ስለመጭዉ የኢትዮጵያ 2018 ምርጫ ኦፌኮ የሰጠዉ ገለጻ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 1 2017
ስለምርጫ 2018 የኦፌኮ ገለጻ
በሚቀጥለው ዓመት በኢትዮጵያ የሚያካሂደዉ 7ኛው ብሔራዊ ምርጫ በጠባብ የፖለቲካ ምህዳር እና በሁለት የአገሪቱ ክልሎች በሚስተዋሉ ግጭቶች ሊፈተን ይችላል ሲል የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አስታወቀ፡፡ ኦፌኮ ገለጻውን የሰጠው ከሰሞኑ የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የልዑካን ቡድንን ስለመጭዉ ምርጫ አዲስ አበባ በሚገኘዉ ዋና ጽ/ ቤቱ ዉስጥ ባነጋገረበት ወቅት ነው፡፡
ፓርቲው ለተመድ ልዑካን ቡድን ገለፅኩት እንዳለዉ፣ ኢትዮጵያ ዉስጥ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ነጻና ገለልተኛ ምርጫን ማካሄድ ቀላል ቀላል አይሆንም። በ2018 ዓ.ም. ለሚካሄደው 7ኛው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ ሁኔታዎችን ለመገምገም ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮች ጋር ሰሞኑን ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የተወያየው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምርጫ ጉዳይ ገምጋሚ ሉዑክ አስቻይ ሁኔታውን መገምገሙን ፓርቲው አስታውቋል፡፡ ኦፌኮ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ተአማኒነት ያለው የምርጫ ሂደት እንዲረጋገጥ መንግስት ሊያሟላቸው የሚገቡ "መሰረታዊ" ጥያቄዎችን በማቅረብ፣ የሀገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ አስመልክቶ ዝርዝር ግምገማ ስለማቅረቡም ተመልክቷል።የኦነግና ኦፌኮ «የሽግግር መንግሥት» ምስረታ ምክረሃሳብ
በኦፌኮ ዋና ጽ/ቤት በተካሄደው ስብሰባ ላይ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ህብረት ቢሮ (UNOAU) የምርጫ ድጋፍ ክፍል ዋና ኦፊሰር አኪንየሚ አዴግባላን እና በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሰላምና ልማት አማካሪ ዶ/ር ዘቡሎን ሱይፎን ጨምሮ አራት አባላት ያለው ልዑክ መሳተፋቸውም ተነግሯል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ “መርጫን መሰረት አድርጎ የሚሰራው አራት አባላት ያሉት ልዑኩ በምርጫ አስቻይ ሁኔታዎች ላይ አነጋግረውን ተወያይተናል” ብለዋል፡፡
"ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ድምፅ የመስጠት ቴክኒካዊ ሂደት ብቻ ሳይሆን የዲሞክራሲያዊ ሂደት ውጤት ነው" ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ "ይህ ሂደት ዛሬ በኢትዮጵያ የለም። በጦርነት እና በፖለቲካ ስደት ውስጥ ተአማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ አይቻልም" በማለት ለልዑኩ ማስረዳታቸውንም አስገንዝበዋል።
በውይይቱ ወቅት “በዋናነት ገዢው ፓርቲ ለነጻና ታዓማኒ ምርጫ እንዳልተዘጋጀ፣ በሁለቱ የአገሪቱ ሰፋፊ ክልሎች ግጭት መኖሩን፣ የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበ እንደመጣ እና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት የሉም” የሚሉ ሃሳቦችንም ለልዑኩ እንዳነሱ ያከሉት ፕሮፌሰር መረራ በነዚህ አይነት ሁኔታ ነጻና ገለልተኛ ምርጫ ማካሄድ ያዳግታል ብለዋል፡፡ የፖለቲካ እስረኞች በአገሪቱ በስፋት እንዳሉም ለልዑኩ ማብራሪያ መስጠታቸውን ያከሉት መረራ፤ ለፖለቲካ ምህዳር መጥበብም እንደማሳያ ካቀረቡዋቸው ነጥቦች አንዱ የፓርቲያቸው በርካታ ጽህፈት ቤቶች መዘጋትና የአመራር አባላቱን መሳደድ በአስያየታቸው አንስተዋል፡፡ ኦፌኮ ከ 206 ጽ/ ቤቶቹ አዲስ አበባ፣ አሰላ እና አምቦ ያሉ ሶስት ጽህፈት ቤቶቹ ብቻ በስራ ላይ እንደሚገኙም የገለጹት ፕሮፌሰር መረራ፤ ጠባብ ያሉት የፖለቲካ ምህዳሩ አስረጂም ነው ሲሉ አስተያየታቸውን በማከል፤ ይሁንና ግን ለቀጣዩ ምርጫ ዝግጁ ለመሆን እየሰሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ “ባለው ሁኔታ እራሳችንን የማደራጀቱን ስራ ቀጥለናል” ያሉት ፕሮፌሰር መረራ ነጻ እና ገለልተኛ ምርጫ ግን አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ ምድር ይካሄዳል የሚል እምነት እንደሌላቸው አስረድተው በተለይም ከምርጫው መካሄድ በፊት ሰፊ ያሉት ሁሉን አካታች አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ጠይቀዋል፡፡የኦፌኮ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያስተላለፈው ጥሪ
ኦፌኮ አፋጣኝ የመተማመን እና የደህንነት እርምጃዎች እንዲሁም መሠረታዊ ተቋማዊ እና ህጋዊ ማሻሻያዎች ከምርጫው በፊት እንዲሰራባቸው እንደጠየቀም ጠቁሟል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሚቀጥለው ዓመት እንዲካሄድ እቅድ በተያዘለት ምርጫ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች እራሳቸውን አድራጅተው በመምጣት የሚያሸንፉ ከሆነ መንግስታቸውና ፓርቲያቸው ስልጣናቸውን ለማስረረከብ ሙሉ ፈቃደኛ ሆነው እንደሚሰሩ በቅርቡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት መጠቆማቸው ይታወሳል፡፡ በመሰል ስብሰባዎች ላይ ባለመሳተፍ ወቀሳ ከሚቀርብባቸው የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ኦፌኮ ግን ውይይቶቹ ከዚህም በላይ ጥልቅ መሆን አለባቸው ይላል፡፡ ፕሮፌሰር መረራ፤ ፓርቲያቸው በቅርቡ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጋር በመሆን ከተለያዩ የማህበረሰብ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ያቀረቡት ባለስድስት ነጥብ ምክረ ሃሳብ ለውይይት ካላቸው ዝግጁነትና ፍላጎት እንደሚመነጭም በአስተያየታቸው አስረድተዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ