ሲዳማ ክልል የሦስት ባለሥልጣናትን ያለመከሰስ መብት አነሳ
ሰኞ፣ ጥቅምት 19 2016የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 6ኛ ዙር 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ከምክር ቤቱ ውሳኔዎች መካከል የሦስት አባላቱን ያለመከሰስ መብት ማንሳት ፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤቶችን ማደራጀትና የቢሮ ሃላፊዎችን ሹመት ማፅደቅ ይገኙባቸዋል፡፡
የለመከሰስ መብት መገፈፍየሲዳማ ክልል ተጨማሪ የሰብዓዊ እርዳታ ጥሪ
ምክር ቤቱ በአስቸኳይ ጉባዔው ሦስት የምክር ቤት አባላቱን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱን የምክር ቤቱ ዋና አፍ ጉባዔ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ የጉባዔውን መጠናቀቅ ተከትሎ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል ፡፡ ያለመከሰስ መብቱ የተነሳው የምከር ቤቱ አባላት በጉዳዩ ላይ እንዲወያዩበት ከተደረገ በኋላ መሆኑን የጠቀሱት ዋና አፈ ጉባዔዋ “ ጉባዔተኛው በህግ ተጠያቂነት ላይ ሀሳብ ቀርቦ ውይይት አድርጎበታል ፡፡ የተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ በህግ እንዲታይ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ታምኖበት አባላቱ ድምፅ ሰጥተውበታል ፡፡ በዚህም በሦስት ድምፅ ታቅቦ ውሳኔው በአብላጫ ድምፅ ሊያልፍ ችሏል “ ብለዋል፡፡
የቀድሞው የሀዋሳ ከንቲባየሲፌፓ አቤቱታ እና የምክር ቤቱ ምላሽ
በዛሬው የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባዔ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳባቸው የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ፣ አቶ አበራ አሬራ እና አቶ ተሰማ ደንጉሼ የተባሉ የምክር ቤት አባላት ናቸው ፡፡ በተለይም ፀጋዬ ቱኬ ባለፈው የነሀሴ ወር በሀዋሳ ከተማ ሲካሄድ የነበረውን የክልሉን ከፍተኛ የአመራሮች ግምገማ ረግጠው ወጡ ከተባለ በኋላ ለወራት ከእይታ ተሰውረው መቆየታቸው ይታወሳል ፡፡ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከረጅም ጊዜ ክትትል በኋላ ከንቲባውን በቁጥጥር ሥር አውያቸዋለሁ ሲል ባለፈው ማክሰኞ ማስታወቁ አይዘነጋም ፡፡
የከፍተኛ ፍርድ ቤቶች መቋቋምና የሃላፊዎች ሹመት
ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም ህዝቡ በፍትህ ፍለጋ እየደረሰበት የሚገኘውን መጉላላት ለማስቀረት በክልሉ አራት የከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እንዲቋቋሙ በቀረበው ሞሽን ላይ ተወያይቶ ማፅደቁንም አፈ ጉባዔዋ ገልጸዋል ፡፡ የፍርድ ቤቶቹ መቀመጫም በአለታወንዶ፣ በበንሳ፣ በይርጋለምና በሀዋሳ ከተሞች ላይ እንዲሆን መወሰኑም በጉባዔው ላይ ተገልጿል።ምክር ቤቱ በመጨረሻም ለሦስት የአስፈጻሚ ቢሮዎች የቀረበለትን የሃላፊዎች ሹመትም ተቀብሎ አጽድቋል፡፡በዚሁ መሰረት አቶ ጎሳዬ ጎዳና የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ፣ አቶ ወሰንየለህ ሰለሞን የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ፣ ወይዘሮ ሰላማዊት መኩሪያ የንግድ ቢሮ ሃላፊ ሆነው ተሹመዋል።
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ