1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

ሳንቲም ፈንድሚ፤ ዲጅታል የዕርዳታ ማሰባሰቢያ መድረክ

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ጥቅምት 13 2017

ሳንቲም ፈንድሚ/SantimFundMe/ የተሰኘው ይህ ዲጅታል መድረክ ለጋሾችም ሆኑ ልገሳ የሚያስፈልጋቸው አካላት በቀላሉ እና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ የልገሳ ስራን እንዲያከናውኑ የሚያደርግ ነው ተብሏል። ዲጅታል መድረኩ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን አገልግሎት ይሰጣል።

ሳንቲም ፈንድሚ ዓርማ
ሳንቲም ፈንድሚ ፤ ዲጅታል በሆነ መንገድ እርዳታ ለማሰባሰብ የሚያስችል መድረክ ነው። ምስል SantimFundMe

ሳንቲም ፈንድሚ፤ ዲጅታል የዕርዳታ ገንዘብ ማሰባሰቢያ መድረክ

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ግለሰቦችን እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን ለመደገፍ  በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እና ጎፈንድሚ በሚባለው ዓለም አቀፍ መድረክ ገንዘብ ማሰባሰብ አሁን አሁን እየተለመደ የመጣ ተግባር ነው።ያም ሆኖ  በዚህ የገንዘብ አሰባሰብ ላይ የተዓማኒነት እና የተደራሽነት ጉዳይ ተደጋግሞ ሲነሳ ይስተዋላል።
ይህንን በመገንዘብ ይመስላል ሳንቲምፔይ ፋይናንሻል ሶሉሽን የተባለ ሀገር በቀል የገንዘብ ነክ ቴክኖሎጅ ተቋም ፤ በቅርቡ ሳንቲም ፈንድሚ/SantimFundMe/ የተባለ   የእርዳታ ገንዘብን ለማሰባሰብ የሚያገለግል አዲስ ዲጅታል መድረክ  ይፋ አድርጓል።
ይህ ዲጅታል መድረክ ለጋሾችም ሆኑ ልገሳ የሚያስፈልጋቸው  አካላት በቀላሉ እና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ የልገሳ ስራን እንዲያካሂዱ የሚያደርግ ነው ተብሏል።

 በገንዘብ አሰባሰብ ላይ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት

በሳንቲምፔይ ፋይናንሻል ሶሉሽን  የአካውንት ማኔጀር የሆነችው ወጣት ቅድስት አያሌው እንደምትገልፀው ይህ ዲጅታል መድረክ ይፋ የተደረገው ከዚህ ቀደም በገንዘብ አሰባሰብ ላይ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ነው።
«ሳንቲም ፈንድሚን [ይፋ]ያደረግነው ወደ ህብረተሰቡ ለመቅረብ ነው። [ ህብረተሰቡን] ለማገልገል የሰራነው ፕሮዳክታችን ነው።የቴክኖሎጅ «ፊን ቴክ ካምፓኒ»  ስለሆነ በተቻለ መጠን ያሉትን ነገሮች እየቀረፍን ለመሄድ ከመፈለግ አኳያ ነው።ስለዚህ ሳንቲም ፈንድሚ የሚፈታው ችግር ምንድነው፤ በጣም ብዙ [እርዳታ]  አለ ።በጣም ብዙ ገንዘብ በሀገራችን ይሰበሰባል።  ግን ትልቁ [ተግዳሮት]  የሚሆነው ብዙ ሰው «ኢንተርናሽናል አካውንት» ጎፈንድ ሚ ላይ[ የሚከፍትለት]   ያስፈልጋል።የሚደረጉት ልግሳዎች በሙሉ ሀገር ውስጥ የሌለ ሰው ገንዘብ የሚሰበስብባቸው ናቸው። ሀገር ውስጥ ያለ ሰው መለገስ ቢፈልግ አያስችለውም ማለት ነው።ሁለተኛ ደግሞ ያንን ጎፈንድ ሚ አካውንት [የሚከፍተው] በሌላ ሰው አካውንት ስለሆነ [ገንዘቡ የሚተላለፈው] አጠያያቂ በሆነ ሁኔታ ነው።አሁን እየተደረገ ያለው።»ካለች በኋላ፤ «ሳንቲም ፈንድሚ አንድ ለየት የሚያደርገው ነገር  [የበጎ አድራጎት] ድርጅቶች ራሳቸው አካውንታቸውን ከፍተው ፤የፈለጉትን ባንክ መርጠው እዚያ ባንክ ላይ [ልገሳ]  ይደረግላቸዋል። [የሚለግሰው]  ሰውም ከፈለገው የባንክ አማራጭ ቀጥታ ወደ ድርጅቱ መለገስ የሚያስችለው ነው።» በማለት ዲጅታል መድረኩ  ከዚህ ቀደም ያጋጥም የነበረውን ችግር እንደሚያቃልል ገልፃለች ። 

ቅድስት አያሌው፤በሳንቲም ፔይ ፋይናንሻል ሶሉዩሽን የአካውንት ማኔጀርምስል Kidist Ayalew

በውጭ ሀገራት ለሚገኙ ለጋሾችም ያገለግላል

ቅድስት እንደምትገልፀው ሳንቲም ፈንድሚ በሃገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን  በውጭ ሀገራት የሚገኙ ለጋሾችም ለሚፈልጓቸው ግለሰቦች ወይም ግብረሰናይ ድርጅቶች ቪዛ እና በማስተር  ካርድን በመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የክፍያ አማራጮችን ተጠቅመው ለበጎፍቃድ የሚውል  ገንዘብን መለገስ እንዲችሉ ያደርጋል። በዚህ ሁኔታ ከውጪ የሚደረጉ የገንዘብ ልገሳዎች የሚከፈሉት የቀኑን የውጭ ምንዛሪ ተመን መሰረት በማድረግ ነው።

ግለሰቦች እና፣ድርጅቶች ለተለያዩ የግል ችግሮች ፣ለትምህርት እና ለህክምና ወጪዎች ያለምንም ችግር  ገንዘብ ለማሰባሰብ ያስችላል የተባለው ይህ ዲጅታል መድረክ፤ ይፋ ከሆነ ካለፈው አንድ ሳምንት ወዲህ በርካታ የሀገር ውስጥ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለመጠቀም ፍላጎት እንዳላቸው ተገልጿል።
ዲጅታል መድረኩ ከቴሌብር፣ ኤም-ፔሳ እና ወደ 10 ከሚጠጉ ባንኮች እንዲሁም ማስተር እና ቪዛ ካርድ ጋር የተቀናጄ ሲሆን፤ ከሚያሰባስበው ገንዘብ ላይ የአገልግሎት ክፍያ አንድ በመቶ ብቻ እንደሚያስከፍል ኃላፊዋ ገልፃለች።ይህም ከጎፈንድሚ ጋር ሲነፃጸር የተሻለ መሆኑን ትናገራለች። «የኛ ክፍያ አንድ ፐርሰንት ነው።ይህንን ያደረግንበት ምክንያት የተለያዩ የአገልግሎት ክፍያዎች ስላሉብን ነው።እነዚህን ለመሸፈን ነው። ያን አንድ ፐርሰንት፤ እንጅ ለትርፍ ያቋቋምነው ወይም ገንዘብ እናገኝበታለን ብለን ያፋ ያደረግነው አይለም። ጎፈንድሚ ላይ ሰዎች የሰበሰቡትን ገንዘብ አያገኙም።ለምሳሌ አንድ የበጎ አድራጊ ድርጅት 1500 ዶላር ፈልጎ ከሆነ የጎፈንድሚው ሲስተም ከሰባት ፣ከስምንት እስከ አስራ አምስት ፐርሰንት ድረስ ነው የሚቆርጠው።ከዚያ በኋላ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ ያ ዶላር ተቀናንሶ ነው የሚገባው።በተለያዩ የአገልግሎት ክፍያዎች ምክንያት።ከምንም በላይ «ቻሪቲዎቹ» ገንዘቡን ተከታትለው ማወቅ አይችሉም።» ስትል ገልፃለች።

ሳንቲም ፈንድሚ በሀገር ውስጥ እና ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውን ሊጠቀሙበት የሚችል የገንዘብ ማሰባሰቢያ ነውምስል Kidist Ayalew

ዲጅታል መድረኩን ለመጠቀም  ሕጋዊ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ 

እንደ ቅድስት ገለፃ ፤ሳንቲም ፈንድሚ ማንኛውም ግለሰብ  እና ፣ ድርጅቶች እንዲጠቀሙበት ሆኖ  የተዘጋጄ ነው።ነገር  ግን ከገንዘብ ማሰባሰቡ በፊት መሟላት የሚያስፈልጉ ሕጋዊ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ ትላለች። «ሳንቲም ፈንድሚን ማንኛውም ሰው እንዲጠቀመው ማስቻል ትልቁ ዓላማችን ነው።እንደ እርዳታ ሁሉም ሰው እርዳታ የሚጠይቅበት ጊዜ ነው።በመንግስት የተቋቋሙ ድርጅቶችም እንዳሉ ሆነው።ስለዚህ  ሳንቲም ፈንድሚ መጀመሪያ ማድረግ የፈለገው ምንድነው እነዚህን ህጋዊነታቸውን ማረጋገጥ አለብን የሚል ነው።»ስትል ተናግራለች።
ስለዚህ የግልም ሆነ የድርጅት እርዳታ  መሰባሰብ ከመጀመሩ በፊት እርዳታው የሚያስፈልጋቸው መሆኑን የሚያሳዩ የተረጋገጡ ህጋዊ ሰነዶችን እንዲያቀርቡ ይደረጋል ስትል አብራርታለች።ይህም መድረኩን ያለ አግባብ እንዳይጠቀሙበት ለማድረግ ይረዳል ብላለች።

ሳንቲም ፈንድሚ ከጎፈንድሚ ጋር ሲነፃጸር የአገልግሎት የክፍያው አነስተኛ ነው ምስል Kidist Ayalew

በአምስት ቋንቋዎች የሚሰራ በመሆኑ ለአጠቃቀም ቀላል ነው 

ዲጅታል መድረኩ  የበይነመረብ ግንኙነት የሚፈልግ ሲሆን፤ቅድስት እንደምትለው ለአጠቃቀም ምቹ እንዲሆን በአምስት ቋንቋዎች ማለትም በእንግሊዝኛ ፣በኦሮምኛ፣በአማርኛ ፣በትግርኛ እና በሶማልኛ ቋንቋዎች የተዘጋጄ ነው። የአጠቃቀም ሂደቱም ማንኛውም ሰው እንዲጠቀምበት ቀለል ተደርጎ መሰራቱን አስረድታለች።
ይህ ዲጅታል መድረክ ተጠቃሚዎች የራሳቸዉን የማህበራዊ መገናኛ ትስስር ገፆችን ማጋራት እንዲችሉ ተደርጎ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በለጋሾች በኩል ያለው የአጠቃቀም ሂደትም ብዙ ውስብስብ አለመሆኑን ገልፃለች።

በዲጂታል ስርዓቶች ግብይቶችን ቀላል እና ደህንነቱ የተጠበቀ የማድረግ ተልዕኮ ይዞ በጎርጎሪያኑ 2019 ዓ/ም የተመሰረተው ሳንቲምፔይ ፋይናንሻል ሶሉሽን አክሲዮን ማህበር፤ የተለያዩ የክፍያ አማራጮችን ለባንኮች፣ ለነጋዴዎች እና ለደንበኞች ያቀርባል። ሳንቲምፔይ ከሀምሌ  2022 ዓ/ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ  አማራጭ  የክፍያ ስርዓት ፈቃድ  የተሰጠው ሲሆን፤ በቅርቡ ይፋ ከተደረገው ሳንቲምፈንድሚ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መድረክ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም ሌሎች ሶስት ገንዘብ ነክ ዲጅታል አገልግሎቶችን ለተጠቃሚ ማቅረቡንም ኃላፊዋ ቅድስት አያሌው ገልፃለች።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW