1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕኢትዮጵያ

ሳዑዲ አረቢያ በ2024 ሰባት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከ100 በላይ የውጪ ዜጎች በሞት ቀጣች

Eshete Bekele
እሑድ፣ ኅዳር 8 2017

ሳዑዲ አረቢያ በተያዘው የጎርጎሮሳውያኑ 2024 ሰባት ኢትዮጵያውያን፣ ሦስት ሱዳናውያን እና አንድ ኤርትራዊን ጨምሮ ከ100 በላይ የውጪ ሀገራት ዜጎች በሞት መቅጣቷን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገበ። በውጪ ዜጎች ላይ ተግባራዊ የሚሆነው የሞት ቅጣት በዓመቱ የጨመረው ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።

እግሩ በካቴና የታሰረ እና ወታደር ቆመው
ሳዑዲ አረቢያ ሞት የተፈረደባቸውን ሰዎች አንገት በመቅላት ትታወቃለችምስል picture-alliance/dpa/R. Qutena

በሀገሪቱ ደቡብ ምዕራብ ክፍል በምትገኘው ናጅራን የተባለች ግዛት አደንዛዥ ዕጽ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በማስገባት የተከሰሰ የመናዊ ትላንት ቅዳሜ በሞት መቀጣቱን የሀገሪቱ ብሔራዊ የዜና ወኪል ዘግቧል። የብሔራዊው ዜና ወኪል ዘገባዎች ላይ በመመሥረት በተደረገ ቆጠራ በዕለተ ቅዳሜ የተፈጸመው የሞት ቅጣት ሊገባደድ አንድ ወር ገደማ ብቻ በቀረው የጎርጎሮሳውያኑ 2024 በሳዑዲ አረቢያ በሞት የተቀጡ የውጪ ሀገራት ዜጎችን ቁጥር 101 አድርሶታል። 

በፈረንሳይ ዜና አገልግሎት መረጃ መሠረት በ2023 በሳዑዲ አረቢያ 34 የውጪ ሀገራት ዜጎች በሞት ተቀጥተዋል። በ2022ም ቁጥሩ ተመሳሳይ ነበር። የዘንድሮው ካለፉት ሁለት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በሦስት እጥፍ ገደማ የላቀ ነው። መቀመጫውን በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ያደረገው የአውሮፓ-ሳዑዲ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት (ESOHR) እንደሚለው የዘንድሮው የሞት ፍርድ ክብረ ወሰን የሰበረ ነው። 

የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሰዎች ክፍል በዩናይትድ ስቴትስ ሀንትስቪልምስል DW/G. Schließ

 

የድርጅቱ የሕግ ዳይሬክተር ጣሐ አል-ሐጂ “ይኸ በውጪ ሀገራት ዜጎች ላይ የተላለፈ ከፍተኛው የሞት ቅጣት ነው። ሳዑዲ አረቢያ በአንድ ዓመት 100 የውጪ ዜጎችን በሞት ቀጥታ አታውቅም” ብለዋል። በፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ መሠረት ዘንድሮ ሳዑዲ አረቢያ ሰባት ኢትዮጵያውያንን በሞት ቀጥታለች። 

«የሳኡዲ አረቢያ መንግስት የሞት ቅጣት እርምጃ ከገባው ቃል ጋር ይጣረሳል»

ከኢትዮጵያውያኑ በተጨማሪ 21 የፓኪስታን፣ 20 የየመን፣ 14 የሶርያ፣ 10 የናይጄሪያ፣ ዘጠኝ የግብጽ፣ ስምንት የዮርዳኖስ ዜጎች በሞት ተቀጥተዋል። ከሱዳን፣ ከሕንድ እና ከአፍጋኒስታን ከእያንዳንዳቸው ሦስት፤ ከኤርትራ እና ከፊሊፒንስ አንድ በሞት ከተቀጡት መካከል ናቸው። 

በውጪ ዜጎች ላይ ተግባራዊ የሚሆነው የሞት ቅጣት በዓመቱ የጨመረው ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ምክንያት እንደሆነ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ ይጠቁማል። በዓመቱ ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ምክንያት 92 ሰዎች በሞት የተቀጡ ሲሆን 69 የውጪ ሀገራት ዜጎች ናቸው። 

ዲፕሎማቶች እና የለውጥ አራማጆች እንደሚሉት የውጪ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ዜጎች የፍርድ ቤት ሰነዶች ማግኘትን ጨምሮ ፍትኃዊ ፍርድ ለማግኘት ከፍተኛ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል። 
ሳዑዲ አረቢያ ሞት የተፈረደባቸውን ሰዎች አንገት በመቅላት የምትታወቅ ቢሆንም የመንግሥት ኦፊሴላዊ መግለጫዎች ግን የቅጣቱን አፈጻጸም ከመግለጽ ይቆጠባሉ። 

በነዳጅ ዘይት የበለጸገችው ሳዑዲ አረቢያ በጎርጎሮሳዊው 2023 እስረኞችን በሞት በመቅጣት ከቻይና እና ከኢራን በመቀጠል ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደነበረች የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ አምስነቲ ኢንተርናሽናል አስታውቆ ነበር። 

በ2024 በሳዑዲ አረቢያ በሞት የተቀጡ ሰዎች ቁጥር እስከ ዛሬ እሁድ 274 መድረሱን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ ያሳያል። 

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW