1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለ አስገዳጅ ጸረ-ኮሮና ክትባት የነዋሪዎች እሮሮ በርዋንዳ

ቅዳሜ፣ ጥር 14 2014

ርዋንዳ የኮቪድ-19 ወረርሺኝን ለመግታት በሚል ጸረ-ኮሮና ክትባትን በግዳጅ እየሰጠች ነው ሲሉ ነዋሪዎች በማማረር ላይ ናቸው። ከርዋንዳ ነዋሪ ግማሽ ከመቶ ያህሉ ማለትም 13 ሚሊዮን ለሁለት ጊዜ ጸረ-ኮሮና ክትባት ተወግቷል። ከ61 ከመቶው በላይ ደግሞ ቢያንስ ለአንድ ጊዜ ተከትቧል።

Afrika Ruanda Kigali Corona Impfung
ምስል Cyril Ndegeya/ Xinhua News Agency/picture alliance

በግዳጅ ተከተብን የሚሉ ቅሬታዎች በብዛት ይሰማሉ

This browser does not support the audio element.

ርዋንዳ የኮቪድ-19 ወረርሺኝን ለመግታት በሚል ጸረ-ኮሮና ክትባትን በግዳጅ እየሰጠች ነው ሲሉ ነዋሪዎች በማማረር ላይ ናቸው። ከርዋንዳ ነዋሪ ግማሽ ከመቶ ያህሉ ማለትም 13 ሚሊዮን ለሁለት ጊዜ ጸረ-ኮሮና ክትባት ተወግቷል። ከ61 ከመቶው በላይ ደግሞ ቢያንስ ለአንድ ጊዜ ተከትቧል። አንዳንድ ነዋሪዎች የተከተቡ ሰዎች ቁጥር እንዲህ ከፍ ያለው ክትባቱ በግዳጅ ስለሆነ ነው ሲሉ ይደመጣሉ። ዶይቸ ቬለ ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ደቡድ ርዋንዳ ውስጥ በምትገኘው የሙሃንጋ ወረዳ ነዋሪ ርዋንዳዊ በግዳጅ ክትባት መውሰዳቸውን ገልጠዋል። ችግር እንዳይደርስባቸው በሚልም ስማቸው አልተጠቀሰም። ነዋሪው ለመከተብ እጃቸውን በካቴና ታስረው መወሰዳቸውን ይናገራሉ።

«ማለዳ ዐሥር ሰአት ላይ የአካባቢያችን ጠርናፊ በራችን በርግዶ ገባ። ከእንቅልፌ በቅጡ ስላልነቃሁ መጀመሪያ ላይ ሌቦች መስለውኝ ነበር። ሦስት ሰዎች ደጃፌ ላይ ቆመው ወደ አካባቢው /ቤት እንድኼድ ነገሩኝ። ከዚያም ለባለሥልጣናት አስረከቡኝ። እዚያም ያለፍላጎቴ ልከተብ እንደሆነ ነገሩኝ። የአካባቢው ባለሥልጣንም ፖሊሶች በጠራራ በግድ እስክከተብ ድረስ ጠራራ ፀሐይ ላይ እንድቀመጥ አዘዛቸው።»

በግዳጅ እንደተከተቡ የተናገሩት ሰው ወደሚከተቡበት ክፍል ሲያመሩ በአምስት ፖሊሶች እና ስድስት ሰዎች ተከበው እንደነበረም ተናግረዋል።

«ሦስት ፖሊሶች መጡ እናም አምስት ኾኑ፤ ሌሎች ስድስት ሰዎችም ነበሩ። በአጠቃላይ 11 ሰዎች ከበውን ወደ አንድ ክፍል ውስጥ እንድገባ አዘዙኝ። በቡጢ ነርተው መሬት ለመሬት ጎተቱኝ። ከኋላ የታሰርኩበት ካቴና የእጄን አንጓ እስኪሰረስረኝ ድረስ አንድ ሰውዬ ጀርባዬን በጉልበቱ ፈጥርቆ ገፋኝ። የሚከትበው ሰውዬ መጥቶ እስኪከትበኝ ድረስም ትንፋሽ አጥሮኝ ጸጥ ልል ትንሽ ነበር የቀረው።»

ምስል Cyril Ndegeya/ Xinhua News Agency/picture alliance

ዋና ከተማዪቱ ኪጋሊ ውስጥ ባለሥልጣናት ያልተከተቡ ሰዎችን ፍለጋ ቤት ለቤት አሰሳ እያደረጉ ነው ሲሉ ሌሎች ነዋሪዎችም ተናግረዋል። በግዳጅ መከተብ ያልፈለጉ አንዳንድ ነዋሪዎች ወደ ጎረቤት ሃገራት ቡሩንዲ እና የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መሰደዳቸውም ተሰምቷል።

ርዋማጋና ከተሰኘች የሀገሪቱ ምሥራቃዊ መንደር የመጡ አንድ ሰው ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት፦ ባለሥልጣናት እሳቸውን እና ባለቤታቸውን በግዳጅ ሊከትቧቸው ሲሉ መኖሪያቸውን ጥለው ሸሽተዋል።

«ከባለቤቴ ጋር ነኝ ። የምናናግራችሁ እቤቴ ውስጥ ኾነን አይደለም። ባለሥልጣናቱ በግዳጅ ሊከትቡን ስለኾነ ከቤት ሸሽተን ተደብቀናል። እኔ የወባ በሽታ ስላለብኝ፤ ኮዋርቴም መድኃኒት እወስዳለሁ። እንዳይከትቡኝ ብለምናቸውም አሻፈረኝ ስላሉ ከቤት አምልጠን ሸሽተናል። ከነርስ ጋር እንደሚመጡ ነበር አስረግጠው የነገሩን። ከዚያም ወደ ክትባት ጣቢያው እንዲወስደኝ አንድ ሞተረኛ ላኩ። ሞተረኛው ለማኅበራዊ ጉዳዮች ጸሐፊዋ ነርሶችን ሊልክ እንደሆነ ነገረው። እነሱ ሲሄዱ እኛ አመለጥን።»

ሰውዬውን ዶይቸ ቬለ ባነጋገረበት ወቅት ወደ ቤታቸው አልተመለሱም ነበር። እንደሳቸው አባባል በግድ እንዲከተቡ የተነገራቸው እሳቸው ብቻ አይደሉም።  የእሳቸውን እና የሌሎች ሰዎች ምስክርነት ዶይቸ ቬለ ከሌላ ገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም። ኾኖም ዶይቸ ቬለ ይህንኑ የነዋሪዎችን አቤቱታ ይዞ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዋችን አነጋግሯል። ሁለቱም በአሁኑ ወቅት ርዋንዳ ውስጥ በግዳጅ ስለሚሰጥ የጸረ ኮሮና ክትባት ምንም መረጃ እንደሌላቸው ገልጠዋል።

ዶይቸ ቬለ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ የርዋንዳ ባለሥልጣናትንም ለማነጋገር ሞክሯል። የርዋንዳ የጤና ሚንሥትር እና ጠቅላይ ሚንሥትር ጽ/ቤት ለቀረበላቸው ጥያቄ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ መግለጫ አልሰጡም። የእንጎሮሬሮ ወረዳ ከንቲባ  ክሪስቶፈር ንኩሲ ግን የሚባለው ሐሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል። እንደውም አንከተብምም ያሉት በኋላ ላይ ሁሉም ነገር ትክክል መሆኑን ሲረዱ ተከትበዋል ብለዋል። በግዳጅ ክትባት ይሰጣል የሚባለው ሐሰት ነው በማለትም እሳቸው በሚያስተዳድሩት ወረዳ በግዳጅ የተከተበ የለም ሲሉ አክለዋል።ላለመከተብ ከባለቤታቸው ጋር እንዳመለጡ የጠቀሱት ርዋንዳዊ ከቤታቸው ሸሽተው የተደበቁ ሌሎች ሰዎች እንዳሉ ያሉበትንም ሊጠቁሙ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ምስል Cyril Ndegeya/ Xinhua News Agency/picture alliance

«እኔ ብቻ አይደለሁም። ከፈለጋችሁ የተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ሰዎች ያሉበትን ልጠቁማችሁ እችላለሁ። እና ክትባትን ዐታሳዩን እያልን አለመሆኑን ልትረዱ ይገባል። ሰዎች ስለዘመቻው የሚያስቡበትን ጊዜ ልትሰጧቸው ይገባል። ለምንድን ነው በግድ ክትባቱ የሚሰጠው? እናን ይበልጥ ያጓጓን ጥያቄ ለምንድን ነው ክትባቱ በግድ የኾነው የሚለው ነው። እባካችሁ እዚህ የሚሰማንን ስሜት እንዳታምታቱት። ከእምነት አለያም ከአስተሳሰብ ጋር አንዳችም የሚያገናኘው ነገር የለም። ሁሉም የሚጠይቀው ክትባቱ ለምን በግዳጅ ኾነ እያለ ነው። ምክንያቱም እንደዚያ እንዲደረግ የሚያዝ ሕግ የትም ቦታ አልተላለፈም።»

ርዋንዳ ውስጥ በግዳጅ ክትባት እንደሚሰጥ፤ እምቢ ያሉት ላይ አካላዊ አለያም ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት እንደሚደርስ የሚጠቁሙ መረጃዎች ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይካለፉት ሳምንታት አንስቶ በስፋት ይንሸራሸራሉ።

ባለፈው ታኅሣስ ወር ላይ ርዋንዳ ውስጥ በማኅበራዊ መገናኛ በስፋት በተሰራጨ የ30 ሰከንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ አንድ በዕድሜ የገፉ እና ልባሳቸው ያደፈ አዛውንት በኪንያርዋንዳ ቋንቋ መከተብ እንደማይፈልጉ ገልጠው በሩን ሲዘጉ ይታያሉ። ከጀርባ የሚሰማው ድምፅ ክትባቱ ለእሳቸው ደኅንነት እንደሆነ ሲገልጥ ይሰማል። ቀጥሎም ዕይታ ውጪ የኾነ ድምፅ፦ «ግን ክትባቱን የማይቀበሉ ከሆነ፤ ስለ ባሕሪዎ የሚቀርበው መረጃ ጥሩ አይሆንም» ሲልም ይደመጣል። ቆየት ብሎም ተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የታዩት አዛውንቱ መሬት ላይ ቁጭ ብለው ሌላ የወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሰ ሰው ትከሻቸው ላይ እጁን አሳርፎ የሚታይበት ፎቶግራፍ በስፋት ተሰራችቷል። በፎቶው ላይ ሦስተኛው ሰው አዛውንቱ ክንድ ላይ በመርፌ ሲወጋም ይታያል። ተንቀሳቃሽ ምስሉ እና ፎቶው በተቀረጹበት ጊዜያት መካከል ምን እንደተፈጠረ ግን ዐይታወቅም።

ዶይቸ ቬለ ተንቀሳቃሽ ምስሉ እና ፎቶግራፉ በአንድ ወቅት የኾኑ ክስተቶች ስለመሆናቸው ማረጋገጥ አልቻለም። የፎቶግራፍ ተንታኞች ግን ፎቶግራፉ ላይ የወታደራዊ የደንብ ልብሱ ላይ የሚታየው የርዋንዳ ሠንደቅ ዓላማ ዲጂታል ለውጦች እንዳሉበት ማስተዋላቸውን ገልጠዋል።  ዶይቸ ቬለ እነዚህኑ ምስሎችየጀርመን ዜና አገልግሎት ባለሞያዎች እንዲያጣሩ ዐሳይቷል። ባለሞያዎቹ ምስሉ ላይ ቴክኒካዊ ለውጥ አለያም ማሳሳቺያ እንደተደረጉ የሚያመላክቱ ምልክቶች ዐለማየታቸውን ጠቅሰዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW