ስለኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ውዝግብ የሕዝብ አስተያየት ከመቀሌ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 2 2017
ስለኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ውዝግብ የህዝብ አስተያየት ከመቀሌ
በኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት መካከል ያለው ውዝግብ ተከትሎ በትግራይ በነዋሪዎች ዘንድ ስጋት ተፈጥሯል። በመቐለ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች በሁሉም በኩል ያሉ ፖለቲከኞች ካለው መካረር እንዲቆጠቡ እንዲሁም ቅድሚያ ለሰላማዊ አማራጮች እንዲሰጡ ይናገራሉ። አንድ ያነጋገርናቸው የመቐለ ከተማ ነዋሪ፥ "አሁን ባለው አለመረጋጋት ምክንያት ሰው ስጋት ውስጥ አስገብቶታል። ማቀድ አትችልም፣ ስረህ መስራት አትችልም።ምክንያቱ ከዛሬ ነገር ምን ይሆናል የሚለው አታውቅም። ጦርነት ይነሳል የሚል ስጋት ውስጥ ነው ያለነው። ኑሮም ተወዷል" ብለዋል። ሌሎች በርካቶችም ተመሳሳይ ሐሳብ ይሰጣሉ። ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ፓርላማ ፊት ቀርበው ማብራሪያ ሰጥተው የነበሩት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ፥ ትግራይ ወደ ጦርነት እንዳይመለስ ኤምባሲዎች ጨምሮ ሌሎች ጥረት ያድርጉ ማለታቸው አይዘነጋም።
በትግራይ ጦርነት የሚከሰት ከሆነ ግን፥ ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሲያስጠነቅቁ ተደምጠዋል።
በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ የተናገሩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ በበኩላቸው በተሳሳተ አረዳድ እና ድምዳሜ ምክንያት ዳግም ጦርነት እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ገልፀው ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ጀነራል ታደሰ፥ ያሉ ልዩነቶች እና ያልተፈፀሙ የፕሪቶርያ ስምምነት ይዘቶች በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ፍላጎት በትግራይ በኩል አለ ያሉ ሲሆን፥ በትግራይ በኩል የሚጀመር ትንኮሳ ይሁን ጦርነት ግን አይኖርም ሲሉም ተደምጠዋል።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ