ስሞታ የቀረበበት ሀገራዊው የውትድርና ምልመላ እና የመከላከያ ሰራዊት ምላሽ
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 25 2017
ስሞታ የቀረበበት ሀገራዊው የውትድርና ምልመላ እና የመከላከያ ሰራዊት ምላሽ
በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተለያዩ አከባቢዎች እየተከናወኑ ነው በተባሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ምልመላ ከፍላጎት ውጪ እየተከናወነ መሆኑን የአይን ምስክሮች ተናግረዋል።
መከላከያ ሰራዊት ግን ግን እንደ ተቋም በሀገር አቀፍ ደረጃ እድሜ፣ ጤና እና ሚዛናዊ ተዋፅኦን ጨምሮ ሌሎች የመመልመያ መሥፈርቶች መሠረት በማድረግ ብቻ ወታደሮችን እየመለመለ መሆኑን በመግለጽ የቀረበበትን ክስ አጣጥሏል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ በጉዳዩ ላይ መረጃዎች እንደደረሱት አስረድቶ ሪፖርት እያጠናቀረ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ስማ ቸው እንዳይጠቀስ እንዲሁም ድምጻቸውንም እንዳንጠቀም ተማጽነው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የሰሜን ሸዋ ዞን ያያ ጉሌለ ወረዳ ፊታል ከተማ ነዋሪ በርካታ ወጣቶች ወደ ገቢያ ሲሄዱም ሆነ ያለፈቃዳቸው ለውትድርና ትፈለጋላችሁ በሚል እንደሚያዙ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በፊት ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ሕፃናትን ጨምሮ ሰዎች ከሕግ ውጪ ለሰራዊት ምልመላ በሚል ተይዘው ገንዘብ መጠየቃቸውን መግለጫ ማውጣቱ የሚታወሰው መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሁንም በአዲስ መልክ ከህጋዊ መስፈርት ውጪ የሰራዊት ምልመላ እየተደረገ መሆኑን መረጃ እንደደረሰውና ሪፖርቱን እያጠናቀረው እንደሚገኝ አስታውቋል። የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ለዶይቼ ቬለ እንደነገሩትም፤ “እንደገና ምልመላው መጀመሩን የደረሰን መረጃ አለ፡፡ ግን ክትትሉ ገና አልተጠናቀቀም” በማለት ሪፖርቱን በማጠናቀር ሂደት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ከአገር መከላከያ የመረጃውን ተጨባጭነት ለማረጋገጥ ለኢፌዴሪ መከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ዛሬ የእጅ ስልካቸው ላይ ብደውልም ምላሻቸውን አላገኘም፡፡
ይሁንና ኮሎኔል ጌትነት ከሰሞኑ እሮብ ሚያዚያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ከመከላከያ ሚዲያ ጋዜጠኞች ጋር አደረጉት ተብሎ በኢፌዴሪ መከላከያ ይፋዊ የማህበራዊ ገጽ በተጋራው መረጃ በጉዳዩ ላይ ሰፊ አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት ወሰድኩ ያለው ወታደራዊ እርምጃዎች
“በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት አንቀፅ 87 የመከላከያ ሠራዊት መርሆች ላይ የመከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ በተጨማሪ በህገ መንግስቱ የተሠጠውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መፈፀሙን ጨምሮ ህጋዊ መሠረት ያላቸውን ተልዕኮዎች አሠራር እና መመሪያን ተከትሎ ይፈጽማል” ያሉት ኮሎኔል ጌትነት ይህን ለመፈፀም ዝግጁነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባር በመሆኑ መተካካት የማያቋራጥ ተከታታይነት ያለው ሥራ ሆኖ መከላከያ በሚያወጣው መደበኛ የመመልመያ መሥፈርት መሠረት ወጣቶችን ወደ ሠራዊቱ የመቀላቀል ሥራ እየተተገበረ ሥለመሆኑ ተናግረዋል።
“መከላከያ እንደ ተቋም በሀገር አቀፍ ደረጃ እድሜን፣ ጤናን፣ ሚዛናዊ ተዋፅኦን ጨምሮ ሌሎች የመመልመያ መሥፈርቶች መሠረት ማሥታወቂያ በሚዲያ በክልል ዞንና ወረዳዎች ተደራሽ በማድረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት አግባብ መሥፈርቱን ያሟሉ ወጣቶችን ብቻ እንደሚመለምል የሚታወቅ እውነታ ነው” ያሉት ኃላፊው “የተለየ አመላካከትና ዓላማ” ያላቸው በሚል የከሰሷቸው ቡድኖች ከዚህ በተቃረነ አገላለፅ ከእድሜ፣ ከጤና እና ከሌሎች ጋር አያይዘው ሲተቹ፤ ትችታቸው ከእውነት የራቀ እና የአፍራሽነታቸው መሳያ ነው ሲሉ ከሰዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች በየፊናቸው በመቶዎች ገደልን አሉ
ኮሎኔል ጌትነት “ፀረ ሠላም ቡድኖች” ያሏቸውን እነዚህን “አፍራሽ” ብለው የጠሩዋቸውን አካላት በሀገር ማተራመስ ከሰውአቸው፤ “በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ግጭት ለመፍጠር መጀመሪያ ሠራዊቱን መንካት በሀሰት ስም ማጥፋት ብለው ያስባሉ” ብለዋል፡፡
“የተመለመለው ወጣት ከተመዘገቡት ቦታ ጀምሮ ማሠልጠኛ ድረስ በርካታ የቁጥጥር ሥርዓቶችን አልፎ ተገቢውን መሥፈርት ካሟላ ብቻ ወታደር እንደሚሆን እንጂ ስለተፈለገ ተብሎ የተመዘገበው ሁሉ ወታደር መሆን አይችልም” ሲሉም አስረድተዋል ነው የተባለው።
ግጭትን ለማሥወገድና ሠላምን ለማምጣት ሁሉም መሥራት እና መትጋት አለበት በማለት ጥሪ ያቀረቡት የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ግጭት በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ድሮን ንፁሃንን ጎዳ በሚል የሚሠራጭ መረጃም አሉባልታ ሲሉ ገልጸውታል፡፡
የወጣቶች ብሔራዊ ውትድርና በግዳጅ ወይስ በፍቃደኝነት?
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በህዳር ወር መግለጫው ከመከላከያ ሰራዊት መስፈርቶች ውጪ “ለምልመላ” በሚል ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን በግዳጅ በመያዝ፤ የተያዙ ሰዎችን ለመልቀቅ የገንዘብ ክፍያ የጠየቁና በሂደቱ የተሳተፉ የፀጥታ እና የአስተዳደር አካላት ላይ ተገቢው ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥም በወቅቱ ማሳሰቡ ይታወሳል።
በወቅቱ በተሰጠው ምክረሃሳብ ላይ የተገኘ ውጤት መኖር አለመኖሩን የተጠየቁት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኦሰመኮ) ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በወቅቱ ህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በመከላከያ ሚኒስቴር በኩል ለኮሚሽኑ በተጻፈው ደብዳቤ ማብራሪያ ብሰጠውም፤ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በኩል እስካሁንም የተሰጠው ምክረሃሳብ ላይ ምላሽ አለመሰጠቱንና ተጠያቂነቱም ለመረጋገጡ ማረጋገጫ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ “እስካሁን ድረስ ከኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ምንም ያገኘነው ምላሽ የለም” ያሉት ወ/ሮ ራኬብ ዛሬ በሰጡን አስተያየታቸው ይህን አክለዋል፡፡ “የመከላከያን በተመለከተ ወዲያው መልስ ስለተሰጠን ወዲያው አሳውቀናል” በማለት በኦሮሚያ ክልል በኩል ተጠያቂነት እንዲሰፍን ብጠየቅም ምላሽ አለመገኘቱን ገልጸዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ