ስለሴቶች መብት ምን ለውጦች አሉ? መሻሻል የሚገባቸውስ?
ማክሰኞ፣ መጋቢት 1 2018
የዓለም የሴቶች ቀን ባለፈው እሑድ ዕለት ሲታሰብ የተመድ በመላው ዓለም ካሉ አዳጊና አዋቂ ሴቶች ጋር በመተባበር መሠረታዊ መብቶችን ለማስከበበር እና ያንንም ለመጠቀም፤ እኩል መብት እና ፍትኅ እንዲሰፍን ተግባራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጠይቋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶችን መብት አክብሮ ስለማስከበር ሲነገር በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ አሁን ምን ለውጥ አለ? ምንስ መሻሻል ይኖርበታል?
የሴቶች መብት ዳራ
በዓለም ደረጃ የሴቶች የመብትና እኩልነት ጥያቄ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መነሳቱ ይታወቃል። ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም እንኳን በአጼ ኃይለሥላሴ ንጉሣዊ ዘመን የሴት የፓርላማ ተመራጭ የነበረበት አጋጣሚ ቢኖርም በብዛት ጉዳዩ በይፋ መነጋገሪያ የሆነውና በመንግሥትም ደረጃ ትኩረት የተሰጠው በደርግ ዘመነ ሥልጣን እንደነበር ይታወሳል። ታሪክ ወደኋላ ሲዳሰስም ሴቶች መሪዎች ብቅ ያሉባቸው አጋጣሚዎችም እንደነበሩ አይዘነጋም።
ለውጥ ሂደት እንደመሆኑ የሴቶች የመብት ጉዳይ የመነጋገሪያ መድረክ ካገኘ ወዲህ መሠረታዊ የሚባሉ አንዳንድ ለውጦች ታይተዋል። የተመድ እና የዓለም ባንክ ሰነዶች እንደሚያመለክቱት የቤተሰብ ሕግ፤ የመሬት ይዞታ ሕግ፤ ከሥራ መብቶች ጋር በተገናኘ የወሊድ እረፍትና ክፍያ ደንብ፤ የስነተዋልዶ ጤናን በተመለከተ አዎንታዊ መሻሻሎች ተከናውነዋል።ዛሬም ግን በማኅበራዊ ጉዳዮች በኩል ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን በተመለከተ በርካቶች ለአካላዊና ወሲባዊ ጥቃቶች መጋለጣቸው እንቀጠለ ነው። በየትኛውም የግጭት አጋጣሚዎች አዳጊም ሆኖ አዋቂ ሴቶች ግንባር ቀደም ሰለባዎች መሆናቸው ይታያል። የኤኮኖሚ ፍትኅም እንዲሁም አሁንም ያለማግኘታቸውንም መረጃዎቹ ያመለክታሉ። ይህም ዛሬም አብዛኞው ወገን የሴቶች መብትን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ እንደሌለው አመላካች መሆኑ ነው የሚገለጸው።
የኅብረተሰቡ ግንዛቤ
ስለሴቶች መብት ጉዳይ ሲነሳ ጉዳዩን «ጽንፍ ይወስዱታል» ተብለው ከሚተቹ የፌሚኒዝም አቀንቃኞች ጋር በማያያዝ ሊያጣጥሉ የሚሞክሩ ጥቂት አይደሉም። ምንም እንኳን ከሴቶች ባልተናነሰ የጥያቄውን አግባብነት ተቀብለው በማኅበረሰቡ ውስጥ በሁሉም ረገድ ለውጦች እንዲኖሩ የሚሟገቱና የሚሠሩ ወንዶች ቢኖሩም ዛሬም ግን ያልገባቸው በርካቶች መኖራቸውን ጋዜጠኛ ቅድስት ክፍለ ዮሐንስ ታነሳለች።
ቅድስት እንደምትለው የሴቶች የመብት ጥያቄ ያልገባቸው ወገኖች ወንድ ጠል አቋም የሚያንጸባርቁ ዋልታ ረገጥ አመለካከት ያላቸው አንዳንዶችን በስም እየጠቀሱ በጥቅሉ ጥያቄውን በማኅበራዊ መገናኛው የሚያጣጥሉ አልጠፉም። ይህ ግን መሠረታዊውን የሴቶችን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኤኮኖሚዊ ጥያቄዎች በአግባቡ በማንሳት መፍትሄ እንዲገኝ የሚንቀሳቀሱትን ሊከልል እንደይገባና በጉዳዩ ላይ ግንዛቤን ማስፋት እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ትሰጣለች።
የታዩ ለውጦች
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የሚታዩ መሻሻሎችን በተመለከተም በቅርብ ከምታውቀው የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ስላስተዋለችው ስትናገር፤ ወትሮ በኃላፊነት መሥራት የማይታሰበው ዛሬ ጥቂትም ቢሆኑ በዚህ ደረጃ መኖራቸውን አስተውላለች።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶችን የመብት ጥያቄዎች በሚመለከት የሚታየውን ለውጥ በትውልድ ከፋፍለን ብንመለከተው ይሻላል የምትለው ወ/ሮ ፍፁም አጥናፍወርቅ ኪዳነ ማርያም ናት። ወ/ሮ ፍፁም ለወጣቶች ከታደርገው የምክርና ድጋፍ በተጨማሪ በሴቶች ጉዳዮች ላይ ሥልጠና ጭምር በመስጠት ትታወቃለች።
ሴቶች እራሳቸውን እያበቁ በተለያዩ የፖለቲካና ኤኮኖሚያዊ እርከኖች በኃላፊነት መሠማራታቸው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታዩ ለውጤቶች ሊጠቀስ እንደሚችል የምትናገረው።
በበርካታ ድርሰቶቿ የምትታወቀው ደራሲ ውዳላት ገዳሙ ግማሹን የዓለም ኅብረተሰብ የሚወክሉት የሴቶች የመብት ጉዳዮች የመንግሥታት የመነጋገሪያ አጀንዳ ከሆነ መሰንበቱን ታነሳለች። ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ሴቶች የሚመሯቸው የመንግሥት መሥሪያቤቶችና ትላልቅ ድርጅቶች መኖራቸውን የመሻሻሎቹ ማሳያዎች ናቸው ባይ ናት። ይህም የሴቶችን ጥያቄዎች ለመፍታት ቀጥታ ተሳትፎ አለ ማለት እንደሚቻል ትናገራለች።
ሴቶች በአደባባይ እኩል እንዳይወጡ ወደ ኋላ ከሚይዛቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ ተተኪ ትውልድ የሆኑትን ሕጻናቶቻቸውን የሚከባከብላቸው ያለማግኘት ጥያቄ ነበር። ደራሲ ውዳላት እንደምትለው በአሁኑ ጊዜ ለዚህ መፍትሄዎች እየተገኙ ነው።
መሻሻል የሚገባው የጥቃት ሰለባዎች ፍትኅ
የሴቶችን መብቶች በተመለከተ ብዙ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች መኖራቸውን ያመለከተችው ደራሲ ውዳላት ገዳሙ፤ ከሁሉም በላይ ግን ለጥቃት ሰላባዎች ፍትኅ ቅድሚያ የሚሰጠው አሳሳቢ መሆኑን አመልክታለች። የጥቃት ሰለባዋ ቃል በቂ ሊሆን ይገባልም ነው የምትለው።
ቀደም ባሉት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ አንዲት ሴት ከሥራው ዓለም በጡረታ ተገልላ ከዚህ ዓለም በሞት ብትለይ የጡረታ ክፍያዋን ቤተሰቦቿ ማግኘት እንደማይችሉ ያስታወሰችው ጋዜጠኛ ቅድስት በኢህአዴግ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናት ይህ እንዲሻሻል በሙያዋ ምክንያት የሆነችበትን አጋጣሚም ታስታውሳለች።
በየዓመቱ የሴቶችን ቀን ዕለቱን ጠብቆ ከማክበር ባሻገርም መደረግ ስለሚገባቸው ወሳኝ ጉዳዮች በየጊዜው ክትትል ማድረግና መሥራት እንደሚገባም ትመክራለች።
በነገራችን ላይ በመላው ዓለም የገንዘብ፤ የደኅንነት፤ የቤተሰብ፤ የንብረት፤ የመንቀሳቀስ፤ የንግድ እና የጡረታ መብቶች በሚመለከት በሴቶች እና ወንዶች መካከል ያለውን ልዩነት ያስወገደ ሀገር የለም። የተመድ እንደሚለው እስካሁን በዚህ ረገድ ለወንዶች ከተሟላላቸው ውስጥ፤ ለሴቶች የተከበረው 64 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው። ስለሴቶች መብት ጥያቄ ማንሳት ማለት የቀጣይ ትውልን መጻኢ ሕይወት ማመቻቸት መሆኑን የተገነዘቡ ጥቂት አይደሉም። ያለ ጾታ ልዩነት ጉዳዩን ያልተረዱ መኖራቸውን በሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች መገመት ይቻላል። ሴቶች እናቶች፤ እህቶችና ሴት ልጆች ከምንም በላይ የትዳር አጋርና የቤተሰብ ዋልታዎች መሆናቸውን ልብ ይሏል። በርዕሰ ጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ያጋሩንን እናመሰግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር