1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሴቶች በዩንቨርስቲ እንዳይማሩ የከለከለው ታሊባንና የገጠመው ተቃውሞ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 14 2015

አፍጋኒስታን ውስጥ ሴቶች ዩኒቨርስቲ ገብተው እንዳይማሩ ታሊባን በዚህ ሳምንት ከከለከለ ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ተቃዉሞና ቁጣ ገጥሞታል። የአፍጋኒስታን ሴት ተማሪዎች እጃቸውን ላለመስጠት እየታገሉ እንደሆነ ነው የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ፔተር ሆርኑግ የዘገበው።

አፍጋኒስታን ምሩቅ ሴት ተማሪዎች
አፍጋኒስታን ምሩቅ ሴት ተማሪዎችምስል JAVED TANVEER/AFP

ታሊባንና የገጠመው ተቃውሞ

This browser does not support the audio element.

በአፍጋኒስታን ልጃገረዶች እና ሴቶች ላይ ታሊባን የሚያደርሰው ጭቆና እንደተሰጋው የማያባራ ሆኗል። 
የታሊባን መንግሥት ማክሰኞ ዕለት ወዲያው ተግባራዊ እንዲሆን በደነገገዉ አዲስ ደንብ መሠረት ሴት ተማሪዎች ከእንግዲህ ዩኒቨርስቲ ገብተው እንዳይማሩ ያግዳል።  ይህ ደንብ በወጣ ማግሥት ወደ ዩንቨርስቲ ግቢ እንዳይገቡ የተከለከሉት ሴት ተማሪዎች ምላሽ ፤  በሀዘን እና በቁጣ መካከል  ነበር ይላል፤ የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ፔተር ሆርኑግ ።  ተማሪዎቹ ተሸፋፍነዋል፣ በፍጥነት ይራመዳሉ  ፤ስጋታቸውም ፊታቸው ላይ ይነበባል። ይሁንና ተቃውሟቸው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲደርስ ጮክ ብለው ቁጣቸውን ይገልፃሉ። 

"ትምህርትን ፖለቲካ አታድርጉ" ይላሉ። መልዕክቱ ለታሊባን ነው። ለደህንነቷ ስትል ትክክለኛ ስሟን መናገር የማትፈልገው ወጣት ተማሪ ማህሮ ማህሪን ብላችሁ ጥሩኝ ትላለች። "ድጋሚ ሴቶች ዩንቨርስቲ እንዳይገቡ እየተከለከሉ ነው። እኛ ግን ዝም አንልም። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዲሁም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዝምታን መምረጣቸው አሳፋሪ ነው።"
ማህሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እገዳው የወጣ ሌሊት የታሊባንን ውሳኔ ማውገዛቸውን አልሰማችም ነበር።  ከማህሮ በትንሽ ርቀት ላይ ተሰባስበው ያሉ አምስት ሴት ተማሪዎች ቆመዋል። ሁለቱ ተቃቅፈው ያለቅሳሉ። ከእንግዲህ በኋላ ዩንቨርስቲም ይሁን የግል ከፍተኛ ተቋም ደጅ አትረግጡም መባላቸው ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ከቷቸዋል። 
ሌላዋ ሌኢላ  ብላችሁ ጥሩኝ ያሉ መምህርት ለጀርመን ARD የቴሌቪዥን የደቡብ እስያ ጣቢያ ስቱዲዮ በዋትስዓፕ በላኩት የድምፅ መልዕክት ታሊባን ድንጋጌውን እንዲሽር ትግል ከጀመሩ ሴቶች መካከል እንደሆኑ ይናገራሉ። "የመማር እና ማስተማር መብታቸው እንዲነጠቅ ከማይፈልጉ ሴቶች ጋር አንድ ላይ ሆነን ተቃውሞው እያሰማን እንገኛለን። የታሊባን አምባገነናዊ አገዛዝ እና ጭካኔውን አንቀበልም ለማለት ተሰባስበናል። የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲሰማው እንፈልጋለን። ምክንያቱም በእርግጠኝነት ታሊባን የበለጠ ይጎዳናል ።"
አፍጋኒስታን ውስጥ  በስልጣን ላይ  ያለው የታሊባን ቡድን ባለፉት 16 ወራት  16  የሴቶችን እንቅስቃሴ የሚገድቡ አዋጆች  ተግባራዊ አድርጓል ፣ ይህም በስልታዊ መንገድ ሴቶች ከስራ እንዲገለሉ፣ ሰውነታቸውን እንዲሸፋፈኑ እና እንደ መናፈሻ ቦታዎች ወይም የስፖርት መሥሪያ ቤቶች ያሉ ቦታዎችን እንዳይጠቀሙ የሚከለክል አዋጅ በማውጣት ነው።  ታሊባን ስልጣን ከተቆጣጠረ ጊዜ አንስቶ ልጃ ገረዶች ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ከልክሏል። 
ሴቶች ከጎናቸው አንድ ወንድ ሳይኖር ብቻቸውን መጓዝ አይችሉም።  ለሴቶች ትንሽም ተስፋ የተጣለባቸው ከፍተኛ ተቋማት ብቻ ነበሩ። እነዚህም ተዘግተው ከቆዩ በኋላ ባለፈው የካቲት ወር የተከፈቱ ሲሆን ከዚያን ጊዜ አንስቶ ወንድ እና ሴት ተማሪዎች በጥብቅ ተለይተው ይማሩ ነበር።  መምህራኖቻቸውም ሴቶች ብቻ ነበሩ። ይሁንና የማክሰኞው አዋጅ ይህንንም አሁን አስቁሟል።  መምህርት ሌኢላ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ንዴታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸዋል።"ሴቶች ከትምህርት መገለላቸው ከእስልምና ሃይማኖታችን እና ከማህበረሰባችን እሴቶች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጻረር ነው ። ይህም የሚያሳየው የታሊባን አገዛዝ ግዴለሽነት ነው።   የአፍጋኒስታን ህዝብ እንዲህ ያለውን ግድየለሽነት አይታገስም። አገዛዙ ስልጣኔ አይወድም። የአፍጋኒስታን ህዝብ ሴት ልጆቻቸው ላይ የሚፈፀመውን ንቀት በዝምታ አያልፍም።  ታሊባን በአፍጋኒስታን ህዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በሰው ልጆች ላይ ያነጣጠረ ርምጃ እየወሰደ እንደሆነ በድጋሚ አሳይቷል።"

ታሊባን ይህን እገዳ ለምን እንዳወጣ በግልፅ  ያለው ነገር የለም። ግልፅ የሆነው ነገር ቢኖር ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የገጠመው ተቃውሞ ነው። የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ሐሙስ ባወጣው መግለጫ ታሊባን ውሳኔውን እንዲቀለብስ ሚኒስትር ሜቭሉት ቻቩሶግሉ ጠይቀዋል።  «ይህ (ሴት ተማሪዎች ዩንቨርስቲዎች እንዳይገቡ የተደረገው) እገዳ እስላማዊም ሰብአዊነትም አይደለም። ስለሆነም ይህን አይነት ክልከላ አንቀበልም። ትክክል ነው ብለንም አናምንም። በአፋጣኝ አቋሟቸውን ይቀይራሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። እያልን ያለነው አንድ ሚሊዮን ስለሚጠጉ ሴት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነው ። ሴቶች ቢማሩ ምን ጉዳት አለው? አፍጋኒስታንን በምን መልኩ ይጎዳል? »
እስከ ጎርጎሮሲያኑ 2019 ዓ ም  ድረስ በሴቶች ላይ የጉዞ፣ ሥራ እና ሌሎች እንደ መኪና ማሽከርከርን የመሳሰሉ ገደቦችን ትፈፅም የነበረችው ሳውዲ አረቢያም ጭምር ታሊባን አቅጣጫውን እንዲቀይር አሳስባለች። የሳውዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዕሮብ ዕለት ባወጣው መግለጫ ለአፍጋኒስታን ሴት ተማሪዎች የተሰማውን “ሐዘን” በመግለፅ ሁኔታው «ሁሉንም ሙስሊም ሀገራት » ያስገረመ ነው ብሏል።
የከፍተኛ ትምህርት እገዳው የታወጀው በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጃገረዶች እና ወጣት ሴቶች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከወሰዱ ከሶስት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው።  በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሦስተኛ ዓመት የኢኮኖሚክስ ተማሪ ለሆነችው ሊዲያ ኤሊያስ በአፍጋኒስታን ሴት ተማሪዎች ላይ እየሆነ ያለው ነገር ጽሑፍ ለማመን ከብዷታል።«በጣም ይከብዳል ። ሴቶች መማር ያስፈልጋቸዋል። ምክንያቱ ምንድን ነው?  ስሰማ በጣም ነው ያዘንኩት። በኮቪድ ጊዜ በነበረው መስተጓጎል ራሱ የነበረው እቤት መቀመጥ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው።»

ለተቃውሞ ሰልፍ ካቡል ውስጥ አደባባይ የወጡ ሴቶችምስል privat
ሴቶች በዩኒቨርሲቲ እንዳይማሩ ከተከለከሉ በኋላ ተቃውሞ ሲያሰሙምስል Bilal Guler/AA/picture alliance

የሊዲያ ጓደኛ  የሆነችው የዓብቃል ፀጋዬ ስለ የአፍጋኒስታን ሴት ተማሪዎች እጣ ፈንታ ገና መስማቷ ነው።  እሷም የዩንቨርስቲ ተማሪ ስለሆነች ራሷን እነሱ ቦታ አድርጋ ነው የምታስበው፤  
« የሰው ልጅ በመማሩ ብዙ የሚያገኘው ነገር አለ። በትምህርት ዓለም ውስጥ ከተማሪዎች፣ ከመምህራን ከዘበኛው ሳይቀር ብዙ ትምህርት ይገኛል። አንዲት ሴት አትማሪም ከተባለች። ከቤት መውጫም የላትም። ትምህርት  ገንዘብ ማግኛ ብቻ ሳይሆን የህይወት ነገሮችን ማግኛ አንዱ መንገድ ነው»

ሰላሳ የሚሆኑ የአፍጋኒስታን ሴቶች ትናንት ካቡል ውስጥ በቡድን አደባባይ በመውጣት የታሊባንን ዉሳኔ ማውገዛቸውን አንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ለፈረንሳይ ዜና ምንጭ ገልፃል። የተወሰኑም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግሯል። ኢትዮጵያዊቷ የዓብቃል ለመብት መቆም ያስፈልጋል ከሚሉት ሴቶች መካከል ናት።  እሷም ይኼን ከማድረግ ወደ ኋላ አትልም። «እኔ በእነሱ ቦታ ብሆን ሴቶች የሚያደርጉትን አደርጋለሁ። የአንድ ሰው ድምፅ ዋጋ እንዳለሁ አውቃለሁ። ስለዚህ ባለኝ አቅም የማህበራዊ ሚዲያን ተጠቅሜም ሊሆን ይችላል ድምፄን የማሰማ ይመስለኛል።  ነገሮችን በተጋፈጡ ጊዜ ነው ለውጥ ማምጣት የሚቻለው። መማር ሰብዓዊ መብት ነው። ስለዚህ ርግጠኛ ነኝ ለመማር ድምፄን የማሰማ ይመስለኛል።»

ብዙም ባይሆኑ ወንዶች የህክምና የዩንቨርስቲ ተማሪዎች አፍጋኒስታን ውስጥ አጋርነታቸውን ለማሳየት አደባባይ ወጥተዋል። ታሊባን ውሳኔውን ካልቀለበሰ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ እየተሰነዘረ ያለው ተቃውሞ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይችላል።  ዩናይትድ ስቴትስ፤ ጀርመን እና የአውሮፓ ህብረት አዲሱን እገዳ ካወገዙት መካከል ይገኙበታል። እሮብ ምሽት በጋራ ባወጡት መግለጫ «ታሊባን ሴቶችን ከአደባባይ መድረክ ለማጥፋት የሚያራምደው ፖሊሲ ታሊባን ከአገሮቻችን ጋር ለሚኖረው ግንኙነት መዘዝ ይኖረዋል።»  ሲል ያስጠነቅቃል።

ፔተር ሆርኑግ / ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW