1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሙዚቃአፍሪቃ

«ስሟ ጊታር ነው» ድምፃዊ ዮሃንስ ጌታቸው

ዓርብ፣ መስከረም 6 2015

ድምፃዊ ዮሃንስ ጌታቸውን በተለይ በቅርቡ ያወጣው «ስምሽ ማነው» የተሰኘው ዜማ ከህዝብ ጋር አስተዋውቆታል። ወጣቱ የሂሳብ አያያዝ ምሩቅ ሲሆን በዚህ ሙያ ከመስራት ይልቅ ሙዚቃ መጫወትን መርጧል።

Äthiopien  Sänger Yohannes Getachew
ምስል privat

This browser does not support the audio element.

እንደ ቲክቶክና ኢንስታግራም ያሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ በደንብ አስመስለው መተወን ወይም መዝፈን የሚችሉ ሰዎችን አስተውለን ይሆናል። አንዳንዶችም ይህንን መድረክ ተጠቅመው ስኬታማ ሆነዋል።  ዮሃንስ ጌታቸው በአሁኑ ጊዜ ላይ ብቅ ብቅ ከሚሉ ድምፃዊያን አንዱ ነው። ይህንን ከህዝብ ጋር ያስተዋወቀውን ሙዚቃ ከመጫወቱ በፊት በርካታ ሙዚቃዎችን በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት አሰራጭቷል። ከልጅነቱ አንስቶ ሙዚቃ ያንጎራጉር እንደነበር የነገረን ዮሃንስ ወደ ሙዚቃው ዓለም ከገባ ሶስት አመት ሊሆነው ነው።  « ቴሌግራም ላይ ድምፅ እየቀረጹ የሚልኩበት ግሩፕ ነበር። ሌሎች ልጆች ሲልኩ ሳይ እኔም ልሞክር አልኩና ላኩ። እና የሰው ምላሽ ቆንጆ ነበር። ከዛ ለምን በደንብ አልሰራም ብዬ ጀመርኩ።» ከዛም በኢንስታግራም እና ቲክ ቶክ ላይ በቪዲዮ ቀርፆ ማሰራጨት ጀመረ። በወቅቱ ይልካቸው የነበሩት ድምፆች ያለ ጊታር የተቀረፁ ነበር። አሁን አሁን ግን ከዮሃንስ እጅ ጊታር አይጠፋም። ሙዚቃዎቹ ደግሞ ቆየት ያሉት ናቸው። የድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ፣ መልካሙ ተበጀ፣ መሀሙድ አህመድ የሁሉም ቆየት ያሉ ዝነኛ ዘፋኞች የሙዚቃ ቅምሻ የዮሃንስ ገፆች ላይ ይገኛሉ።

«ስምሽ ማነው» የተሰኘው ዜማ ዮሃንስን ከህዝብ ጋር አስተዋውቆታል። ቪዲዮው ዩ ቲብ ላይ ከ 370 ሺ በላይ ተመልካቾችን አግኝቷል። « ግጥም እና ዜማውን የደረሱት ጋሽ አየለ ማሞ ናቸው። ማንዶሊን በመጫወት የሚታወቁ ትልቅ ሰው ናቸው። በድምፅ ደግሞ ያቀነቀነው ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ነው። » ይላል። ዮሃንስም ይህንን አስመስሎ ዘፈነ። ብዙ ተቀባይነት ስላገኘም ፍቃድ ጠይቆ በቪዲዮ መልክ ለመቅረፅ ወሰነ። ጊታር መጫወት የለመደው በራሱ ነው።
የ26 ት ዓመቱ  ዮሃንስ ቆየት ያሉ ሙዚቃዎችን መጫወት የመረጠው « ብዙውን ጊዜ ከኋላ ጀምረን ነው ወደራሳችን የምንመጣው። በሙዚቃ ኢንዱስትሪውም ወርቃማ የሚባለው ጊዜ በእነሱ ጊዜ ነው። የድምፅ መለኪያም የሚባሉት እነሱ አንጋፋዎቹ ናቸው።» ዮሃንስ ቲክቶክ ላይ 51 ሺ ፤ ኢንስታግራም ላይ ደግሞ ወደ 21 ሺ ተከታዮች አሉት። በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደዚህ ተቀባይነት ማግኘቱ ዮሃንስ «ጠንክሬ እንድሰራ ብርታት ሆኖኛል» ይላል። አሁን ደግሞ  « የራሴ የሆነ ስራ እያዘጋጀን ነው። ከዚህ የተሻለ ነገር ይዤ እመጣለሁ ብዬ አስባለሁ»።

ምስል privat

ዮሀንስ በአሁኑ ሰዓት የምሽት ክለቦች ላይ አድዋ ከተባለው ባንድ ጋር ይሰራል። ወደ ሙዚቃው ዓለም ከመግባቱ በፊት ደግሞ የሂሳብ አያያዝ ተማሪ ነበር። « በዲግሪ ተመርቄያለሁ። ያኔ እየተማርኩም  መስራት የምፈልገው ሙዚቃው ላይ ነበር። እና ያንን እንደጨረስኩ ወደሙዚቃው ገባሁ» ወጣቱ የሙዚቃ አቀንቃኝ ዮሃንስ ፣ቴሌግራም ፣ ቲክ ቶክ እና ኢንስታግራምን ለበጎ ተጠቅሞባቸው ስኬታማ ለመሆን ረድተውታል። ከራሱ ተሞክሮ ተነስቶ እንደሱ ተሰጥዎ ላላቸው ሌሎች ወጣቶች የሚመክረው ደፋር መሆንን ነው።  «መፍራት ሳይሆን ማሳየት እና አስተያየትን መቀበል ነው። አሁን ላይ ደግሞ ጊዜው የቴክኖሎጂ ስለሆነ ራስን ለማሳየት ግዴታ መድረክ መፈለግ አይጠበቅም። »

ልደት አበበ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW