግፋሉ ስትል ኢትዮጵያ በድጋሚ ወነጀለች

እስክንድር ፍሬው
ዓርብ፣ ጥቅምት 13 2019

በኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ እና በዉጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በጋራ በተዘጋጀ የፖሊሲ ውይይት ላይ ገላጻ ያደረጉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፣ በአካባቢው ያሉ የተለያዩ ሀገራት ትብብር ለህልውና በሚል ለተደራጀው የተቃዋሚዎች ጥምረት ድጋፍ ያደርጋሉ በሚል ተናግረዋል

አቶ ጌታቸዉ ረ,ዳ።አቶ ጌታቸዉ፣ ሱዳን ግብፅና ኤርትራ የ,ኢትዮጵያ ታጣቂዎችን ይደግፋሉ በማለት በድጋሚ ወነጀሉ
አቶ ጌታቸዉ ረዳ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳይ አማካሪምስል፦ Office of the Prime Minister-Ethiopia

ሱዳን ግብፅና ኤርትራ ታጣቂዎችን ይደግፋሉ ስትል ኢትዮጵያ በድጋሚ ወነጀለች

This browser does not support the audio element.


ሱዳን፣ ግብፅና ኤርትራ በኢትዮጵያ ለተቋቋመው የታጣቂዎች ትብብርድጋፍ ያደርጋሉ ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በድጋሚ ወንጅለዋል።የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸዉ በኢትዮጵያና በሱዳን ያለው ግጭት፣ በአፍሪካ ቀንድ ያለው የጂኦፖለቲካ ፉክክርና አሰላለፍ የሚንፀባረቅበት ጭምር መኾኑን ይናገራሉ።በሌላ በኩል፣ የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዮሱፍ ትናንት ባወጡት መግለጫ፣ ባለፈው ሰኛ በአብዬ ግዛት የተፈፀመውንና ቢያንስ 153 ሰዎች የተገደሉበትን የሰው አለባ አውሮፕላን ጥቃት በጽኑ አውግዘዋል።

የአትዮጵያ መንግሥት ውንጀላ

በኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ እና በዉጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በጋራ በተዘጋጀ የፖሊሲ ውይይት ላይ ገላጻ ያደረጉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትርጌታቸው ረዳ፣ በአካባቢው ያሉ የተለያዩ ሀገራት ትብብር ለህልውና በሚል ለተደራጀው የተቃዋሚዎች ጥምረት ድጋፍ ያደርጋሉ በሚል ተናግረዋል።

"የትብብሩ ተባባሪዎች- ተዋንያን ከሚባሉት ውስጥ፣ ሱዳን አለበት፣ ግብፅ አለበት፣ ኤርትራ አለበት" ብለዋል።

በስም የተጠቀሰት መንግሥታት በተለያያ ጊዜ በሰጧቸው አስተያየቶች የቀረቡባቸውን መሰል ውንጀላዎች አስተባብለዋል።

በአካባቢው ያለው የሀገራት አሰላለፍ ያለው ተጽዕኖ

በኢትዮጵያና በሱዳን ያለው ግጭት፣ በአፍሪካ ቀንድ ካለው የጂኦፖለቲካ ፉክክርና አለመረጋጋት ማሳያዎች አንዱ መኾኑን የፖለቲካና የፀጥታ ተንታኛች ይናገራሉ። እስራኤል፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬቶችና ኢትዮጵያ ባንድ ወገን፣ ግብፅ፣ ኤርትራና ሱዳን በሌላ ወገን፣ ያሉበት አሰላለፍ በሂደት ቅርፅ እየያዘ መምጣቱንም ይጠቅሳሉ። በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው መወነጃጀል ለምሳሌ ከዚሁ አሰላለፍ ጋር የተያያዘ መኾኑን ያምናሉ። በአብዱልፈታህ አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጊዜያዊ ሉአላዊ ምክር ቤት፣ ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ድጋፍ ታደርጋለች በማለት ኢትዮጵያን ይወነጅላል። ኢትዮጵያ በበኩሏ፣ የአልቡርሀን ቡድን በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ ሲገባና ታጣቂዎችን ሲደግፍ መቆየቱን በመግለጽ ትከሳለች።

የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኝ ዶ/ር እንጋላ ቾሜ እንደሚሉት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታም በቀጠናው ያለው የሀገራት አሰላለፍ የሚንፀባረቅበት ጭምር ነው። ። 

"የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት ያገረሸው፣ ግብፅ በተለይ የኢትዮጵያን የቀይ ባሕር ተደራሽነት ፍላጎት ለመቃወም፣ የቀይ ባሕር አዋሳኝ ሀገራትን እያደራጀችና እየመራች ባለችበት ወቅት መኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። እና ይሄ በግብፅ የሚመራውና ኤርትራ፣ ጂቡቲ ሶማሊያ ያሉበት ኢትዮጵያን ለመቃወም የተደራጀ የቀይ ባሕር ቅንጂት ከ2024 ገደማ ጀምሮ ቅርፅ እየያዘ ቆይቷል" በማለት አስረደተዋል።

የተባባሰው የሱዳን ጦርነትና የአፍሪካ ኀብረት መግለጫ

በሌላም በኩል፣ ባለፈው ሰኛ በአብዬ ግዛት በሚገኘው አሚዬት ገበያ አቅራቢያ የተፈፀመውና ቢያንስ የ153 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የድሮን ጥቃት ከተለያዩ አቅጣጫዎች ውግዘትን ማስከተሉን ቀጥሏል።

የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዮሱፍ ትናንት ባወጡት መግለጫ ድርጊቱን በእጅጉ አውግዘዋል። በሱዳን የቀጠለው ጦርነት የንጹሃንን ሕይወት እየቀጠፈ መኾኑንም ሰሞኑን የደረሱትን ጥቃቶች በመጥቀስ አብራርተዋል። ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻም፣ በምዕራብ ኮርዶፋን ግዛት 80 ሰዎች፣ በደቡብ ዳርፉር 23 ሰዎች፣ በካርቱም ደግሞ ሦስት ህጻናት መገደላቸውንም የመገናኛ ብዙሃንን ዘገባ መነሻ በማድረግ ዘርዝረዋል።  ሊቀመንበሩ በመልዐክታቸው፣ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች በሲቪሎችና በሲቪል ተቋማት ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ጥቃቶች እንዲቆጠቡ  አሳስበዋል።

በጀርመን የአለምአቀፍና የአካባቢ ጥናት ተቋም ተመራማሪ የኾኑት ሃገር አሊ ዛሬ ለዶይቸ ቨለ እንደገለፁት፣ በሱዳን በቀጠለው ግጭት በተለይ በሰው አልባ አውሮፕለን የሚጎዱ ሲቪሎች ቁጥር ጨምሯል።

"በተለይ በዚህ አመት ካለው የግጭቱ አካሄድ ጋር በተያያዘ የተስተዋለው ምንድን ነው፣ ለመጀመሪያ ገዜ አብዛኛዎቹ ሲቪሎች በሱዳን የሞቱትና የቆሰሉት በሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት ነው። ያ አስገራሚ ነው። ምክንያቱም በሰው አልባ አውሮፕላኖች የሚካሄዱ ጥቃቶች የሱዳን ጦር ኃይል ከዚህ ቀደም ይጠቀምባቸው ከነበሩት መሳሪያዎች እጅግ በበለጠ ኢላማቸውን መምታት የሚችሉ እንደኾኑ ይነገራል። ስለዚህ ይህ ማለት፣ የሰው አልባ አውሮፕላኖችን የሲቪሎችን ጉዳት በሚቀንስ መንገድ መጠቀም የሚያስችል በቂ ችሎታ የለም፣ ወይ ደግሞ በአንዳንድ ዘመቻዎች ወቀት ሲቪሎች ኾነ ተብሎ ኢላማ ይደረጋሉ ማለት ነው" በማለት አብራርተዋል።

የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሕሙድ አሊ የሱፍ ዓብዬ ግዛት ላይ የደረሰዉን ጥቃት አዉግዘዋልምስል፦ Michael Kappeler/dpa/picture alliance

የሱዳን ጦር ኃይልም ኾነ የጥኖ ደራሽ ኃይሉ የሚፈፅሟቸው ጥቃቶች በሲቩሎች ላይ ጉዳት እያደረሱ መቀጠላቸውንም ጠቅሰዋል።
 
የሱዳኑ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ያስከተለው ምላሽ

የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈው የድሮን ጥቃት የተፈፀመውሱዳንና ደቡብ ሱዳን የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱበት የአብዬ ግዛት በሚገኝ ገበያ አቀራቢያ ነው። ጥቃቱ የተፈፀመው በጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን በሚመራው የሱዳን ጦር ኃይል መኾኑን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል። የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም፣ ሱዳን ሲቪሎችን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ድርጊቶች እንድትቆጠብ አሳስቧል። በጁባ የሚገኙትን የሱዳን አምባሳደር በማስጠራትም ተቃውሞውን ገልጿል።  የአብዬ ግዛት በሱዳንና በደቡብ ሱዳን የይገባኛል ውዝግብ ያለበት በመኾኑ ምክንያት በዚያ የተሰማራው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጊዜያዊ የፀጥታ ኃይል አሁንም በስፍራው ይገኛል። የፀጥታ ኃይሉ የደረሰውን ጉዳት እየገመገመ መኾኑን የተናገሩት የድርጅቱ ዋና ፀኃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ፣ ሲቪሎችንና የሲቪል ተቋማትን ኢላማ ማድረግ በአለምአቀፍ ሕግ የተከለከለ ነው ብለዋል። "ተፋላሚ ወገኖቹ በዚህ አለምአቀፍ ሕግ መሰረት ያለባቸውን ግዴታ መወጣት እንዳለባቸው ማስታወስ እፈልጋለሁ" በማለትም አክለዋል።

እስክንድር ፍሬዉ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW