1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዲዛይነት ምህረት ታሪኩ

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ኅዳር 9 2015

በቤተሰቧ ሳሎን ውስጥ በአንድ የልብስ ስፌት ማሽን የስፌት ሥራ እንደጀመረች ታሪኳን ያጫወተችን ምህረት ታሪኩ ትባላለች። ምህረት የሰፋችውን አንድ ከረባትም ዩናይትድ ስቴትስ ለሚገኙ የአንድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ልካም ነበር። ለምን?

Äthiopien Modedesignerin Mihret Tariku und ihr Label
ምስል Privat

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ውስጥ ከከፍተኛ ተቋም ተመርቀው ስራ የማያገኙ ወጣቶች ቁጥር እጅግ ብዙ የሚባል ነው። ከእነዚህ ምሩቃን አንዷ ምህረት ታሪኩ ትባላለች። የ 25 ዓመት ወጣት  የሆነችው ምህረት ታሪኩ በ 2014 ዓም ከጅማ ዩንቨርስቲ በማቴሪያል ኢንጂነሪንግ ተመርቃለች። በተመረቀችበት መስክ ግን ስራ አላገኘችም። « 47 ገደማ ተማሪዎች ነበርን ግን ስራ አላገኘንም። ስራ ለማግኘት በጣም ሞክረናል። ስራ አገኘሽ ወይ የሚል ነገር ስላለ ድብርት ውስጥ ላለመግባት አማራጭ መፈለግ ያስፈልጋል። » ስለሆነም አብዛኞቻቸው ቤተሰባቸው በተሰማራበት የስራ መስክ ለምሳሌ ንግድ እየተሳተፉ እንደሆነ ምህረት ትናገራለች። ምህረት ብዙም ማሰብ አልነበረባትም። አማራጯ ከመጀመሪያው አንስቶ መስራት ወይም መማር የፈለገችው የፋሽን ዲዛይን ስራ ሆነ። « ከስምንተኛ ክፍል አንስቶ እሰፋ ነበር። በማገኘው ቁሳቁስ ጫማዎችን ፣ቦርሳዎችን እና ልብሶችን በአሻንጉሊት እለማመድ ነበር። ከፍ ስልም ቴክስታይል ፋሽን ዲዛይን መማር ፈለኩ፤ የተመደብኩት ግን ኢጂነሪንግ ነበር።» ይህንንም ዩንቨርስቲ ገብታ ለአምስት አመታት ያህል ተከታተለች። ይሁንና በመጨረሻ ድሮም ልትሰራበት የምትመኘው የፋሽን ስራን ሀ ብላ ጀምራለች። እነዚህ አምስት አመታት በከንቱ የባከኑ ናቸው?  በአንድ በኩል አዎ በሌላ በኩል ደግሞ አይ ትላለች ምህረት። 
የራሷን ተሞክሮ ምሳሌ በማድረግ አንድ ተማሪ የፈለገውን ትምህርት በከፍተኛ ተቋም ደረጃ እንዲያጠና ቅድሚያ ቢሰጠው ጥሩ እንደሆነ እና የትምህርት ፖሊሲው ላይ ቢስተካከል የምትለው ሀሳብን ምህረት እንዲህ ስትል ትገልፃለች።  « የመጀመሪያ የተመደብኩበት ሰሞን ላይ የመማር ፍላጎቱ አልነበረኝም።  ቤተሰብ ከኔ መማርን ይጠብቃል በሚል ነው የተማርኩት። ፋሽን ዲዛይን ከመጀመሪያው ደርሶኝ ቢሆን ጥሩ ደረጃ ላይ እደርስ ነበር። እና ትምህርት በፍላጎት ቢሆን ያ ሰው ደስተኛም እየሆነ በጣም ብዙ ነገሮችን ማወቅ ፣ መስራት ራሱንም መለወጥ የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል።»
ምህረት ስራዬ ብላ ልብስ መስፋት የጀመረችው የቤተሰቧ ሳሎን ቤት ውስጥ ነው። በወቅቱ አንድ ትንሽ ስፌት መኪና ነበራት። ትሰፋ የነበረውም ማታ ማታ ነው። « ስፌት የጀመርኩት በእናትና በአባቴ ሳሎን ቤት ውስጥ ነው ። እነሱ እስከሚተኙ ያለውን ሰዓት ድምፅ የማያወጣ ለምሳሌ እንደ ዲዛይን ማውጣት አይነት ስራ እሰራለሁ። እነሱ ሲተኙ ደግሞ የመስፋት እና የመግጠሙን ስራ እሰራለሁ።» ምህረት በአሁኑ ሰዓት BOMERC ዲዛይን የተሰኘ የንግድ መለያ አላት። ንግዱን አብሯት የመሰረተው ቦኤዝ ብርሀኑ ይባላል። ቦኤዝ ጅማ ዩንቨርስቲ የኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ መምህር እና ለጀማሪ ድርጅቶች ወይም Start-ups አማካሪም ነው።  ምህረት ስፌቶቿን ፌስቡክ  እና ቴሌግራም የመሳሰሉ የማህበራዎ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ታስተዋውቃለች። 
ለንግድ የሚሆን የፋሽን ውጤቶችን ምህረት መስፋት ስትጀምር ከእውቀት ይልቅ ፍላጎቷ ብቻ ያመዝን እንደነበር ከመናገር አትሸሽግም። « ማንም ያስተማረኝ ሰው የለም። ራሴን በራሴ ነው እያስተማርኩ የመጣሁት። የትኛውንም ስራ ለመስራት ድፍረቱ ስላለኝ እሞካክራለሁ። » በአሁኑ ሰዓት ምህረት በተለይ የሴቶች ቦርሳ ላይ ባህላዊ ጥለቶችን እየተጠቀመች ትኩረት ሰጥታ ትሰራለች። ምህረት አንድ የሰፋችውን ከረባት በመካከለኛው ዩናይትድ ስቴትስ ኢንዲያና ግዛት የሚገኘው የ Purdue University ፕሬዚዳንት ለሆኑት ሚች ዳኒኤልስ ልካ ነበር። ለእኚህ ሰው ለመላክ የመረጠችውም አብሯት ንግዱን የመሰረተው ቡኤዝ በአጋጣሚ በማንዴላ ዋሽንግተን ፌሎውሺፕ ስር ከሌሎች በርካታ የአፍሪቃ ወጣቶች ጋር ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ይሄድ እና እኝህን የዩንቨርስቲ ፕሬዚዳንትም ያገኝ ስለነበር ነው። የምህረት ዋና አላማ ምን እንደነበር ስትናገር « ወጣቶች እድሉን ስላላገኘን እንጂ መስራት እንደምንችል ለማሳየት  እና የራሴን ጥረት ለመግለፅ ፈልጌ ነው።» ትላለች ፕሬዚዳንቱም የምህረት ከረባት እንደደረሰባቸው በመግለፅ አበረታታች ደብዳቤ ፅፈውላታል።
ምህረት ለእኚህ የዩንቨርስቲ ፕሬዚዳንት ስትፅፍ ከማህበረሰቡ በርካታ ፈተናዎች ገጥሟት እንደነበር አንስታላቸዋለች። ትልቁ የገጠማት ፈተናም ብዙ ሰዎች ለምን አምስት አመት በተማረችው ሙያ ስራ እንደማትፈልግ የሚያነሱላት ጥያቄ ነበር። አሁን ግን በጀመረችው የፋሽን ስራ ገፍታ ለመስራት ምህረት ቆርጣ ተነስታለች።  « የመጀመሪያው ፍላጎቴም ስለነበር በጣም ደስ ብሎኝ ነው አሁን እየሰራሁ ያለሁት። በተቻለኝ አቅም ሌሎች ማሽኖችን ጨምሬ ፣ የተማረ የሰው ኃይልም ቀላቅዬ ሀገሬ የምትታወቅበት የፋሽን ዲዛይን አስተዋጽዎ ለማድረግ እየሞከርኩ ነው» ትላለች።

ምህረት ታሪኩ የምትሰፋቸው ቦርሳዎችምስል Privat
ምህረት BOMERC ዲዛይን የተሰኘ የንግድ መለያ አላትምስል Privat

ልደት አበበ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW