1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሴቶች በአፍሪቃ የተሻለ የፖለቲካ ውክልና አላቸውን ?

ዓርብ፣ ጥር 23 2017

በርካታ ተንታኞች በጋና በውሳኔ ሰጭ ቦታዎች ላይ የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ ነው ይላሉ።በቅርቡ የተመረጡት የጋናፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ 42 ሚኒስትሮችን ሲሰይሙ ከመካከላቸው 7ቱ ብቻ ናቸው ሴቶች። ሆኖም ጄን ናና ኦፖኮኩ አግየማንግ የመጀመሪያዋ የሀገሪቱ ሴት ም/ፕሬዝዳንት መሆናቸው ለውጡ እንደሚቀጥል ተስፋ አስጨብጧል።

የናሚብያ ምክትል ፕሬዝዳንት ኔቱምቦ ናንድ ንድየትዋህ
የናሚብያ ምክትል ፕሬዝዳንት ኔቱምቦ ናንድ ንድየትዋህ ምስል፦ Esther Mbathera/AP Photo/picture alliance

ሴቶች በአፍሪቃ የተሻለ የፖለቲካ ውክልና አላቸውን ?

This browser does not support the audio element.

የጋና ምክትል ፕሬዝዳንት  ጄን ናና ኦፖኩ አግየማንግ እና የናሚብያ ምክትል ፕሬዝዳንት ኔቱምቦ ናንዲ ንዳይትዋህ ከፍተኛው የስልጣን ማማ ላይ የሚገኙ ሴት የአፍሪቃ  መሪዎችን  ጎራ ተቀላቅለዋል። የቶጎዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክትዋር ቶሜጋህ ድጎቤን የናሚብያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር  ሳራ ኩጎንግልውኣ አማድሂላን  የዩጋንዳዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮቢናህ ናባንጃ እና የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁዲት ሱሚንዋን ከፍተኛ የመንግሥት ሃላፊነት የተሰጣቸው አፍሪቃውያት መሪዎች ናቸው ። ታዲያ ይህ በአፍሪቃ ሴቶች የተሻለ የፖለቲካ ውክልና እንዳላቸው ማሳያ ይሆን?


የናምቢያ ሁለት ከፍተኛ የስልጣን እርከኖች የተያዙት በሴቶች ነው። የናምብያዋ ፕሬዝዳንትዋ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሴቶች ናቸው ። ይህ ለውጥ በጉልህ የሚታይ ነው። ከዚህ ሌላ ከሀገሪቱ ካቢኔ አባላት አምስቱ ሴቶች ናቸው። የዶቼቬለዎቹ ኦኬሪ ጂናዞና ካይ ኔቤ እንደዘገቡት የናሚብያ የሴቶች እና የጾታ እኩልነት፣የቤተሰብና የህጻናት ጉዳይ፣ ማኅበራዊ አካታችነትና ልማት፣ የማኅበራዊ ጥበቃና ማኅበራዊ ደኅንነት እንዲሁም የሀገር በቀልና እና ህዳጣን ጉዳዮች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በሴት ሚኒስትሮች ነው የሚመሩት። 

የአንጎላ ምርጫ፣ የአፍሪቃ ሴቶች አበሳ

ሩዋንዳ የሴቶች የስልጣን ውክልና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝባት ሀገር  ናት። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ስድስት ሀገራት ብቻ ናቸው በሕግ አስፈጻሚም ሆነ በሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶቻቸው ከ50 በመቶ በላይ የሴቶች ውክልና ያላቸው። በምክር ቤቶቿ 60 በመቶ ሴቶች የተወከሉባት ሩዋንዳ፣ ከዓለም የመጀመሪያውን ደረጃ ይዛለች። በዚህ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ሀገራት ውስጥ ኩባ፣ኒካራጉዋ፣ አንዶራ፣ ሜክሲኮ ኒውዚላንድ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ይገኙበታል። ሩዋንዳ ላስመዘገበችው ለዚህ ለውጥ በተለይ በምክር ቤት የሴቶች ውክልና ከፍ እንዲል በ2003 ዓ.ም. በጸደቀው ሕገ መንግሥትዋ ለሴቶች 30 በመቶ ኮታ በማስቀመጥ የወሰደችው ልዩ እርምጃ አስተዋጽኦ አድርጓል። የሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በፈቃደኝነት ለሴት እጩ ተወዳዳሪዎች  የራሳቸውን ኮታ መድበዋል።

 

የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁዲት ቱሉካ ሱሚንዋምስል፦ Xinhua/IMAGO


የዓለም የኤኮኖሚ ፎረም ፣በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን ያህል ሴቶች ለከፍተኛ ስልጣን እንደበቁ የፈተሸው የ2023 ዓም ዘገባው እንዳመለከተው ሩዋንዳና ሌሎች ናሚብያንና ደቡብ አፍሪቃን የመሳሰሉ ከሰሀራ በረሀ በታች ያሉ ሀገራት ጋር አንድ ላይ ሆነው ከአጠቃላዩ ድርሻ 70 በመቶውን የሴቶች ስልጣን ክፍተት ሸፍነዋል። ይህም ከደቡባዊ እስያ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም ከሰሜን አፍሪቃ ሀገራት በፊት ያለውን ቦታ እንዲይዙ አድርጓቸዋል። 


ይህ በእንዲህ እንዳለ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ፣ ማሊ እና ቻድ በምዘናው ከ62 በመቶ በታች ነጥብ በማስመዝገብ አነስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። የተመድ የሴቶችን ጉዳይ የሚከታተለው ክፍል እንደሚለው በአፍሪቃ ለሴቶች ከፍተኛ ስልጣን መስጠትን በሚመለከት አንዳንድ ለውጦች ቢታዩም በአሁኑ አካሄድ ግን የጾታ እኩልነትን እውን ለማድረግ ሌላ 130 ዓመት ሊወስድ ይችላል። በብዙ ሀገራት ሴቶች አድልዎና መገለል ይደርስባቸዋል፤  ይናቃሉም። ሮስ ሩበን የታንዛንያ ሴት የመገናኛ ብዙሀን ባለሞያዎች ማኅበር ዋና ሃላፊ ናቸው።እርሳቸው እንደሚሉት  ችግሩ ሴቶች ለከፍተኛ ሃላፊነቶች ብቁ ናቸው ተብሎ አለመታመኑ ነው። «ሀገሪቱን ለሚገዛው መንግሥት ከፍተኛ ሃላፊነቶች ሴቶች ብቃት አላቸው ተብለው አይታመኑም። ስለዚህ ከተግዳሮቶቹ አንዱ አንድም ሴት ለከፍተኛ ሃላፊነት አይገባቸውም የሚለው አመለካከት በሰዎች ውስጥ አሁንም መኖሩ ነው።  

የታንዛንያዋ ፕሬዝዳንት ሱሁሉ ሀሰን እንደ ገዥው CCM ፓርቲ እጩ በጥቅምት በሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ታንዛንያን እንደገና እመራለሁ የሚል ተስፋ አላቸው። በጥቅምቱ ምርጫ ሁለት ሴት ተፎካካሪ እጩዎች ይወዳደራሉ። አንደኛዋ ሱሁሉ ሀሰን ሲሆኑ ሁለተኛዋ ደግሞ ኅብረት ለለውጥና ግልጽነት በምህጻሩ ACT ወይንም ዋዛላንዶ የተባለውን ፓርቲ ወክለው የሚወዳደሩት ዶዶሮቲ ሰሙ ናቸው። ሮይበን እንዳሉት  ይህ የመጀመሪያ ባይሆንም እነዚህ ሁለት ሴቶች ለታንዛንያ ፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር መብቃታቸውን እንደ አንድ ትልቅ ምዕራፍ ነው ያዩት።  
« ከዚህ ቀደም ለዚህ ትልቅ የስልጣን ማማ ከተወዳደሩት አራት ሴቶች አብዛኛዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት ነበሩ። አሁን ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ገዥው ፓርቲ CCM ሴት እጩ መምረጡ ትልቅ ርቀት መሄዱን ያሳያል።» 

የታንዛንያ ፕሬዝዳንት ሳምያ ሱሁሉ ሀሰንምስል፦ Tanzanian State House Press

የ65 ዓመትዋ ሀሰን የታንዛንያ ፕሬዝዳንት የሆኑት ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ከ3 ዓመት በፊት ከሞቱ በኋላ ነው። አወዛጋቢዎቹን የማጉፋሊን ፖሊሲዎች ለመቀየር ቃል ቢገቡም ባለፈው ዓመት በተካሄደው አካባቢያዊ ምርጫ ተቃዋሚዎችን በተደጋጋሚ በማሰር በማገትና በመግደል ሲተቹ ነበር ። በሮይበን እምነት ፓርቲያቸው CCMም እድገታቸውን መመዘኖና ተከታትሎ ከሌሎቹ በተለየ ለቦታው የሚመጥኑ ናቸው የሚል አመለካከት አለው። 

በሶማሊያ ምርጫ የሴቶች ተሳትፎና የአውሮፓ ህብረት የአፍሪቃ ድጋፍ
በአንጻሩ እንደዶቼቬለዎቹ ኦኬሪ ጂናዞና ካይ ኔቤ  የጋና የምርጫ ስርዓት ሴቶችን የሚያበረታታ አይደለም። ምንም እንኳን ለ30 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የጾታ እኩልነት ሕግን ለማሻሻል ጥረት ቢደረግም ሀገሪቱ ይህ ሕግ ማጽደቁ የተሳካላት በታህሳስ ከተካሄደው ምርጫ አስቀድሞ በጎርጎሮሳዊው 2024 ዓም ነው። ዓላማውም የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2030 ዓም ወደ 30 በመቶ ማሳደግ ነው። በርካታ ተንታኞች እንደሚያምኑት ሕጉ በመዘግየቱ በውሳኔ ሰጭ ቦታዎች ላይ የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ ነው።

ለምሳሌ በቅርቡ የተመረጡት የጋናፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ 42 ሚኒስትሮችን ሲሰይሙ ከመካከላቸው 7ቱ ብቻ ሴቶች መሆናቸው የተደባለቀ ስሜት አሳድሯል። ሆኖም ጄን ናና ኦፖኮኩ አግየማንግ  የመጀመሪያዋ የሀገሪቱ ሴት ምክትል ፕሬዝዳንት መሆናቸው ለውጡ እንደሚቀጥል ተስፋ አስጨብጧል። ማቪስ ዶምበጋናው የዴሞክራሲያዊ ልማት ማዕከል ተመራማሪና ተንታኝ እንደሚያምኑት ይህ ለጋና ትልቅ እምርታ ነው። «አንዳንድ ለውጦች እያደረግን መሆኑን ጠቋሚ ነው። ለተጨማሪ ሴቶች እድል መስጠትና ወደ ቦታው እንዲገቡ በሩን መክፈትም ነው። በዚህ ምክንያትም ባለፉት ዓመታት ብዙ ለውጦች አላመጣንም።» አንድ ጥናት እንዳመለከተው ሴቶች በፖለቲካ ቢሮዎች እንዲመረጡ ከወንዶች እኩል መብት ሊሰጣቸው ይገባል። ሴቶችም እኩል በሚያደርጉ መብቶች ሊደሰቱ ይገባል። 

ኂሩት መለሰ 

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW