1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ስለደካማዉ የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ምን ያዉቃሉ?

ቅዳሜ፣ መስከረም 10 2018

ደቡብ ሱዳን አዲስ የእርስ በርስ ግጭት አፋፍ ላይ ያለች ይመስላል። ከጎርጎረሳዉያኑ 2018 ጀምሮ በሃገሪቱ የነበረዉን ከፍተኛ የእርስ በእርስ ጦርነት ያስቆመዉ የሰላም ስምምነት በተለይ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር በአገር ክህደት እና በሌሎች ወንጀሎች ከተከሰሱ እና እስር ላይ ከዋሉ በኋላ የሰላም ስምምነቱ ዳመና ያጠላበት ይመስላል።

ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር
ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻርምስል፦ Alex McBride/AFP

ስለደካማዉ የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ምን ያዉቃሉ?

This browser does not support the audio element.

ስለደካማዉ የደቡብ  ሱዳን የሰላም ስምምነት ምን ያዉቃሉ?

ደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር መታሰራቸዉን ተከትሎ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተቃዋሚዎች ሁሉ 'የአገዛዝ ለዉጥ' ለማድረግ ዝግጁ እንዲሆን አሳስበዋል። በጎርጎረሳዉያኑ 2018 የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች በሃገሪቱ ሰላም ለመፍጠር የደረሱት ስምምነት የመፍረስ አደጋ የተጋረጠበት እና ሃገሪቱ ዳግም የእርስ በእርስ ጦርነት አፋፍ ላይ የመዉደቅዋ ሁኔታ ለምን ይሆን?

ደቡብ ሱዳን አዲስ የእርስ በርስ ግጭት አፋፍ ላይ ያለች ይመስላል። ከጎርጎረሳዉያኑ 2018 ጀምሮ በሃገሪቱ የነበረዉን ከፍተኛ የእርስ በእርስ ጦርነት ያስቆመዉ የሰላም ስምምነት በተለይ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር በአገር ክህደት እና በሌሎች ወንጀሎች ከተከሰሱ እና እስር ላይ ከዋሉ በኋላ የሰላም ስምምነቱ ዳመና ያጠላበት ይመስላል።

በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ ሰኞ  የተቃዋሚዉ የሱዳን ህዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ (SPLM-IO) የህግ አውጭ ጆሴፍ ማልዋል ዶንግ በቁጥጥር ስር ከሚገኙት ከደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ከሪክ ማቻር ጎን እንደሚቆሙ እና በህጋዊ መንገድ የቀረበባቸዉን ክስ እንደሚከላከሉ ለዶቼ ቬለ አሳውቋል። እንደ ሕግ አዉጭዉ ገለፃ ፤ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት የሳልቫ ኪየር መንግስት የደቡብ ሱዳንን የሰላም ስምምነትን በማደናቀፍ እና ሚኒስትሮችን፣ ገዥዎችን እና የፓርላማ አባላትን ያለምንም ቅድመ ምክክር ከስልጣን በማባረር ብሎም የ «SPLM-IO» የሱዳን ህዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ -ተቃዋሚንም በማግለል ከሰዋል። 

በፓርላማው ውስጥም ተመሳሳይ ነገር አድርገዋል፣ ያለእኛ ፈቃድ እና ስምምነት ሰዎችን በማሰናበት እና በመሾም። ይህ ማለት መንግስት ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ አልያም ለማክበር ፍላጎት የለውም ነው።» ሲሉ ተናግረዋል። የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ያስቆመዉ ጉዳዮች እና የስምምነቱ ግብ ምን ነበር?

የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ግብ ምን ነበር?

ደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የጀመረው በጎርጎረሳዉያኑ ታህሳስ 2013 ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር የስልጣን ግብ ግብ ከጀመሩ በኋላ እንደነበር የሚታወስ ነዉ። እነዚህ ሁለት የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ለደቡብ ሱዳን ነፃነት ወሳኝ ሚና የተጫወተው የሱዳን ህዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ መሪዎች ናቸዉ። ይሁን እና ሁለቱም ከተለያዩ ጎሳዎች እና አንጃዎች የመጡ የደቡብ ሱዳን ዜጎች ናቸዉ። ኪር በደቡብ ሱዳን ብዙ ህዝብን የሚያቅፈዉ የዲንቃ ጎሳ አባል ሲሆኑ ማቻር ደግሞ በደቡብ ሱዳን በህዝብ ብዛት ሁለተኛ ከሆነዉ የኑዌር ጎሳ ተወላጅ ናቸዉ። በደቡብ ሱዳን በተለምዶ የኑዌር ጎሳ የዲንቃ ጎሳ ተቀናቃኝ ተደርጎ ይታያል። በዚህም ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ምክትላቸዉ የነበሩትን ሪክ ማቻርን መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ሞክሮ ከሸፈበት ሲሉ በመክሰስ መላውን ካቢኔ አሰናብተዋል። 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደዘገበው በአምስት ዓመታት የእርስ በርስ ግጭት ብቻ በደቡብ ሱዳን ወደ 400,000 የሚጠጉ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ከጠቅላላው 11 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅለዋል። የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ በሰላም ስምምነት የተቋጨዉ የደቡብ ሱዳኑ ግጭት ጦርነት፤ ዛሬ ወደ ጎሳ እና ጎጥ ፉክክር እና ሽኩቻ ተሸጋግሯል። የታጠቁ ቡድኖች በተባበሩት መንግስታት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የቀረቡትን የሰላም ተነሳሽነት በተደጋጋሚ ችላ ሲሉ ታይተዋል።

የነሐሴ 2018 የሰላም ስምምነት

የደቡብ ሱዳንን የእርስ በእርስ ጦርነት ያስቆመዉ የሰላም ስምምነት የተፈረመዉ በጎርጎረሳዉያኑ ነሐሴ 2018 ነበር። ስምምነቱን አዲስ አበባ ላይ እንዲፈፀም ያመቻቸዉ ደግሞ የምሥራቅ አፍሪቃ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ነዉ። በደቡብ ሱዳን ይታይ የነበረዉን ግጭትን ለመፍታት በተገባው ስምምነት መሰረት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር አሁን የተለያየውን SPLM-IO የሱዳን ህዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ -የተቃዋሚ መሪን ሪክ ማቻርን በምክትል ፕሬዝዳንትነት ወደነበረበት መልሰዋል። ይሁን እና ሌሎች የስምምነቱ ገጽታዎች፣ በተለይም ምርጫ ለማካሄድ እና የታጠቁ ኃይሎችን ወደ አንድ አካል ለማዋሃድ የተገባው ቃል በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ አልሆነም። 

ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻርምስል፦ Simon Maina/AFP

መጋቢት፣ 2025 ማቻር በቁጥጥር ስር ዋሉ

ማቻር ለቁም እስር የተዳረጉት ነጩ ጦር እየተባለ የሚጠራው፣ የኑዌር ተዋጊ ቡድን፣ በሰሜናዊ የላይኛው ናይል ግዛት የሚገኝን የደቡብ ሱዳንመንግሥት ጦር ተዋግቶ ወደ 250 የሚጠጉ ወታደሮችን ከገደለ በኋላ ነው። ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ለጥቃቱ ሪክ ማቻርን ተጠያቂ አድርገዉ ሲይዙ የማቻር የሱዳን ህዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ -ተቃዋሚ SPLM-IO ከነጩ ጦር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለዉም ሲሉ ለግድያዉ ተጠያቂ እንዳልሆኑ ይከራከራል። ይህን ተከትሎ በምላሹ የሪክ ማቻር የሱዳን ህዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ -ተቃዋሚ SPLM-IO በጎርጎረሳዉያኑ 2018 ከተደረሰዉ የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ነጥቦች መካከል አንዳንድ ስምምነቶችን በከፊል እንደሚሰርዝ ገልጿል።

በደቡብ ሱዳን በሚገኘዉ በባህር ኤል ጋዛል ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር እና የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኝ ጆሴፍ ሉአል ዳሪዮ እንደሚሉት ማቻርን ወደ ጎን ማግለልና ከፖለቲካዉ መንደር ማስወጣት የደቡብ ሱዳንን የሽግግር መንግስት ሙሉ በሙሉ አደጋ መጣል ነዉ።

«የማቻር ከቦታዉ ላይ ገለል መደረግ በተዋዋይ ወገኖች መካከል የሚደረገውን ድርድር እና መተማመንን ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶችን ሊያወሳስብ ይችላል። በማቻር ቡድን ውስጥ የስልጣን ሽኩቻ እንዲፈጠር፣ የአመራር ክፍተት እንዲፈጠር፣ አልፎ ተርፎም የሌሎች አካላት ጣልቃ ገብነትን መጋበዝ የሀገሪቱን መረጋጋት በእጅጉ ይጎዳል።» ሲሉ ዳሪዎ ተናግረዋል።

ማቻር በአገር ክህደት፣ ግድያ፣ በሴራ፣ በሽብርተኝነት፣ የህዝብ ንብረት እና ወታደራዊ ንብረቶችን በማውደም እና በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባቸዋል። መንግስታዊው የደቡብ ሱዳን ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቴሌቪዥን ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ እንደዘገበዉ የደቡብ ሱዳንፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻርን፤ በሀገር ክህደት በመወንጀል ከሥልጣናቸው አግደዋቸዋል። ማቻር ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ላይ በሀገር ክህደት እና በግድያ ወንጀል የተከሰሱት ከሰባት አጋሮቻቸው ጋር ነው። የተቃዋሚው የሱዳን ሕዝቦች የነፃነት ንቅናቄ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሪት ሙክ፤ የማቻርን ምክትል ፕሬዝዳንትነት እገዳ ውድቅ በማድረግ የ 2018 ቱ የሰላም ስምምነት ዋስትና ሰጪዎች ጣልቃ እንዲገቡ አሳስበዋል። ሙክ ፤ የኪር ፓርቲ የፖለቲካ የበላይነትን ለማረጋገጥ የፍትህ ስርዓቱን አሻሽለዋል ሲሉም ከሰዋል። በደቡብ ሱዳን የሚገኙ የመንግሥት ተቃዋሚዎች ደጋፊዎቻቸውን በማሰባሰብ የስርዓት ለውጥ እንዲደረግም ጠይቀዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻርምስል፦ Samir Bol/REUTERS

የትጥቅ ግጭት በአሁኑ ወቅት ደቡብ ሱዳንም ሆነ ዜጎችዋ ሊሸከሙት የማይችሉት ቀንበር ነው ሲሉ የተናገሩት የደቡብ ሱዳኑ የኢኮኖሚክስ መምህሩ አኮል ማዱክ "ጦርነት ሲኖር ኢኮኖሚው ይጎዳል - ዜጎችም ይሠቃያሉ። የዋጋ ንረት እየጨመረ፣ የንግድ ልውውጥ እየተስተጓጎለ፣ የመንግስት ሰራተኞች ለወራቶች ደመወዝ ሳይከፈል፤ብሎም  የጎረቤት ሱዳን ግጭት ተጨማሪ ጫና ሲፈጠር እያየን ነዉ ብለዋል።     

ካይ ኔቤ / አዜብ ታደሰ

ዮሃንስ ገብረግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW