ስለ ትግራይ ክልል ወቅታዊ የፀጥታ ኹኔታ የፓርቲዎች እና የሲቪክ ድርጅት አስተያየት
ሰኞ፣ ጥቅምት 9 2019
ስለ ትግራይ ክልል ወቅታዊ የፀጥታ ኹኔታ የፓርቲዎች እና የሲቪክ ድርጅት አስተያየት
በትግራይ ክልል የመከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ ሰላም ኃይል በህወሓት ላይ እየወሰዱት ነው የተባለ እርምጃ በኅብረተሰቡ ዘንድ ድጋፍ ያገኘ መሆኑን በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ። ፓርቲዎቹ ለዚህ ማሳያ ያቀረቡት ህወሓት በአጭር ጊዜ ጥቂት ከማይባሉ የክልሉ ከተሞች ተገፍቶ የወጣው በጦርነት ብቻ ሳይሆን ድርጅቱን ከሕዝብ ለመነጠል ተሠርቷል የተባለ ተግባር ውጤት በማምጣቱ ነው። ሌላኛው በክልሉ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ የፌዴራል መንግሥቱምሆነ ህወሓት በገቡበት ግጭት ምክንያት ሕዝብ የመንግሥት አገልግሎት እንዳያገኝ ብቻ ሳይሆን ክልሉ በጦርነትና በኢኮኖሚያዊ ድቀት ውስጥ እንዲያልፍ አድርገውታል ሲል ከሷል። ኹኔታውን በቅርበት የሚከታተል አንድ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ላይ የሚሠራ ሲቪክ ድርጅት በበኩሉ በክልሉ አሁንም "ጦርነት ቆሟል የሚያስብል ነገር እንደሌለ" ገልፀዋል።
መንግሥት በትግራይ ክልል አሥር ተግባራት ያሉትና ለስድስት ወራት የሚቆይ ባለአደራ አስተዳደርመመስረቱን፣ ይህንን ተከትሎ ህወሓት ውሳኔው "ሕጋዊነት ወይም ተፈጻሚነት እንደሌለው" ሊታወቅ ይገባል ማለቱን መነሻ በማድረግ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክልሉ አኹን ስላለበትን ኹኔታ ያላቸውን ምልከታ ጠይቀናል። ሁለት ፓርቲዎች ሕዝቡ ለህወሓት ድጋፍ መንፈጉን መመልከታቸውንና ይህም የሥራቸው ውጤት መሆኑን ተመሳሳይነት ያለው ሀሳብ አንፀባርቀዋል። የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ፖርቲ አንዱ ሲሆን የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ ሓለፎም ምርኤ ይህንን ብለዋል።
"የመከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ ሰላም ኃይል ተናበው ነው እየሠሩ ያሉት። በኅብረተሰቡ ዘንድም ተቀባይነት አለ። ሥጋት ግን አለ" የመቀሌው አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ "ወታደራዊ የሰው ኃይል እና ሎጂስቲክስ ለማንቀሳቀስ" በመንግሥት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ሲል የከሰሰው ህወሓት በአካባቢው "ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳይደረግ" ሰሞኑን አስጠንቅቋል። የትንሳኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አብርሃም ፅጌ እንደሚሉት ግን ይህንን የሚያደምጥ ሕዝብ የለም።
"ሕዝቡ አሁን ሥራውን እየሠራ ነው። እለታዊ እንቅስቃሴ የኤርፖርትም ይሁን የከተማዋ እንቅስቃሴ በተረጋጋ ኹኔታ እየሄደ ነው።" የስምረት ፖርቲ ቃል አቀባይ አቶ ሓለፎም ምርኤ እንዳሉት የህወሓት የውስጥ ለውስጥ ማስፈራሪያ ግን የበረታ ነው። "ማስፈራራት አለ ውስጥ ለውስጥ።"
የጦርነቱ ኹኔታ አሁን ምን ይመስላል?
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ኹኔታ ጦርነት ሳይሆን "የትጥቅ ግጭት" በሚል የሚገለጽ ነው ማለቱ ይታወሳል። የፌዴራሉ መንግሥት ግን ህወሓት ጀመረው ያለው ውጊያ "ጦርነት" መሆኑን እና እሱም "ለአራተኛ ጊዜ በህወሓት ሽንፈት ተጠናቋል" ማለቱ ይታወሳል። ይህ ዉጊያ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንታኞች እና የሕግ ባለሙያዎች ኹኔታው "አሸናፊና ተሸናፊ" የሌለው የእርስ በርስ ጦርነት መሆኑን ገልፀዋል። ሳልሳይ ወያነ ትግራይም ይህንኑ ያምናል። የፓርቱው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ብርሃነ አጽብሃ። "የመንግሥት ተቋማት የሚባሉት አገልግሎት መስጠት አቁመዋል። ክልሉ ግን በጦርነት እና በኢኮኖሚያዊ ድቀት ውስጥ እያሳለፈ እንደሆነ የሚጠቁም መረጃ አለ።"
በትግራይ ክልል ላይ ባለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ አተኩሮ የሚሠራው ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ ዛሬ ለዶቼ ቬለ እንዳለው፣ በክልሉ አሁንም ጦርነት ቆሟል ለማለት የሚያስደፍር ተጨባጭ ለውጥ የለም። "በተለያዩ አካባቢዎች ጦርነቶች እንደቀጠሉ ናቸው። የቆመ ነገር ያለ አይመስለኝም።"
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ