1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

ስለ ሐማስ መሪ መገደል የአሜሪካና አጋሮቿ ዕይታ

ዓርብ፣ ጥቅምት 8 2017

የእሥራኤል ጦር የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋርን የጋዛ ሠርጥ ውስጥ ባደረሰው ጥቃት ትናንት መግደሉን ዐሳውቋል ። የመሪው መገደል በአካባቢው ሰላም ለማስፈን «መልካም አጋጣሚ ነው» ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ዛሬ ተናግረዋል ። የጀርመን ርእሰ-ብሔር ዖላፍ ሾልትስም ይህንኑ ከቤርሊን ደግመዋል። የተባለው ዕውን ይሆን?

የሐማስ መሪ
የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋርን የጋዛ ሠርጥ ውስጥ የእሥኤል ጦር ትናንት ባደረሰው ጥቃት ትናንት መግደሉን ዐሳውቋል ። ፎቶ፦ ከማኅደር ከሁለት ዓመት ግድም በፊት ሐማስ የተመሰረተበትን 35ኛ ዓመት ጋዛ ሠርጥ ውስጥ ሲያከብሩ የተነሳ ምስልምስል MOHAMMED ABED/AFP

የሐማስ መሪ መገደል ምዕራባውያን ያሉትን ሰላም ያስገኝ ይሆን?

This browser does not support the audio element.

የእሥራኤል ጦር የሐማስ አዲሱ መሪ ያህያ ሲንዋርን የጋዛ ሠርጥ ውስጥ ባደረሰው ጥቃት ትናንት መግደሉን ዐሳውቋል ። የመሪው መገደል በአካባቢው ሰላም ለማስፈን «መልካም አጋጣሚ ነው» ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን  ዛሬ ተናግረዋል ። ጀርመን ቤርሊን ውስጥ ከአውሮጳ መሪዎች ጋር የተወያዩት ፕሬዚደንቱ፦ እሥራኤል የሐማሱ መሪን መግደሏ «ፍትሕ የተፈጸመበት ቅጽበት ነው» ብለዋል ። ያህያ ሲንዋር «የአሜሪካኖች፤ የእሥራኤሎች እና የጀርመኖች ብሎም የሌሎች በርካቶች ደም እጁ ላይ ነበር» ሲሉም አክለዋል ።

ስቱዲዮ ከመግባቴ በፊት የዋሽንግተን ወኪላችን አበበ ፈለቀን በስልክ አነጋግሬዋለሁ ። ምዕራባውያን የሐማስ መሪ መገደል ሰላም ለማምጣት መልካም መንገድ ነው ቢሉም፥ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ግን «ፍልስጥኤም ነጻ እስክትወጣ ድረስ» እንፋለማለን ሲል ዛሬ ዝቷል ። የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር በእሥራኤል ጥቃት መገደል በምን መልኩ ነው በአካባቢው ሰላም ሊያመጣ ይችላል ተብሎ በዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿ የታሰበው የሚለውን ጥያቄ በማብራራት ይጀምራል ።

ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጋር የተወያዩት የጀርመን ርእሰ-ብሔር ዖላፍ ሾልትስ በበኩላቸው፦ የሐማሱ መሪ መገደል በጋዛ ሠርጥ የተኩስ አቁም ተፈጻሚ እንዲሆን ያስችላል የሚል ተስፋ እንደሰነቁ ገልጠዋል ። የሐማስ መሪ ያህያ ኢብራሒም ሀሰን ሲንዋር መገደል ከተኩስ አቁሙ ባሻገርም ታጋቾችን ነጻ ለማድረግ ስምምነት ላይ ለመድረስ ያግዛልም ብለዋል ። በዚህ ረገድ የአሜሪካኖቹ ዕይታ ምን ይመስላል?

በእሥራኤል ተደጋጋሚ የአየር ጥቃትና ድብደባ ምስቅልቅሏ የወጣው ጋዛ ሠርጥ ከፊል ገጽታምስል OMAR AL-QATTAA/AFP

ያህያ ሲንዋር፦ ሐማስ መስከረም 26 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ደቡባዊ እስራኤል ላይ በከፈተዉና በርካቶች በተገደሉበት ጥቃት ዋነኛ አቀናባሪ ነበሩ ተብሏል ። እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ኅብረት፣ ብሪታንያና ተከታዮቻቸዉ በአሸባሪነት የፈረጁት የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ ፖለቲካዊ መሪ እስማኤል ሀኒዬህ ኢራን ቴህራን ከተማ ውስጥ ባለፈው ሐምሌ ወር ሲገደሉ እሳቸውን የተኩ መሪም ነበሩ ። በሁለት ወራት ከዐሥራ አምስት ቀናት ግድም ልዩነት ብቻ እሥራኤል የሐማስ ወታደራዊ መሪ እሥማኤል ሐኒዬን  እና አዲሱ የፖለቲካዊም የወታደራዊ መሪም የነበሩት ያህያ ሲንዋርን መግደሏ ምን አንደምታ አለው በተኩስ አቁሙ ሒደት ላይ?

አበበ ፈለቀ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW