1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለ በቴ ኡርጌሳ ቤተሰቦች እስር የሒውማን ራይትስ ዎች ዘገባ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 1 2016

ሒውማን ራይትስ ዎች በአቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ አስራ አንድ ሰዎች እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል። ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የቀድሞው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የፖለቲካ ኦፊሰር የነበሩት የአቶ በቴ ወንድም ይገኙበታል። የኢትዮጵያ መንግሥት ግድያውን ለማጣራት ዓለም አቀፍ ዕገዛ ሊጠይቅ እንደሚገባ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ አሳስቧል።

አቶ በቴ ኡርጌሳ
የኢትዮጵያ መንግሥት የአቶ በቴ ኡርጌሳን ግድያ ለማጣራት ዓለም አቀፍ ዕገዛ ሊጠይቅ እንደሚገባ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ አሳስቧል።ምስል Private

ስለፖለቲከኛ ቀድሞ ፖለቲከኛ ቤተሰቦች እስር የሁማን ራይትስ ዎች ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የቀድሞ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ዑርጌሳ ባለፈው ሚያዚያ ወር በትውልድ ከተማቸው ምስራቅ ሸዋ ዞን መቂ ከተማ ተገድለው መገኘታቸውን ተከትሎ አገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ድምጻቸውን አጉልተው አሰምተው ነበር፡፡ ግድያውን ተከትሎ በወቅቱ መግለጫ የሰጠው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም በፖለቲከኛው ህልፈት እጃቸው ያለባቸው ገለልተኛ እና ሀቀኛ በሆነ መንገድ ተጣርቶ ተጠያቂ በማድረግ ለህዝብም ይፋ ይደረጋል ብሎ ነበር፡፡ በዚያው ሰሞንም በክልሉ የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ በግድያው የተጠረጠሩትን 11 ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቆ መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡፡

የሁማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ጭብጥ

የዓለማቀፉ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሁማን ራይትስ ትናንት ባወጣው መግለጫ የአቶ በቴ ዑርጌሳ ግድያን ተከትሎ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ወንድማቸውን ጨምሮ 11 ሰዎች እስካሁን ከህግ አግባብ ውጪ በሆነ የተራዘመ እስር ላይ ናቸው በሚል ተችቷል፡፡ ሰብዓዊ ተቋሙ “ባለስልጣናት በአስቸኳይና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ያለ ክስ በእስር ላይ የሚገኙትን ይልቀቃቸው” ሲል ጠይቋል፡፡ ሁማን ራይትስ ዎች በአቶ በቴ ግድያ ላይ ምርመራ ለማድረግ ዓለማቀፍ ድጋፍ ያሻልም ነው ያለው፡፡

የፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ ግድያን ማጣራቱ ተግዳሮት ገጥሞት ይሆን?
ባለፈው ሚዚያ ወር መጀመሪያ መቂ ከተማ ከተኙበት ሆቴል ተወስደው መገደላቸው የተገለጸው የቀስሞ ፖለቲከኛ አቶ በቴ ዑርጌሳ ከመኝታቸው በተወሰዱ ማግስት ማለዳውን ጭንቅላታቸውን በጥይት ተደብድበው አስከሬናቸው ከከተማው ጎዳና ላይ መገኘቱን ያስታወሰው የሰብዓዊ ተቋሙ መግለጫ፤ በወቅቱ የአከባቢው ፖሊስ የአቶ በቴ ወንድም ሚሎ ዑርጌሳ እና ሌላው የቤተሰብ አባል ኤባ ዋኔን ጨምሮ 13 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ጽፏል፡፡  

የሒውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ ላቲይታ ባድርምስል Human Rights Watch

የሁማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌይቲትያ ባደር “ያለ ክስ እየተፈጸመ ያለው የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እስሩ የግድያውን እውነታ ግልጽ ከማውጣት ይልቅ የመሸፋፈን አዝማሚን የሚያሳይ ነው” ብለዋል፡፡ እናም አሉ ባደር “ባለስልጣናቱ ያለ ህግ አግባብ የታሰሩትን በአስቸኳይ በመልቀቅ ለገለልተኛ ምርመራ ለዓለማቀፍ ድጋፍ በራቸውን ክፍት ማድረግ አለባቸው” ሲሉ መክረዋል፡፡

የፖለቲከኛ በቴ ኡርጌሳ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

ዶይቼ ቬለ ሰብዓዊ ተሟጋች ድርጅቱ ስላወጣው መግለጫ እና ተራዝሟል ስለተባለው እስራት፤ ብሎም በአቶ በቴ ግድያ እየተሰራ ስላለው የፍትህ ሂደቱ ለመጠየቅ በወቅቱ ምርመራውን ለጀመረው ለምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ በተለይም ለዞኑ ወንጀል መከላከል ፖሊስ ኃላፊ ኮማንደር መሀመድ ሀጂ ብደውልም ለዛሬ ጥረቱ አልሰመረም፡፡

የቀድሞ ፖለቲከኛ ቤተሰቦች አስተያየት

አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ አንድ የቀድሞ ፖለቲከኛ ቤተሰብ ግን የአቶ በቴ ዑርጌሳ ወንድም ሚሎ ዑርጌሳ እና የአጎታቸው ልጅ እንዲሁም አቶ በቴ ያደሩበት ኤቢ ሆቴል ባለቤት አቶ አበበን ጨምሮ 11 ሰዎች በታሰሩ በአንድ ወር ለፍርድ ቤት ብቀርቡም፤ እስካሁን የቀረበባቸው ማስረጃ በቂ አይደለም ያለው የዱግዳ ወረዳ ፍርድ ቤት በነጻ እንዳሰናበታቸው አስረድተዋል፡፡ ይሁንና እስካሁንም ድረስ በፍርድ ቤት ነጻ ከተባሉ በኋላ የተመሰረተባቸው ተጨማሪ ክስ በሌለበት በእስር ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ሒውማን ራይትስ ዎች በአቶ በቴ ግድያ የተጠረጠሩ አስራ አንድ ሰዎች እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል። ምስል John MacDougall/AFP/Getty Images

የፖለቲከኛ በቴ ህልፈትና የቤተሰቡ እጣ ፈንታ

“በወቅቱ 13 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው የተገለጸ ሲሆን 11ዱ በመቂ የታሰሩ ነበሩ፡፡ ሌሎች በአዳማ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ ሰዎች እንዳሉ ነበር የሰማነው፡፡ በመቂ ከታሰሩት ውስጥ የአቶ በቴ ወንድም ሚሎ፣ ጓደኛው እና አቶ በቴ በእለቱ ያደሩበት ሆቴል ባለቤት አቶ አበበ የሚባሉ፣ በእለቱ በሆቴሉ እንግዳ ተቀባይ የነበረች ሴት እና አቶ በቴ ተገድለው በተጣሉበት አከባቢ ብሎኬት ሚጠብቁ አንድ የጥበቃ ስራ ላይ የተሰማሩ ከታሰሩት 11 ሰዎች መካከል ናቸው፡፡ በወቅቱ ሚያዚያ ወር መጀመሪያ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ከአንድ ወር በኋላ ነበር ለፍርድ ቤት የቀረቡት፡፡ ከዚያን አንዴ ሶስቴ ፍርድ ቤት ተመላልሰው ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ በቂ ማስረጃ አልቀረበልኝም በማለት በነጻ አሰናብቶአቸው መዝገቡንም ዘጋ፡፡ ከዚያ በኋላ ራሱ ሁለት ወር ተቆጥሯል 11ዱም በዚያው በመቂ ፖሊስ ጣቢያ እንደታሰሩ ናቸው” ብለዋል፡፡

ሌላም የቤተሰብ አባል ተመሳሳይ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ አጋርተዋል፡፡

ሁማን ራይትስ ዎች ስለ ግድያ ምርመራ አስፈላጊነት

ሁማን ራይትስ ዎች በትናንት ሪፖርቱ አቶ ቤቴ በተገደሉበት ማግስት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በግድያው መንግስት እጁ እንዳለበት ተደርጎ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጨውን ዘመቻ መቃወሙን አስታውሶ፤ የአቶ በቴ ወንድም ሚሎ ዑርጌሳን ጨምሮ 11 ሰዎች በእስር ላይ የምገኙት ያለህግ አግባብ ነው ብሏል፡፡ ሰብዓዊ ተቋሙ አቶ በቴ ለአንድ ዓመት ገደማ ያለ ህግ አግባብ ታስረው በጠና ህመማቸው ምክንያት መፈታታቸውን አስታውሷል፡፡ 

ሁማን ራይትስ ዎች የአቶ በቴ የትግል አጋር የሆኑት ሰባት የኦነግ ከፍተኛ አመራሮችም ያለ ፍርድ ለአራት ዓመታት ገደማ በእስር ላይ መሆናቸውን በዚሁ ሪፖርቱ አካቷል፡፡ 
ዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩናይትድ ኪንሀግደም እና የአውሮፓ ህብረት መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሚያደርገው ምርመራ ላይ ጫና ልደረግበት እንደማይገባም ጥሪ ማቅረባቸውንም የሰብዓዊ ተሟጋች ተቋሙ ሪፖርት አስታውሷል፡፡

ሥዩም ጌቱ 

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW