1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ስልጠና ህይወታቸውን የቀየረው ወጣት ሴቶች

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 11 2015

የኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ“ተመራቂዎች የቀደመ ህይወታችሁን በመርሳት በአዲስ መንፈስና የስራ ተነሳሽነት ራሳችሁን እንድትለውጡ አደራ”ብለዋል፡፡ ህይወት ሰርተን የምናገኛት እንጂ ተሰርታ አትጠብቀንም፣ የራሳችንን ህይወት የምንሰራትም፣ የምናበላሻትም እኛው ነንና ህይወትን እንስራት ብለዋል፡፡

Logo JeCCDO

ስልጠና ህይወታቸውን የቀየረው ወጣት ሴቶች

This browser does not support the audio element.

መንግስታዊ ካልሆነው ከ«ኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት» ባገኙት የስልጠናና የቁሳቁስ ድጋፍ ከአስቸጋሪ ህይወት መውጣታቸውን በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ ወጣት ሴቶች ተናገሩ።ድርጅቱ እንዳለው እስካሁን ከ300 በላይ ወጣት ሴቶችን በማገዝ በተለያዩ ስራዎች እንዲሰማሩ አድርጓል፡፡  ባለፉት 30 ዓመታት  ድርጅቱ የተለያዩ ማህበረሰብ አቀፍ እገዛዎችን በማድረግ ብዙዎች ከነበሩባቸው ችግሮች እንዲወጡ ሲያደርግ መቆየቱን የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ ተናግረዋል፡፡ 
ኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ከሚያደርጋቸው እገዛዎች መካከል እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ተግባራት ተሰማርተው ህይወታቸው ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ላመራ ሴት ወጣቶች ስልጠና መስጠትና በስራ እንዲሰማሩ በማድረግ ነው፡፡ ትናንት 100 የሚጠጉ በጭፈራ ቤት፣ በጎዳና፣ በሴተኛ አዳሪነትና በመሰል ስራዎች ተሰማርተው የነበሩ ወጣት ሴቶችን በተለያዩ ሙያዎች አስልጥኖ አስመርቋል፡፡ በምግብ ዝግጅት ሰልጥነው ከተመረቁት መካከል አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው ተመራቂ፣ 
“ህይወቴ በጣም ያስጠላ ነበር፣ 4 ዓመታት ጭፈራ ቤት ሰርቻለሁ፣ ምንም ለውጥ አልነበረኝም፣ እሰራለሁ፣ ይጠፋል፣ ኢየሩሳሌም በጣም ደግፎኛል፣ ምግብ ዝግጅት ሰልጥኛለሁ፣ አሁን (ምግብ ቤት) ሊከፈትልኝ ነው በጣም ደስ ብሎኛል፣ ሶስት ወር ሰልጥኛለሁ፣ ወደ ቀደመው ህይወት ለመመለስ ፍፁም አላስብም፣ እንዲያውም የበፊቱ ይፀፅተኛል፣ እስካሁን ያሳለፍነው ህይወት በጣም ያስጠላ ነበር፣ አሁን እንደገና እንደመወለድ ነው፡፡” ብላናለች፡፡ 
ከዚህ በፊት በፀጉር ሥራ ሙያ ተመርቀው አሁን በስራ ላይ ካሉት መካከል ወ/ት ቅድስት ዓለማየሁ የራሷን ሥራ በመስራት ኑሮዋ በእጅጉ መለወጡን ነግራናለች፡፡ 
“4ኛ ዙር ነው የተመረቅሁት፣ ከዚያ በፊት የነበረኝ ህይወት በጣም አስከፊና አሰልቺ ነበር፣ ያኔ እጣጣለሁ፣ አጨሳለሁ፣ እቅማለሁ፣ ከሰካራሙ ጋር አብሬ…፣ የሚያስጠላ ህይወት ነው የነበረኝ፣ ከህክምና ጀምሮ ብዙ ነገር ተደርጎልኛል፣ በኢየሩሳሌም ድጋፍ የሴት ፀጉር ስራ ሶስት ወር ሰለጠንኩ፣ 20 ሺህ ብር ድጋፍ ተደርጎልኝ፣ የራሴን ፀጉር ቤት ከፍቼ፣ እቁብ እየጣልሁ ጥሩ ኑሮ እየኖርኩ ነው፡፡” 
በኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት የባህር ዳር ቅርንጫፍ ፕሮጀክት አስተባባሪ ወ/ሮ አባይነሽ ሊቀመላኩ በተለይ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ያሉ ልጃገረዶችን ካሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለማውጣት የ3 ወራት ስልጠና፣ የቁሳቁስና ለስራ ማስኪያጃ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፣ ፕሮጀክቱ ለ5 ዓመታት የሚቀጥል ሲሆን፣ በቀጣይም ለሌሎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ ሴቶች ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመልክተዋል፡፡ 
“ፕሮጀክቱን እ. ኤ. አ. 2020 ነው የጀመርነው፣ የ5 ዓመት ፕሮጀክት ነው ወደ 309 በአስቸጋሪ ሁኔታ የነበሩ ሴቶችና ልጃገረዶችን፣ በማሰልጠንና በማቋቋም፣ እናግዛለን፣ የሚሰለጥኑት በዋናነት በወንድና በሴት ፀጉር ስራ፣ በምግብ ዝግጅት፣ በሱቅ ስራ፣ በበግና ዶሮ እርባታ፣ በልብስ ንፅህና አሰጣጥ በአጠቃላይ ከ14 ዓይነት የሙያ ስልጠናዎች በሚፈልጉት በአንዱ እንዲሰለጥኑ ይደረጋል፡፡” ነው ያሉት፡፡ 
የኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ በበኩላቸው “ተመራቂዎች የቀደመ ህይወታችሁን በመርሳት በአዲስ መንፈስና የስራ ተነሳሽነት ራሳችሁን እንድትለውጡ አደራ” ብለዋል፡፡ ህይወት ሰርተን የምናገኛት እንጂ ተሰርታ አትጠብቀንም፣ የራሳችንን ህይወት የምንሰራትም፣ የምናበላሻትም እኛው ነንና ህይወትን እንስራት ነው ያሉት አቶ ሙሉጌታ፡፡ 
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ህፃናት፣ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ የሺሐረግ ፋንታሁን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትኩረት በሚሰጧቸው ችግር ፈቺ የማህበረሰብ ሥራዎች መሳተፋቸው አርአያ መሆኑን ጠቁመው መንግስትም ለተመራቂዎች የተመቻቸ የስራ ሁኔታ እንዲኖራቸው ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ 
ከዚህ ቀደም ተመርቀው ውጤታማ ለሆኑ 13 ሴቶች ትናንት ለእያንዳንዳቸው የ8 ሺህ ብር ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፤ ኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ከአማራ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሌሎች ማኅበረሰብ አቀፍ እገዛዎችን ያከናውናል፡፡ 

ጣና ምስል፦ DW/Azeb Tadesse Hahn
ባህርዳር ከተማምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW


ዓለምነው መኮንን 

ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW