1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"ስምምነቱ ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ነው።" አምባሳደር ዴቪድ ሺን

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 24 2016

«በጂቡቲና በአዲስ አበባ መኻከል ያለው የትራንስፖርት መሠረተ ልማት፣በበርበራና በአዲስ አበባ መኻከል ካለው እጅግ የላቀ ነው።ስለዚህ፣በበርበራና አዲስ አበባ መኻከል ያለውን መስመር ለመገንባት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ካልወጣበት በቀር፣የወጪና ገቢ እንቅስቃሴውን ወደዚያ ለማዞር እጅግ የሚያስቸግር ነው የሚሆነው።»አምባሳደር ዴቪድ ሺን

Addis Abeba | Unterzeichnung des Memorandum of Understanding zwischen Äthiopien und Somaliland
ምስል TIKSA NEGERI/REUTERS

"ስምምነቱ ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ነው።" አምባሳደር ዴቪድ ሺን

This browser does not support the audio element.

የመግባቢያ ስምምነቱ ምንነት

በጎርጎሮሳዊው 2024 አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ላይ፣ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ፣በተፈራረሙት የመግባቢያ ሠነድ መሠረት፣ ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ የኤደን ባህረ ሠላጤ 20 ኪሎ ሜትር ላይ የጦር ሰፈር ለመገንባትና የበርበራ ወደብን ለመጠቀም የሚያስችል የ50 ዓመት ሊዝ ታገኛለች።በምላሹ ኢትዮጵያ የራስ ገዝ አስተዳደር ለሆነችው ሶማሌላንድ ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ ሃገር እንደምትሆንና፣ ለሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ቴሌኮሚኒኬሽን ድርሻ እንደምትሰጥ ተገልጿል።የኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ዉል ከቪየናዉ ስምምነት አኳያ


ስለስምምነቱ የአንጋፋው ዲፕሎማት አስተያየት

የኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የመግባቢያ ሠነድ ፊርማ ስምምነት ላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባደረጉት ንግግር "የኢትዮጵያ ስብራት ጥገና ቀን"ሲሉ ነበር የገለጹት። ይህ የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ ስምምነት፣ ያለውን አንድምታ በተመለከተ፣ በአፍሪቃ በተለይም በምስራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁት የቀድሞው ዲፕሎማት አምባሳደር ዴቪድ ሺን ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ስምምነቱ ብዙ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን ተናግረዋል።«በአእምሮዬ የሚመላለሰው ትልቁ ጥያቄ፣ኢትዮጵያ ለምን ይህን ለማድረግ ፈለገች የሚለው ነው። የጂቡቲን ወደብ በሌላ ለመተካት የተደረገ ጥረት ካለ አላየሁም።ምክንያቱም በጂቡቲና በአዲስ አበባ መኻከል ያለው የትራንስፖርት መሠረተ ልማት፣በበርበራና በአዲስ አበባ መኻከል ካለው እጅግ የላቀ ነው።ስለዚህ፣በበርበራና አዲስ አበባ መኻከል ያለውን  መስመር ለመገንባት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ካልወጣበት በቀር፣የወጪና ገቢ እንቅስቃሴውን ወደዚያ ለማዞር እጅግ  የሚያስቸግር ነው የሚሆነው።ኢትዮጵያ የወደብ «ባለቤት ሆነች» መባሉና የህዝብ አስተያየት"በመሆኑም የመግባቢያ ስምምነቱ፣ ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ በኩል ምርቶቿን ከማስገባት እና ከማስወጣት ይልቅ፣በኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ የኢትዮጵያን የጦር ሰፈር መመስረት ላይ ያተኮረ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው አምባሳደር ሺን ተናግረዋል።

በርበራ በኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ የሚገኝ ዓለም አቀፍ እውቅና ያልተሰጣት የሶማሊላንድ ወደብ ምስል Yannick Tylle/picture alliance

ስምምነቱ በኢጋድ ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ

ስምምነቱ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መንግስታት ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲቋረጥ ሊያደርገው ይችላል ያሉት የቀድሞው ዲፕሎማት፣በአካባቢው የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት(ኢጋድ)ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።"ኢትዮጵያና ሶማሊያ የድርጅቱ አባል እንደመሆናቸው መጠን፣ጉዳዩ በኢጋድ ጉዳዮችን በመወሰንና በማስፈጸም ረገድ ችግር ሊያስከትል ይችላል።ኢትዮጵያ በዚህ ስምምነት በርግጥም የምትገፋ ከሆነ ተግባራዊነቱ ላይ በርካታ ጥያቄዎችን ማስነሳቱ አይቀርም ።በተለይም በኤርትራ ዘንድ ፣ኢትዮጽያ በበርበራ በኩል የባህር ኀይል ጦር ሠፈር ለምን ለማቋቋም ፈለገች?  ዓላማው ምንድነው? የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል።ለዚህ ጥያቄ አስካሁን ምላሽ የለንም። ይህን ጥያቄ ደግሞ ኤርትራ ብቻ ሳትሆን ሌሎችም ያነሱታል ብዬ ዐስባለሁ።"አምባሳደር ሺን እንደሚሉት፣በአካባቢው ሃገራት ዘንድ፣የባህር በር የሌላት ኢትዮጵያ የባህር ኀይል የጦር ሠፈር ለማቋቋም የፈለገችበት ምክንያት ጥያቄዎችን የሚያጭር ብቻ ሳይሆን ሊያስቆጣም የሚችል ነው።የዐቢይ የወደብ መሻት ከኢትዮጵያ ጎረቤቶች ተቃውሞ ቢገጥመውም አላፈገፈጉም

የበርበራ ወደብምስል Yannick Tylle/picture alliance

ሶማሌላንድ የግዛቴ አንድ አካል ናት የሚለው የመቆዲሾ መንግስት፣ሶማሌላንድ ይህን ስምምነት ለማድረግ ሥልጣን የላትም በማለት በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ውድቅ ማድረጉ ይታወቃል።አምባሳደር ዴቪድ ሺን፣ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ሥምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አቅም አላቸው ወይ የሚለው ብዙ ጥያቄ የሚያስነሳ አንደሆነና ስምምነቱ በብዙ መልኩ ግልጽ አለመሆኑንም አብራርተዋል። ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ የምትሰጠው ዕውቅና፣ ሌሎች የአፍሪቃ ሃገሮችም ለራስ ገዝ አስተዳደሯ ዕውቅና እንዲሰጡ፣ በር ይከፍት ይሆናል የሚል ግምት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

ታሪኩ ኃይሉ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW