1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነሐሴ 27 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ነሐሴ 27 2016

ኢትዮጵያ በፓሪስ ፓራሊምፒክ በወርቅ ተሽቆጥቁጣለች ። ማንቸስተር ዩናይትድ በገዛ ሜዳው ኦልድ ትራፎርድ ጉድ ሆኗል ። እስካሁን አንድም ግብ ባልተቆጠረበት ሊቨርፑል የ3 ለዜሮ ብርቱ ቅጣት ደርሶበታል ። ቸልሲ እናs አርሰናል ነጥብ ጥለዋል ። ማንቸስተር ሲቲ በአሸናፊነት ግስጋሴው ገፍቶበታል ።

Tigest ist der erste äthiopische Paralympiker, der eine Goldmedaille gewann
ምስል Himanot Tirune/DW

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

ማንቸስተር ዩናይትድ በገዛ ሜዳው ኦልድ ትራፎርድ ጉድ ሆኗል ። እስካሁን አንድም ግብ ባልተቆጠረበት ሊቨርፑል የ3 ለዜሮ ብርቱ ቅጣት ደርሶበታል ። ቸልሲ ትናንት አርሰናል ቅዳሜ ዕለት ነጥብ ጥለዋል ። ማንቸስተር ሲቲ በአሸናፊነት ግስጋሴው ገፍቶበታል ። እስካሁን በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ከሊቨርፑል ጋ በእኩል ነጥብ እና ተመሳሳይ የተጣራ ግብ ሆኖም ብዙ በማግባት ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ተቆጥሮበታል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ ከታችኛው ዲቪዚዮን ያደገው ሐይደንሀይም በጨዋታ ዘመኑ ሁለተኛ ዙር ውድድር ቢሆንም ባዬርን ሙይንሽንን በልጦ በደረጃ ሠንጠረዡ አንደኛ ላይ ሰፍሯል ። የአትሌቲክስ እና ሌሎች ስፖርታዊ መረጃዎችን አካተናል

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያ በዘንድሮ የፓሪስ 2024 ፓራሊምፒክስ ፉክክር ተደጋጋሚ ድሎችን እያስገኘች ነው ። ስታድ ደ ፍራንስ ውስጥ ዛሬ ጠዋት በነበረው የ1500ሜትር T11 (ሙሉ ለሙሉ ማየት በተሳናቸው) ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ያየሽ ጌጤ የራሷን ክብረወሰን በመስበር ጭምር የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች ። ያየሽ ከረዳቷ ክንዱ ሲሳይ ጋር አብራ በመሮጥ ባደረገችው ፉክክር ለድል የበቃችው ውድድሩን በ4 ነጥብ አምስት ሰከንድ በማሻሻል ጭምር ነው ።

ያየሽ ከሁለት ወር በፊት ኮቤ ውስጥ በነበረው የዓለም ፓራሊምፒክስ አትሌቲክስ ፍጻሜ ፉክክርም ክብረወስን በመስበር ጭምር ነበር ያሸነፈችው ። ያየሽ በኦሎምፒክ ድል ስታስመዘግብም የመጀመሪያዋ ነው ።

ኢትዮጵያ በዘንድሮ ውድድር በሁለት ሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ተካፍይ ሆና በሁለቱም ሴት አትሌቶች የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግባለች ። ውድድሩን ያጠናቀቀችበር 4:27.68 አዲስ ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል ። የቻይና ሯጭ ሻንሻን 4:32.82 በመሮጥ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች ። ደቡብ አፍሪቃዊቷ ደሎውዛኔ ኮዬትዜ የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘት ችላለች ።

ዛሬ በተመሳሳይ በተካሄደ የወንዶች የ1500ሜትር T11 ማለትም የማጣሪያ ውድድር ይታያል ሁለተኛ በመውጣት ነገ ለሚደረገው የፍጻሜ ውድድር አላፊ መሆኑን አረጋግጧል ። 

በሌላ  የፓሪስ 2024 ፓራሊምፒክስ የሴቶች 1500 ሜትር የT13 (በጭላንጭል የሚያዩ) የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት ገዛኻኝ ትናንት አሸናፊ በመሆን የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች ። 80 ሺህ ታዳሚዎች በተገኙበት የፍጻሜው ውድድር አትሌት ትእግስት አስደማሚ ድል ስታስመዘግብ በስፍራው የነበረችው የፓሪስ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ ቀጣዩን ዘገባ ልካልናለች ።

በፓሪስ ፓራሊፒክስ ኢትዮፕያ ተደጋጋሚ ድል ቀንቷታል ምስል Himanot Tirune/DW

በፔሩ ሊማ በተካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ፉክክር የኢትዮጵያ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ደማቅ ታሪክ አስመዝግቧል ።  ካለፈው ሳምንት ማክሰኞ ነሐሴ 21 ቀን፣ እስከ ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በነበረው ፉክክር የኢትዮጵያ ቡድን ስድስት የወርቅ፤ ሁለት የብር እና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ፉክክሩን በከፍተኛ ድል አጠናቋል ።

ኢትዮጵያን የቀደመችው ዩናይትድ ስቴትስ ስምንት የወርቅ፤ አራት የብር እንዲሁም አራት የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች ። ቻይና በአራት ወርቅ፤ በአራት ብር እና በሦስት ነሐስ ሦስተና ደረጃ ይዛለች ። ተመሳሳይ አራት የወርቅ እና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ ያገኘችው ጃማይካ አራተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች። ኬንያ በሦስት ወርቅ፤ በሦስት የብር እና በአንድ የነሐስ ሜዳሊያ አምስተኛ ሆናለች ። ጀርመን በአንድ ወርቅ እና በሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎች ብቻ ተወስኖ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ 14ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ።  ከስሩ ፈረንሳይ እና ኖርዌይ በአንድ የወርቅ ሜዳሊያ  15ኛ ደረጃ አግኝተዋል ። 

እግር ኳስ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ  የእግር ኳስ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣርያ  ባለፈው ሳምንት ባደረጋቸው ጨዋታዎች ከሱዳን ብሔራዊ ቡድን ጋር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም 2-0 አሸንፏል ። ግቦቹን ቢንያም ዐይተን እና ቸርነት ጉግሳ አስቆጥረዋል ።  ብሔራዊ ቡድኑ ቀደም ሲል በተመሳሳይ የልምምድ ጨዋታ ከድሬዳዋ ከተማ ቡድንን ጋ በማድረግ 4-0 አሸንፏል ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በ2025 የአፍሪቃካ ዋንጫ ማጣርያ ከታንዛንያ እና ኮንጎ ዲ.ሪ ጋር ለሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ዛሬ ወደ ታንዛኒያ ማቅናቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዐሳውቋል ።

የፓራሊምፒክስ ውድድር የሚካሄድበት ስፍራ ። ፓሪስ ፈረንሳይምስል DIMITAR DILKOFF/AFP

ፕሬሚየር ሊግ

ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት በሜዳው ኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም የ3 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል ። በትናንቱ ግጥሚያ ማንቸስተርን ጉድ ያደረገው ሊቨርፑል ነው ። የምሽቱ ድንቅ ተጨዋች የተባለው ኮሎምቢያዊው ሉዊስ ዲያዝ በ35ኛው እና 42ኛው ደቂቃዎች ላይ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል ። ኳሶችን በግሩም ሁኔታ ሲያመቻች የነበረው ግብጻዊው ሞሐመድ ሣላኅ በበኩሉ 56ኛው ደቂቃ ላይ ሦስተኛዋን ኳስ ከመረብ አሳርፏል ። ከጨዋታው በኋላ በባዶ እግሩ ከመልበሻ ክፍል ወጥቶ ባደረገው አጠር ያለ ቃለ መጠይቅ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ከሊቨርፑል ጋ እንደሚለያይ ጠቁሟል ። ከሊቨርፑል ጋ ያደረገው የሦስት ዓመት ውልም በቀጣዩ የጎርጎሪዮሱ ዓመት በጋ ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ።  ውሉን ስለማራዘምም እስካሁን ያናገረው ሰው እንደሌለ ትናንት ገልጧል ።

ቸልሲ በሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ ከክሪስታል ፓላስ 1:1 ሲወጣ፤ ኒውካስል ቶትንሀምን 2 ለ 1 አሸንፎ ሸኝቷል ።  ቅዳሜ ዕለት በነበሩ ግጥሚያዎች፦ ኢፕስዊች ከፉልሀም ጋ አንድ እኩል ወጥቶ ነጥብ ተጋርቷል ። ላይስተር ሲቲ በአስቶን ቪላ የ2 ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል ። ኤቨርተን በሜዳው ጉዲሰን ፓርክ ስታዲየም በቦርመስ የ3 ለ2 ሽንፈት ደርሶበታል ። ብሬንትፎርድ ሳውዝሐምፕተንን 3 ለ1 አሸንፏል ። ኖቲንግሀም ፎረስት ከዎልቨርሐምፕተን እንዲሁም 49ኛ ደቂቃ ላይ ዴክላን ራይስ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተበት አርሰናል ከብራይተን ጋ አንድ እኩል ተለያይተዋል ።

በጀርመናዊው አማካይ ካይ ሐቫርትስ ቀዳሚውን ግብ ያስቆጠረው በሜዳው ኤሚሬትስ ስታዲየም የተጫወተው አርሰናል ነበር ። ከረፍት መልስ ጃዎ ፔድሮ ብራይተንን አቻ አድርጎ ነጥብ ለመጋራት ያስቻለውን ኳስ ከመረብ አሳርፏል ። በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተው ዴክላን ራይስ ጉዳይ አጨቃጭቋል ። ጨዋታው ዳግም እንዳይጀምር ሆን ብሎ ለቅጣት የተመቻቸችውን ኳስ ጨረፍ አድርጎ በመምታት አዘግይቷል በሚል ነበር ዳኛው በሁለተኛ ቢጫ ቀይ ካርድ ያስወጡት ። በርካታ ደጋፊዎች ሆን ብሎ ቅጣት ምቱን አላጨናገፈም ሲሉ ተከራክረዋል ።

ኧርሊንግ ኦላንድ ሦሰት ኳሶችን ከመረብ አሳርፎ ሔትሪክ በሠራበት ግጠሚያ ማንቸስተር ሲቲ ዌስትሐም ዩናይትድን በሜዳው ኦሎምፒያስታዲዮን 3 ለ1 አሸንፏል ። ማንቸስተር ሲቲ በመጀመሪያው አጋማሽ አንድ እኩል በሆነበት ወቅት ምናልባትም 3 አለያም 4 ለዜሮ መምራትም ይችል ነበር ። የባከነው ደቂቃም ተጨምሮ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲልም የግብ ቀበኛው ኧርሊንግ ኦላንድ አራተኛ ግቡ ሊሆን የሚችል ኳስ በግብ ጠባቂው ተጨናግጦበታል ። እስካሁን 7 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ በብቸኝነት እየገሰገሰ ነው ። የሊቨርፑል አጥቂ ሉዊስ ዲያዝ እና የብሬንትፎርድ አማካይ ብሪያን ምቤውሞ ሦስት ግብ አላቸው ።

የኤርቤ ላይፕትሲሽ የስሎቬኒያ አማካይ ኬቪን ካምፕልምስል UWE KRAFT/AFP via Getty Images

ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ በሦስት ግጥሚያ ዘጠኝ ነጥብ ሰብስበው አንደኛ እና ሁለተኛ ናቸው ። ሁለቱ ቡድኖች ሰባት ተመሳሳይ የተጣራ ግብ ክፍያ ሲኖራቸው፥ ሊቨርፑል እስካሁን የግብ ክልሉ አልተደፈረም ። ብራይተን፤ አርሰናል እና ኒውካስል በሦስት ጨዋታዎች እስካሁን ሰባት ሰባት ነጥብ ሰብስበው ከሦስተኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ተደርድረዋል ።   የሐምሌ 22 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ቡንደስሊጋ

ከታችኛው ዲቪዚዮን ያደገው ሐይደንሀይም ገና ከሁለት ጨዋታዎች በኋላም ቢሆን ምሥጋና ለባዬርን ሙይንሽን እያለ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ሰፍሯል ። ከባዬርን ሙይንሽን በውሰት ለሐይደንሀይም የሚጫወተው የ18 ዓመቱ ፖል ቫነር 9ኛ ደቂቃ ላይ በቀዳሚነት ያስቆጠራት ተደምራ አውግስቡርግን 4 ለ0 ጉድ አድርጓል ።

ሐይደንሀይም፤ ባዬርን ሙይንሽን እና ኤር ቤ ላይፕትሲሽ እያንዳንዳቸው በስድስት ነጥብ ቀዳሚው ስፍራ ላይ ናቸው ። ዶርትሙንድ እና ዑኒዮን ቤርሊን በ4 ነጥብ አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍረዋል ።

ቶማስ ሙይለር እጅግ ስሜታዊ ያደረገውን ምርጥ ግብ ተቀይሮ ከገባ በኋላ 78ኛ ደቂቃ ላይ ነበር ያስቆጠረው ምስል Sven Hoppe/dpa/picture alliance

ባዬርን ሙይንሽን ፍራይቡርግን ትናንት 2 ለ0 ድል አድርጓል ። ቀዳሚዋን ኳስ ሐሪ ኬን ከመረብ አሳርፏል ። ሔሪ ኬን የአውሮጳ ምርጥ ግብ አግቢ በሚል በተሸለመው ወርቃማ ጫማ ነበር ፍጹም ቅጣት ምቱን በተረጋጋ መልኩ በግሩም ሁኔታ ያስቆጠረው ። የሐምሌ 15 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ቶማስ ሙይለር እጅግ ስሜታዊ ያደረገውን ምርጥ ግብ ተቀይሮ ከገባ በኋላ 78ኛ ደቂቃ ላይ ነበር ያስቆጠረው ። ሠርጌ ግናብሬ ያሻማውን ኳስ ቶማስ ሙይለር በቀኝ እግሩ ተቆጣጥሮ ሰውነቱን በማዞር በግራ እግሩ በቀጥታ ከመረብ አሳርፏል ። የባዬር ሙይንሽን አዲሱ አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒንም ሆነ የቡድኑ አመራርን ከመቀመቻቸው ብድግ አስብሎ እንዲያጨበጭቡ ያስደረገ ግብ ። በዚህ ውብ ግብ የ34 ዓመቱ ቶማስ ለ710ኛ ጊዜ በመሰለፍ ከግብ ጠባቂው ሴፕ ማየር በአንድ በልጦ ክብረ ወሰን መስበር ችሏል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW