ሲዳማ የዞን መስተዳድሮችን እያዋቀረ ነው
ረቡዕ፣ ሰኔ 21 2015የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት አራት የዞን መስተዳድሮችን አዋቀረ ፡፡ በዞኖቹ የምሥረታ ጉባዔ ላይ የክልሉ ርዕስ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የዞኖቹ መዋቀር ሕዝቡ አገልግሎቶችን በቅርበት ለማግኘት ሲያነሳ ለነበረው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡ የክልሉ ፖለቲከኞች በበኩላቸው የዞን መዋቅር ዝርጋታው የክልሉን አስተዳደራዊ ወጪ በማናር የበጀት ጫና እንዳይፈጥር ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል ፡፡
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ክልሉ በአራት የዞን አስተዳደር እንዲዋቀር የሚያስችለውን ውሳኔ ያሳለፈው በ2014 ዓም የነሀሴ ወር ላይ ነበር ፡፡ ይሁንና ከአንድ ዓመት ገደማ ቆይታ በኋላ ዛሬ የዞን መዋቅሮቹን የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ፡፡ የዞን ምክር ቤቶቻቸውን እያደራጁ የሚገኙት ዞኖች ምሥራቃዊ ፣ ሰሜናዊ ፣ ደቡባዊ እና ማዕከላዊ ዞኖች የሚል መጠሪያ ያላቸው ናቸው ፡፡
በምስራቅ ሲዳማ ዞን ምሥረታ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የዞኖቹ መዋቀር ህዝቡ አገልግሎቶችን በቅርበት ለማግኘት ሲያነሳ ለነበረው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ነው ብለዋል ፡፡ ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ ህዝቡ የሚያቀርባቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እየመለሰ እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ ደስታ “ የዞን መዋቅር ከህብረተሰቡ የረጅም ጊዜ ፍላጎቶች አንዱ ነበር ፡፡ አሁን ላይ ለዚህ የሚሆን ምላሽ ተገኝቷል “ ብለዋል፡፡
የአስተዳደር መቀመጫውን የዳዬ ከተማን አድርጎ ምሥረታው ያካሄደው የምስራቅ ሲዳማ ዞን መስተዳድር ምክር ቤት የዞኑን ዋና አስተዳዳሪ ሹመትን ጨምሮ ሌሎች የካቢኔ አባላት ምርጫን አካሂዷል፡፡
ዶቼ ቬለ (DW) በክልሉ የዞን መዋቅር ዝርጋታ ዙሪያ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ሊቀመንበር ረዳት ፕሮፌሰር ተሰማ ኤሊያስ መዋቅሩ በሁሉት መንገድ ሊታይ ይገባል ይላሉ ፡፡ የዞኖቹ መዋቀር ህብረተሰቡ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በቅርበት ለማግኘት እንደሚያስችሉት የተናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ተሰማ “ ነገር ግን መዋቅሩ ሲሰፋ ለቢሮ ፣ ለተሽከርካሪ ፣ ለሹመኞች ወዘተ የሚከፈለው ክፍያ የክልሉን ውስን ሀብት ሊበላ ይችላል ፡፡ በእኔ እምነት የዞን መዋቅር ብቻው በራሱ ግብ አይደለም ፡፡ ጠንካራ መዋቅሮችን አብሮ መዘርጋት ያሥፈልጋል ፡፡ በተለይ አሁን በክልሉ ጎልተው የሚስተዋሉ የሙስና ፣ የጎሰኝነት እና ሌሎች ብልሹ አሠራሮችንም መቅረፍ ይገባል ፡፡ አነኝህ ችግሮች የዞን መዋቅር በመዘርጋት ብቻ መፍትሄ ሊያገኙ የሚችሉ አይደሉም ፡፡ ተጨማሪ ሥራዎች ያሥፈልጋሉ “ ብለዋል ፡፡
ፎቶ ፡ ከሲዳማ ክልል ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ጽሕፈት ቤት
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ