ሳልሳይ ወያነ ትግራይ የህወሓት ወታደራዊ ክንፍን መክሰሱ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 9 2017
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ያወጣው በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፥ ከጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት ባላገገመችው ትግራይ ለአንድ የፖለቲካ ሐይል ባጋደሉ ታጣቂዎች ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈፀሙ ነው ብሏል። ሰሞኑን በዓዲጉደም እና ሞኾኒ ከተፈጠሩ ሞትን ያስከተሉ ክስተቶች በተጨማሪ በሌሎች ተጋሩ ላይም የተለዩ በደሎች እየተፈፀሙ ነው ሲል ገልጿል። የእነዚህ ጥፋቶች ተጠያቂ «የህወሓት ፖለቲካዊ ክንፍ» መሆኑ ደግሞ ለእነዚህ ተግባራት «የሕግ ማስከበር እርምጃ» በማለት ሓላፊነት ወስዷል ያለው ተቃዋሚው ፓርቲው፥ የህወሓት ወታደራዊ ክንፍን ትዕዛዝ ተቀብለው በንጹሐን ላይ እጃቸውን የሚያነሱት ደግሞ ከተጠያቂነት አያመልጡም ብሏል።
ለዶቼቬለ የተናገሩት የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር አሉላ ሃይሉ፥ የህወሓት ወታደራዊ ክንፍ የአስተዳደር አካላትን «ለነሱ ታማኝ በሆኑ የመቀየር» ሕገወጥ ተግባር እየፈፀሙ ነው፥ ይህ ደግሞ በትግራይ ከፍተኛ አደጋ ፈጥሮ ይገኛል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም ሳልሳይ ወያነ ትግራይ በክልሉ ያለውን ፖለቲካዊ ቀውስ ለመፍታት ሁሉም ሐይሎች የሚያሳትፍ «ብሔራዊ ጉባኤ» ተጠርቶ መፍትሔዎች ማበጀት ይገባል ይላል።
ከዚህ በተጨማሪ ተቃዋሚው ፓርቲ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ በትናንቱ መግለጫው ጨምሮ እንዳለው፥ እያንዳንዱ የትግራይ ሠራዊት አባል ራሳቸውን «ኮር እና ከኮር በላይ» ብለው ከሚጠሩ የህወሓት ወታደራዊ ክንፍ አዛዦች የሚሰጥ ንጹሐን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንዳይቀበሉ ጥሪ አቅርቧል።
በትግራይ በተለይም ባለፈው ሳምንት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መፈንቅለ መንግሥት ያለው እና በታጣቂዎች የተደገፈ የአስተዳደር አካላትን የመቀየር ተግባራት በተለያዩ ከተሞች እና ወረዳዎች የታየ ሲሆን፥ ይህን ተግባር በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ "«ሕግ ማስከበር» እንቅስቃሴ እንዳለው ይታወሳል።
ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ