1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለ መርዓዊ ከተማ ግድያ የዓይን እማኝ ምስክርነት

ሐሙስ፣ የካቲት 7 2016

በመርዓዊ ከተማ ከተፈፀመው የሲቪል ዜጎች ግድያ በኋላ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች የገጠር ቀበሌዎች እና ወደ ባሕር ዳር ከተማ «እየተሰደዱ» መሆኑን አንድ የዐይን እማኝ ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። ኢሰመኮን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ግድያው በገለልተኛ አካል እንዲመረመር ያቀረቡትን ጥሪ መንግሥት ውድቅ አድርጓል።

ኢሰመኮ
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ምስል Ethiopian Human Rights Commission

ስለ መርዓዊ ከተማ ግድያ የዓይን እማኝ ምስክርነት

This browser does not support the audio element.

በመርዓዊ ከተማ ከተፈፀመው የሲቪል ዜጎች ግድያ በኋላ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች የገጠር ቀበሌዎች እና ወደ ባሕር ዳር ከተማ «እየተሰደዱ» መሆኑን አንድ የዐይን እማኝ ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። ወደ ባሕርዳር የሚሰደዱ የከተማዋ ነዋሪዎች «መንገድ ላይ ኬላ ተዘርግቶ አትገቡም እየተባሉ ነው»ም ብለዋል። «ሕዝቡ ከመጠን በላይ ተደናግጧል» ያሉት እኒሁ ሰው ከተገደሉት ሰዎች መካከል በግጭቱ ተሳትፎ የሌላቸው «የቀን ሠራተኞች» እንደሚገኙበት አስረድተዋል። መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በመርዓዊ ከተማ «ቢያንስ 45 ሲቪል ሰዎችን የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች «ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል» በሚል ምክንያት ከሕግ ውጭ መግደላቸውን» ይፋ አድርጓል። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ግን «የመከላከያ ኃይሉ የትኛውንም ዐይነት ሲቪል ዒላማ አላደረገም» በማለት ኢሰመኮም ሆነ ሌሎች አካላት ያወጡትን መግለጫ ውድቅ አድርገዋል።  

ስለ ግድያው ማን ምን አለ

የመርዓዊ ከተማነዋሪዎችን ጨምሮ ፣ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን 45፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ 80 እንዲሁም በኢትዮጵያ የአሜሪካ፣ የካናዳ፣ የእንግሊዝ ኤምባሲዎች እና የአውሮጳ ሕብረት የመንግሥት የፀጥታ ኃይላት በሰሜን ጎጃም ዞን መርዓዊ ከተማ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ. ም ሲቪል ንጹሐን ዜጎችን መግደላቸውን ገልፀው ድርጊቱ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጥሪ አድርገዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያ «የመከላከያ ኃይሉ የትኛውንም ዐይነት ሲቪል ኢላማ አላደረግም» ሲሉ አስተባብለዋል።ምስል Seyoum Getu/DW

ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን እንዳንገልጽ የጠየቁ አንድ የዓይን እማኝ መርዓዊ ከተማ ነዋሪዎቿ ከደረሰባቸው ጉዳት በኋላ ሕዝቡ ክፉኛ መደናገጡን፣ ብዙ ሰው ከተማዋን ጥሎ ወደ አጎራባች የገጠር ቀበሌዎች እየሸሸ መሆኑንና ፣ ከተማዋ በአሳዛኝ ድባብ ውስጥ መሆኗን ገልፀዋል።

 

የከተማዋ ነዋሪዎች «እየተሰደዱ» ነው መባሉ 

መንግሥታዊው የመብት ተቋም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በመርዓዊ ከተማ «ቢያንስ 45 ሲቪል ሰዎችን የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች «ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል» በሚል ምክንያት ከሕግ ውጭ መግደላቸውን» እንዳረጋገጠ ይፋ አድርጓል። ኮሚሽኑ «የፋኖ አባላት ናቸው» በሚል ተጠርጥረው የተያዙ እና ለጊዜው ብዛታቸውን ለማረጋገጥ ያልተቻለ ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል» ብሏል። ያነጋገርናቸው የዓይን እማኝ የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች የገጠር ቀበሌዎች እና ወደ ባሕር ዳር ከተማ «እየተሰደዱ» መሆኑንም ገልፀዋል። 

የመንግሥት ኮሙንኬሽን አገልግሎት ማስተባበያ 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያ «የመከላከያ ኃይሉ የትኛውንም ዐይነት ሲቪል ኢላማ አላደረግም» ሲሉ አስተባብለዋል። የዓይን እማኙ ግን በመከላከያ ሠራዊት አባላት የተገደሉት አብዛኞቹ የመርዓዊ ከተማ ነዋሪዎች የግጭት ተሳትፎ የሌላቸው « የቀን ሠራተኞች» ናቸው ነው የሚሉት። የአውሮጳ ኅብረት በቃል አቀባዩ በኩል ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል መርዓዊ ከተማ የተፈጸመው ግድያ በነጻ እና ገለልተኛ ቡድን ተጣርቶ የወንጀሉ ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል። በኢትዮጵያ የካናዳ ኤምባሲ ግድያው «እጅግ» እንደሚያሳስበው አስታውቋል። ድርጊቱን «የሚረብሽ» ያለው በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲ ደግሞ «ሙሉ ምርመራ» እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW