ስድስተኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ
ሰኞ፣ ሰኔ 14 2013ኢትዮጲያዊያን ለክልላዊና ለፌደራል እንደራሴ ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ እጩዎችን ለመምርጥ የሚያስችላቸውን ድምፅ ከማለዳው አንስቶ እየሰጡ ነው። ለስድስተኛ ጊዜ በሚካሄደው የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት እጩዎች ምርጫ ለመሳተፍ ከ37 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን የአገሪቱ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።ይሁን እንጂ የፌደራሉ መንግስት አካል ከሆኑት ዘጠኝ ክልላዊ መስተዳድሮች መካከል የትግራይ ክልል በፀጥታ ፣ የሶማሌ ክልል ደግሞ ከህትመት ጋር በተያያዙ ችግሮች በዛሬው ቀን ድምፅ አይሰጥባቸውም። በዋና ከተማይቱ በአዲስ አበባ ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ህዝቡ ድምጹን እየሰጠ ነው። የዶቼቬለ ዘጋቢ ተዘዋውሮ ከተመለከታቸው የምርጫ ጣቢያዎች በአንዳንዶቹ ምድምጽ አሰጣጡ በተያዘለት ሰዓት ያለመጀመር ችግሮች ታዝቧል።ለአዲስ አበባ ምክር ቤት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢዜማው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በሚወዳደሩበት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 23 የምርጫ ጣቢያ 5 ላይ የድምፅ መስጫ ወረቀት ከሌላ የምርጫ ጣቢያ ጋር በመቀያየሩ ምክንያት ድምፅ መስጠት የተጀመረው ከጥዋቱ 2 ሰዓት 45 ደቂቃ ላይ ነበር።ምክትል ከንቲባዋ ቢሸነፉ ስልጣን ለማስረከብ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀው ምንም ይሁን ምንም ኢትዮጵያ የምታሸንፍበት ምርጫ እንደሚሆን እምነቴ ነው ብለዋል።በጅማ እና አጋሮ ከተሞች ከማለዳው 12:00 ሰዓት ጀምሮ ድምጽ መስጠት ተጀምሯል። በየድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ረዣዥም ሰልፎች ይታያሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በትውልድ መንደራቸው በሻሻ ድምጽ ይሰጣሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ምርጫው ዛሬ በባሕር ዳርና አካባቢው በሰላማዊ ሁኔታ ተጀምሯል። ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በ272 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የሀዋሳ ከተማ ጎህ እንደቀደደ በተከፈቱት የምርጫ ጣቢያዎች ህዝቡ ድምጽን እየሰጠ ነው። ህዝቡ ድምጽ እየሰጠ ነው። በድሬዳዋም በገጠር እና በከተማ በሚገኙ አርባ ሰባት የምርጫ ክልሎችና ሁለት መቶ ሀምሳ ስድስት የምርጫ ጣቢያዎች ህብረተሰቡ ድምፁን በመስጠት ላይ ይገኛል። በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫው ዘግየት ብሎ መጀመሩ ቅሬታ ቢፈጥርም ነዋሪው በምርጫው የሚፈልገውን እየመረጠ መሆኑን መራጮች ገልፀዋል።
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ሰሎሞን ሙጬ
ታምራት ዲንሳ
መሳይ ተክሉ