ስለ አዲስ አበባ "ኮሪዶር" ልማት የመንግሥት፣ የተነሺዎች እና የመብት ድርጅት አስተያየት
ሰኞ፣ ሚያዝያ 13 2017
ስለ አዲስ አበባ "ኮሪዶር" ልማት የመንግሥት፣ የተነሺዎች እና የመብት ድርጅት አስተያየት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት በትንሳኤ በዓል አዲስ አበባ ካዛንቺስ አካባቢ ይኖሩ ከነበሩና ወደ ሌላ ቦታ ከተዛወሩ ሰዎች ፊት ቆመው "በዘር፣ በሃይማኖት እና በሰፈር ሳንከፋፈል ለለውጥ የምንተጋ እንድንሆን" የሚል ንግግር አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህ የኮሪደር ልማት ተነሺዎችን "በጋራ እንደተለመደው እየተጠያየቃችሁ የምትኖሩበት ኹኔታ ተፈጥሮላችኋል" ብለዋቸዋል።
በዚሁ የ "ኮሪደር ልማት" ምክንያት ቤታችሁ ሰነድ አልባ ነው በሚል ገርጂ አካባቢ የፈረሰባቸው ሰዎች ግን "የነበረን ማህበራዊ ኑሮ፣ እድር ተበትኖ" ያለምንም ካሳ እንዲሁ ቀርተናል ብለዋል።
"በዘር፣ በሃይማኖት እና በሰፈር ሳንከፋፈል ለለውጥ የምንተጋ እንድንሆን" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት በትንሳኤ ዕለት ብዙ የአዲስ አበባ ከተማ የታላቁ ቤተመንግሥት እና የካዛንቺስ አካባቢ "ኮሪደር" የተባለው የከተማ መልሶ ማልማት ሥራ ተነሽዎች በሚኖሩበት አዲስ መንደር ተገኝተው ያደረጉት ንግግር ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህ ይኖሩበት ከነበረው መሃል ከተማ ተነስተው 22 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በተሠራው ገላን ጉራ የተባለ መንደር እንዲኖሩ ለተደረጉ ነዋሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት "ልጆቻችሁ መልካም ትምህርት ቤት፣ መመገቢያ ቦታ" አግኝተዋል ብለዋል።
"ልማት ሲመጣ ብዙ አሉባልታ፣ ብዙ ስሞታ፣ ብዙ ክስ፣ ብዙ ወቀሳ ይኖራል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ወቀሳዎች ሳያስተጓጉሉን መልካም ሰፈር በማየታችን" ደስተኞች ነን ነው ያሉት።
"ከተማችን [አዲስ አበባ] ተጎሳቁላ ቆሽሻ ነበር። እኛ ደግሞ ባለቤቶች ነን። ሀገራችን ነው። ጉስቁልናዋ ያመናል፣ እንቀይረው ያልነው ለጋራ ጥቅም ለልጆቻችን ደስታ፣ መፃዒውን ዘመን ለማሳመር ብቻ ነው"።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህ የከተማ ልማት ውጥን ምክንያት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኑራቸው የተናጋ፣ መስተጋብራቸው የተበጠሰ፣ እጃቸው ላይ የነበረን በርካታ ሀብትና ንብረት ድንገት ያጡ፣ ከመኖሪያ ብቻ ሳይሆን ከመሥሪያ ቦታቸው ተነቅለው የቀሩት ጥቂት አይደሉም። ሕጋዊ ሰነድ ያላቸውም ይሁን የሌላቸው።
እነዚህ ሰዎች ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ገርጂ ወረዳ 13 ቤታቸው ሰነድ አልባ ነው በሚልና በዚሁ የከተማ ልማት ምክንያት ከ2003 ዓ. ም ጀምሮ የአየር ካርታ ማረጋገጫ የነበራቸው መመሆኑን የሚገልፁ ግን ቤታቸው የፈረሰባቸው ሲሆኑ፣ በስፍራው ለብዙ ዓመታት ይኖሩ እንደነበር የሚናገሩ አሁን ለማን አቤት እንደሚሉ እንኳን ግራ መጋባታቸውን በመግለጽ ላይ ያሉ ናቸው።
"13 ዓምት፣ 15 ዓመት፣ 20 ዓመት የኖረ አለ እዚያ ቦታ ላይ"።
እድር፣ እቁብ፣ ማኅበር ኢትዮጵያዊያን በየአካባቢያቸው በጋራ ተሳስረው የሚኖሩባቸው የአኗኗር ቁልፍ መስጋብሮች ናቸው።
ከካዛንችስ የተነሱ ነዋሪዎች ይህ እንደተጠበቀላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ የገርጂ አካባቢዎቹ ቤታቸውን ያጡት ግን የገጠማቸው በተቃራኒው እንደሆነ ይገልጻሉ።
"ድሮ የነበረን ማኅበራዊ ኑሮ፣ እድር ተበትኗል"
በአዎንታም በዓሉታም፣ ከውስጥም ከውጪም አስተያየቶች ያልተለዩት የኮሪደር ልማት አምነስቲ ኢንተርናሽናልሳይቀር "ሰዎችን በግዳጅ ማፈናቀል በአፋጣኝ እንዲያቆም" ጥያቄ ያቀረበበት ሆኗል።
ይሄው የመብት ተቆርቋሪ ተቋም የፌዴራል መንግሥት በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ክልሎች ለኮሪደር ልማት በሚል "በግዳጅ መፈናቀልን ለመከላከል ቁልፍ የሕግ እና የአሠራር ሥርዓቶች ባለማዘጋጀቱ የተጎጂዎችን ሰብአዊ መብቶች ጥሷል" ሲል እርምት እንዲደረግ በቅርቡ መጠየቁ ይታወቃል።
ሰለሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ነጋሽ መሐመድ